Connect with us

ሞያሌ-እንደ ቆንጆ ሴት የሚናጠቁባት የድንበር ከተማ

ሞያሌ-እንደ ቆንጆ ሴት የሚናጠቁባት የድንበር ከተማ

ህግና ስርዓት

ሞያሌ-እንደ ቆንጆ ሴት የሚናጠቁባት የድንበር ከተማ

ሞያሌ-እንደ ቆንጆ ሴት የሚናጠቁባት የድንበር ከተማ፤
ሥራና አብሮ መኖር የነዋሪዋ መኖሪያ ነው

ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ሞያሌ ከተማ ጎዳና ላይ ቆሞ እንደ ቆንጆ ሴት ሲል የንግዷን ከተማ ጽፏታል፡፡ የሞያሌዎች ጠባይ፣ የከተማቸውን ድምቀትና የራሱን ውሎ እንዲህ ያካፍለናል፡፡ | ከሄኖክ ስዩም በድሬቲዩብ

ድምቀቷ ድንበር አትመስልም፡፡ ከመሃሉ በላይ ደማቅ ናት፡፡ ግርግር የማይነጥፍበት ጎዳናዋ በንግድ ቀልቡን አጥቷል፡፡ ሞያሌ አየሯ ብቻ ሳይኾን ገበያዋም የሞቀ ነው፡፡ ጎዳናዋ ላይ ቆሜያለሁ፡፡ ሞተር ሳይክሎቿ ቀልብ የላቸውም፡፡ እዚህ የዓለም ውድ ጫማ በረዳው ደገፍ ያለ ጎዳና አዳሪ አድርጎት መመልከት ብርቅ አይደለም፡፡ ልባሽ በሽ ስለሆነ መዘነጥ ቄንጠኛ አያስብልም፡፡

ሞያሌ እንደ ቆንጆ ሴት ናት፤ ፈላጊዋ ብዙ ነው፡፡ ወዲያ የምታዩት ባንዲራ ከዚህኛው ጋር ቢለያይ አይግረማችሁ፡፡ አንዷ ከተማ ሁለት ክልል ውስጥ ተካታለች፡፡ እናም የሱማሌም የኦሮሚያም ባንዲራ ይውለበለብባታል፡፡ በእነኚህ ባንዲራ የሁለቱም ነኝ የምትለው ከተማ ግን ይበልጥ የኬኒያዎች ናት፡፡ የኬኒያ መኪና ይጋልብባታል፡፡ ኬኒያውያን እንዳሻቸው ይሆኑባታል፡፡

ከባህር ወለል በላይ አንድ ሺ ዘጠና ሜትር ከፍታ ላይ ያረፈች ከተማ ስለሆነች አየር ንብረቷ ሞቃታማ ነው፡፡
ስልጡን ከተማ ናት፡፡ ቀደምት ነዋሪዎቿ ግሪኮች ነበሩ፤ ምናልባትም ከእነኛ አውሮጳውያን ንግድና የሥራ ቅልጥፍናን ወርሳ የቀረች ከተማ ሳትሆን አትቀርም፡፡ ጾም አይታደርም፤ ሰው ሁሉ ይሮጣል፡፡ አዲስ አበባ ቡቲኩ ያሸበረቀበት ጫማና ልብስ የሚመረጠው ሞያሌ ጎዳናዎች ላይ ነው፡፡

ሱቆቿ ደማቅ ናቸው፡፡ ብዙ ነገር የሚገኝባት የለም ማለት የምትጠላ ከተማ መሆኗን አየሁ፡፡ የቶርሽን ጫማ ገበያዋ ግርግር ይበዛበታል፡፡ ጥሩ ዕቃ ጥሩ ቦታ ሄዷል፡፡ ሞያሌ በር ናት፡፡ ወደ ሩቁ የአፍሪቃ ሀገር የምታሻግር በር፡፡

ስንቱ አሁን በቆምኩበት አድርጎ ሀገር ጥሎ ጠፍቷል፡፡ የኬኒያ ምድር ታየኝ፡፡ ያ ሰፈር ሌላ ሀገር ነው፡፡ ያ ሰፈር ውጪ ሀገር ተብሎ ይቆጠራል፡፡ ውጪ ሀገር ለመሄድ ሞተር መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ የእኔ ሀገር ሞተሮች ብርር ብሎ እዚያ ሀገር ያለ ከልካይ ይገባሉ፡፡
ነዋሪዎቿ ቋንቋቸው ስራ ነው፡፡ የቱም ቋንቋ ከየቱም የሚግባባት የስራ መዲና ናት፡፡ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ንግድ ነው፡፡

የሚበልጠው ነገር አብሮ መኖር፤ ሞያሌ ሰላምን በማጣት ተፈትና አይታዋለች፡፡ ያ ብጥብጥ የነዋሪዎቿ መሻት አይደለም፡፡ ያ ብጥብጥ ሞያሌና ሞያሌዎችን የማያውቅ የለኮሰው እሳት ነው፡፡ ዛሬ ያ ቀን አልፏል፡፡ ዛሬ ሌላ ቀን ነው፡፡ ሞያሌም እንደ ጥንቱ ደማቅና ሞቅ ያለች ናት፡፡ ለዘለዓለም እንዲህ ያደርግሽ፤

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top