የህወሓት ሊቀ መንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ከመቓልሕ ትግራይ መጽሄት ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ የትግራይ ክልል ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በይፋዊ ድረገጹ አውጥቶታል፡፡ ከዚሁ ቃለምልልስ ቀንጨብ ያደረግነውን እነሆ፡፡
***
“….የ2010 ፈተና ግን የተለየ ፈተና ነው፡፡ አዲስ የመስመር ወይም የአሰላለፍ ማስተካከያ የሚጠይቅ አይደለም፡፡ ጥገኛው ሃይል በራሱ የብልሽት መንገድ ነው የመጣው፡፡ በ1994 የተሃድሶ ወቅት እንዳስቀመጥነው ጠላታችን ኪራይ ሰብሳቢነት ነው፤ እርሱ ላይ ማተኮር አለብን ብለን ነበር፡፡
አርሶ አደሩንም ሌላውንም ይዘን ኪራይ ሰብሳቢዎችን እንግጠም የሚል አቋም ነበረን፡፡ በዚያም መሰረት ብዙ ተራምደናል፡፡ ነገር ግን በሚገባ ስላልተወገነ ኪራይ ሰብሳቢው ወደ ስልጣን መጣ፡፡ ስለዚህ ጠላት ነው ብለን ያስቀመጥነው፤ ልናፈርሰው ይገባናል ያልነው፤ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚው ካልተቀየረ ያ ጠላት ሊፈርስ አይችልም፡፡
ስለዚህ በሂደት እያለ ተኮላሸ እንጂ አሁን አዲስ ሁነት አልተፈጠረም፡፡ የትግሉ አግባብ፤ ጠላት የምንለውም፤ የምንገነባው ስርዓትም እስከ 40 ዓመት ምን መሆን እንዳለበት ተቀምጧል ብለዋል፡፡
ውስጣዊ ትግል ስለተቀዛቀዘ፤ መገንባት ያለበት ስርዓት ስላልተገነባ ጥገኛው ተመልሶ የመምጣት ዕድል ነው ያገኘው፡፡ አሁን አዲስ መስመር አይደለም የሚያስፈልገን፡፡ መስመሩ እሱ ራሱ ነው፡፡ አሁን የሚያስፈልገን ትግል ነው፡፡ አሁን ያጋጠመንን አደጋ እንዴት አድርገን በፅናት እንመክተው የሚለው ካልሆነ በቀር መስመሩ ለረጅም ጊዜ የሚሆን ነው ብለዋል፡፡
ልማታዊ መንግስት የምንለው አብቅቶለታል ማለት አይደለም፡፡ አሁን ልማታዊው መንግስትና ህብረ ብሄራዊ ፌዴራሊዝም ነው በመፍረስ ላይ ያለው፡፡ አሁን ያለንበት ሁኔታ ከሌላው የተለየ ነው፡፡ የተለየ የትግል አግባብ ያስፈልጋል፡፡
እንደ ትግራይ ያስቀመጥነው አለ፡፡ ማዕከላችንን ትግራይ አድርገን እንስራ ነው የምንለው፡፡ በትግራይ ያለውን ችግር እየፈቱ በሃገር ደረጃ ደግሞ እንደ ህወሓት ከሌሎች ፌዴራሊስት ሃይሎች ጋር በመተባበር ግዴታህን መፈፀም ነው፡፡ የነበረን መስመር ሊቀጥል የሚችል ነው፡፡ የመስመር ለውጥ አያስፈልገንም፡፡
እነሱ የመስመር ለውጥ አድርገዋል፡፡ እኛ ጠላታችን ኪራይ ሰብሳቢ ነው እንላለን፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የምንለው ልማታዊ ዲሞክራሲ አይሰራም ነው የሚሉት፡፡ ነገር ግን ብዙ ልማት እንዳስገኘ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ መስመሩ እሱ ነው እንላለን፡፡ የትግል አግባብና ሰትራቴጂዎችን በማስተካከል መታገል ነው የሚጠይቀው፡፡
አሁን የጥገኝነት የበላይነት ነው ያለው፡፡ አሁን ያለንበት ፈተና ተሻግረነዋል የሚባል አይደለም፡፡ ገና ግጥሚያ ላይ ነን፡፡ ምከታ ላይ ነን፡፡ አሁን በገለፅነው አግባብ ገጥመን ልንሻገረው ይገባናል፡፡ በትግል ውስጥ እንገኛለን እንጂ ተፈትቷል ማለት አንችልም፡፡ በድምሩ የትጥቅ ትግሉ ፈተናዎች ታልፈዋል፡፡
በሰላም ወቅት ያጋጠመችንን አንዲት ፈታኝ መድረክም ተሻግረናታል፡፡
ሁለተኛዋን ለመሻገር ግን ገና በትግል ላይ ነን፡፡ ፍላጎታችን የተሻለ ውጤት ማምጣትና ማስተካከል ነው፡፡ ልናሸንፍ እንችላለን የሚል እምነት አለኝ ፡፡”