ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ታገቱ ስለተባሉ ተማሪዎች የሰጡት ማብራሪያ ስለ መታገታቸው እንዲጠራጠሩ እንዳደረጋቸው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ /ኦፌኮ/ ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ገለጹ። ማብራሪያው የተቀላቀለ መሆኑንም የኢትዮጵያዊያን ሃገር አቀፍ ንቅናቄ /ኢሀን/ ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል አስታወቁ።
ከትናንት በስትያ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንደኛ ልዩ ስብሰባ በአካሄደበት ወቅት በደምቢዶሎ ታግተዋል የተባሉት ተማሪዎችን በተመለከተ አባላቱ ለጠየቁት ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡትን ምላሽ እንዴት አገኛችሁት ሲል የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎችን አነጋግሯል።
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ /ኦፌኮ/ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና ፤በርግጥም ተማሪዎቹ ታግተዋል ወይስ አልታገቱም የሚለውን መጠራጠር ደረጃ መድረሳቸውን ተናግረዋል። ፕሮፌሰር መረራ እንዳሉት መንግሥት ከሰጠው ምላሽ ፓርቲያቸው ልጆቹን በተመለከተ ግልፅ ያልወጡለት ነገሮች አሉ፤ በርግጥም ጉዳዩ ተፈፅሟል ወይስ አልተፈፀመም ? የሚለው ነገር የበለጠ መጣራት ያለበት ጉዳይ ነው።
ብዙ አላስፈላጊ ቀውስ እየፈጠረ ያለ ነገር በመሆኑ በትክክል ተጠልፈዋል? አልተጠለፉም? የሚለው ለወደፊቱም ቢሆን ጉዳዩ እየተጣራ ቢወጣ የተሻለ ነው፤ ተጣርቶም ማን ጠለፈ ? ለምን ያንን አደረገ ? የሚለውን ግልፅ አድርጎ መውጣት ካልቻለ አስቸጋሪ ነው። መንግሥት ስለታገቱት ተማሪዎች ያለውን ነገር ግልፅ ሊያደርግ አለመቻሉ የልጆቹን መታገት ራሱ ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል ብለዋል ፕሮፌሰር መረራ።
የኢትዮጵያዊያን ሃገር አቀፍ ንቅናቄ /ኢሀን/ ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት እንደገለጹት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታጋቾቹን በተመለከተ ያደረጉት ማብራሪያ የተቀላቀለ ነገር ነው ።
እንደ ኢንጅነር ይልቃል ማብራሪያ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሆነ ግዜ ላይ ተፈተው ሊሆን ይችላል፤ ሌላ ቦታ ሆነው ይሆናል፤ ተይዘውም ሊሆን ይችላል፤ ስለዚህ እያጣራን ነው ይሉና ትንሽ ቆይተው ደግሞ ያገቷቸው ሰዎች የሀገር ውስጥ ሰዎች ስለሚሆኑ ብለው መናገራቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማብራሪያ የተቀላቀለ ያደርገዋል።
ኢንጅነር ይልቃል እንዳሉት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መታገታቸውን ራሱ ያላመኑ የሚያስመስሉ ንግግሮችን ሲያደርጉ ነበር፤ ስለ ልጆቹ ግልፅ የሆነ ነገርም አልሰጡም። በህዝብ ውስጥ የሚብላሉ ጥያቄዎችን ለራሳቸው የህዝብ ግንኙነትና ለገጽታ ግንባታ በሚመቻቸው መልኩ መልስ ለመስጠት እንጂ ግልፅ ነገር አልተናገሩም።
የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር /ትዴት/ ሊቀመንበር ዶክተር አረጋዊ በርሄ በበኩላቸው፤ የአጋቾቹ ማንነት እንዲሁም ምንነት ባልተረጋገጠበት ሁኔታ ተቻኩሎ ለማስፈታት የሚደረጉ ሙከራዎች አደገኛ ሊሆኑ ስለሚችሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያንን ያብራሩበት መንገድ ትክክለኛና ተገቢ አካሄድ ነው።
ዶክተር አረጋዊ ከተማሪዎቹ መሀል አንድ ሰው እንኳን ጉዳት ቢደርስበት ለህዝቡ ትልቅ ህመም ነው፤ መንግሥትም ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ስራዎችን ለመስራት ማቀዱ ያስመሰግነዋል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለምክር ቤቱ አባላት፣ ‹‹አግቻለሁ ብሎ ኃላፊነቱን የወሰደ አካል የለም። እነዚህ ግለሰቦች መጀመሪያ ታግተዋል፤ ከዚያ ተፈተዋል ከተባለ በኋላ አዳዲስ መረጃዎች መምጣት ሲጀምሩ መረጃውን ለማጥራት ሙከራ ስናደርግ ተማሪ ያልሆኑ ከተማሪ ጋር ስማቸው የተገለጠ ሰዎች ያሉበት መሆኑ ተሰማ። ሆኖም ታግተውበታል ከተባለበት ስፍራ ውጪ መኖራቸውን የሚያመላክት መረጃ መኖሩ፣መከላከያው አስሶ ምንም የለም በማለቱ በመንግሥት በኩል የታገቱ የሉም የሚል ግፊቶች ነበሩ›› ብለዋል።
‹‹እስካሁን ድረስ መከላከያ በሚያደርገው ኦፕሬሽን አንድም ሰው የተጎዳም የሞተም ሰው ልናገኝ አልቻልንም። እኔ አገትኩ የሚል ሀይልም የለም። ተጎድተዋል እንዳይባል በሁሉም ቀበሌ በሁሉም ወረዳዎች ካለው ህብረተሰብ ተጎድቶ የተገኘ ሰው የለም። ችግር አልደረሰባቸውም እንዳይባል ልጆቹ ቤተሰብ ጋር ያልደረሱ አሉ›› ማለታቸው ይታወሳል።
(ምንጭ፡-አዲስ ዘመን ጥር 27 ቀን 2012)