ክቡር ጠ/ሚኒስትሬ!…በድፍረት ልምከርዎ!
(በድጋሚ የቀረበ)
የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትሬ ሆይ ለጤናዎ እንደምን ከረሙልኝ? እኔ ዕድሜ ለእርስዎና ለአስተዳደርዎ በመዓት ስጋት ውስጥ ተከብቤ እንዳለሁ አለሁ፡፡ አዎ!…ይኸቺ መከረኛ ሀገር በመዓት ችግሮች ውስጥ እየዳከረች ነው፡፡ አክራሪ ብሔርተኞች እና ተረኛ ነን ብለው የሚያስቡ ኃይሎች በአንድ በኩል፤ ተገፋን፣ ተረሳን የሚሉ ኃይሎች በሌላ በኩል ሕዝብን መከራ የሚያበሉ ሆነዋል፡፡ ክቡርነትዎ ግን ችግሩን ማስቆምዎ ቀርቶ ችግሩን በስሙ ጠርተው ሲያወግዙ አለማስተዋሌ ሌላ ስጋት እንደሆነብኝ እንደምን ልደብቅዎ?
ይኸውና ዛሬም ሰሜን ጎንደር ታምሷል፡፡ ንጹሀን እየሞቱ ነው፡፡ ምዕራብ ወለጋ የጸጥታ ችግር የዜጎችን እንቅስቃሴ ገድቧል፡፡ አዲስአበቤ ለዓመታት ቆጥቦ የሰራው የኮንደሚኒየም ቤት በጉልበተኞች ዛቻ ታግዶ ዓመት ሊደፍን ነው፡፡ ለገደንቢ ወርቅ ማዕድን ሥራ ላይ የተሰማራው የግል ኩባንያ መጀመሪያ በጉልበተኞች፣ በኋላም እነሱን በደገፈ የመንግሥት መዋቅር ከሥራ ውጪ እንዲሆን ከተደረገ አንድ አመት አልፏል፡፡ በእምነት ተቋማት ላይ ያነጣጠረው ተደጋጋሚ ጥቃት መዓት መዘዝ እየሳበ ነው፡፡ ዙሪያችን ሁሉ በስጋት ተከቧል፡፡ እርስዎ ሆኑ አስተዳደርዎ ግን ስለነዚህ አሰቃቂ ሁኔታዎች አይቶ እንዳላየ፣ ሰምቶ እንዳልሰማ ዝምታን መርጠዋል፡፡ ሕዝብ እየሞተ፣ እየተሰደደ ዝምታ፤ መልዕክቱ ምን እንደሆነ ለማንም አይገባም፡፡ ክቡርነትዎ ድፍረት አይሁንብኝና ሀገር በቀውስ መዓት በሚተራመስበት በዚህ ወቅት እንደደላው መሪ ስለበቤተመንግስት እድሳት መጠናቀቅ፣ ስለአዲስአበባ ወንዝ ልማት መጀመር ብስራት የሚነግሩበት ጊዜ ተርፍዎት ባየሁ ጊዜ ሐዘኔ በርትቶብኛል፡፡ ምንድነው እየሆነ ያለው ነገር? ማን ይንገረን? ማን አይዟችሁ ይበለን? ማን ያጽናናን? ማን ጉዳታችን ይካሰን?
ክቡርነትዎ ስለኢትዮጵያዊነት፣ ስለመደመር በየጊዜው በሚነግሩን ትንታኔ ተማርኬ ለወራት በደመነፍስ ስከተልዎትና ሳጨበጭብልዎ መቆየቴን መደበቅ አልሻም፡፡ ይህን ማድረጌ ላመንኩበት ነገር በመሆኑ አልቆጭም፡፡ ግን ሠላምና መረጋጋት በሌለበት ኢትዮጵያዊነት ለእኔ ትርጉሙ ምንድነው? መደመርስ?
ክቡርነትዎ፤ በአገራችን ላይ እየመጣ ያለው አደጋ የመቀልበስ ታሪካዊ አደራ በእጅዎ ነው፡፡ እባክዎ የደፈረሰው እንዲጠራ፣ በየቦታው የሚታየው ጢስ እንዲጠፋ ዓይንዎን ይግለጡ፡፡ ዙሪያዎን ይቃኙ፡፡ እባክዎ አደጋ ላይ ያሉ ወገኖችዎን ይታደጉዋቸው፡፡ እባክዎን ለአጥፊ ኃይላት ምንም አይነት ትግዕስትና ልምምጥ ማድረግ አቁመው አደብ ያስገዙልን፡፡ እባክዎ አክራሪ ብሔርተኞች እና ባለተራ ነን ባይ ፖለቲከኞችን የመቆንጠጥ አቅም ይኑርዎት፡፡
የየትኛውም ሀገር መንግሥት የሠላምና የጸጥታ መደፍረስ ጉዳይ የሚበልጥ ምንም አይነት ቀዳሚ አጀንዳ የለውም፡፡ ማንም መንግሥት የህዝብ ጥቃትን፣ የመሰረተ ልማት ውድመትን አሜን ብሎ አይቀበልም፡፡ ማንም መንግሥት የህዝብ ገንዘብ የዘረፉ ኃይላትን አያስታምም፡፡ የትኛውም መንግሥት የተነሳ እሳት ዳር ቆሞ አይሞቅም፡፡ ወይንም እሳቱ በራሱ ይጠፋል ብሎ ለዕድል ሀገሩን አሳልፎ አይሰጥም፡፡ እናም ሕግና ስርዓት የማስከበር ጉዳይ ከመኖርና ካለመኖር ሕልውና ጋር በቀጥታ የተሳሰረ ነው፡፡
እባክዎ አሁንም ኳሷ በእግርዎ ስር ነች፡፡ በአግባቡ ተጫውተው ያሸንፉባት፡፡ ሀገርዎንና ሕዝብዎን መታደግ ቀዳሚ ሥራዎ ይሁን፡፡
ጥቂት ጊዜ ሰውተው መልዕክቴን ስላነበቡ አመሰግንዎታለሁ፤ መልካሙን ሁሉ እመኝልዎታለሁ፡፡
አክባሪዎ፡- ጫሊ በላይነህ