Connect with us

ከምር የህወሓት የአፈና ዘመን ናፈቀኝ!

ከምር የህወሓት የአፈና ዘመን ናፈቀኝ!
Photo: Facebook

ፓለቲካ

ከምር የህወሓት የአፈና ዘመን ናፈቀኝ!

ከምር የህወሓት የአፈና ዘመን ናፈቀኝ!
(ጫሊ በላይነህ)

ሞኝ ነኝ። “የሰው የለው ሞኝ” ያለው አቀንቃኝ ለመሳሳቱ ምስክሩ እኔ ነኝ። ለውጥ መጣ ሲሉኝ መንጋውን ተከትዬ አጨብጭቤ ነበር። ሽብርተኞቹ እኛ ነበርን ሲባል መሪዬን አምኜው ነበር። በማዕከላዊ ተዘጋ አጀንዳ ጉሮ ወሸባዬ ሲደለቅ ከበሮ ያዥ ነበርኩኝ።

ስለኢትዮጵያዊነት ከፍታ ሲነገር በእምባ እየታጠቡ ካነቡ ወገኖቼ አንዱ ሆኜ ታይቻለሁ። ስለመደመር ሲሰበክ ግራና ቀኝ ማየት ተስኖኝ እነዶክተር ዐብይን አትንኩ ባይ ነበርኩኝ። ዛሬ ከ22 ወራት የለውጡ ዕድሜ በኋላ ሁሉም ነገር ቃል ብቻ መሆኑ ገባኝ። ቃል ሥጋ መሆን ሲያቅተው ማየቴ በራሴ እንዳፍር አደረገኝ።

ልብ በል!… እነጠ/ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ወደሥልጣን መሣብ ከንቱ ነበር እያልኩኝ አይደለም። ለውጡ ብዙ ያስገኘው መልካም ፍሬ መኖሩን አልክድም። የኘረስ ነፃነቱ ነገር ዛሬም ጥያቄ የሚነሳበት ቢሆንም ቅሉ የታሰሩ ጋዜጠኞች እንዲፈቱ፣ የታፈኑ መገናኛ ብዙሀን ነፃ እንዲወጡ የአንበሳውን ድርሻ ተወጥቷል።

በቂም በቀል ጭምር የታሰሩ ፖለቲከኞች የነፃነት አየር እንዲተነፍሱ፣በአሸባሪነት የተፈረጁ ድርጅቶች በታላቅ ክብር ወደአገር እንዲገቡ የዶክተር ዐብይ አመራር የማይተካ ሚና ነበረው።

ግን ምንዋጋ አለው?!.. ዜጎች በህገወጦች ሲፈናቀሉ፣ በአደባባይ ሲገደሉ፣ ሲዋረዱ፣ ሲታፈኑ…ሕግና ሥርአትን የማስከበር አቅም አንሶት ለማየት በቃን።ዛሬ ኢትዮጵያውያን በውጭ አገር ተከብረው እየኖሩ፣ በገዛ አገራቸው ግን በነፃነት ተዘዋውሮ መስራት፣ ሐብት ማፍራት፣ መኖር እንዲሁም የመረጡትን ሀይማኖት ማራመድ፣ ሀይማኖታዊ ክብረበአላቸውን በሠላም ማከናወን… የማይችሉበት ጊዜ ላይ ደረሱ።

ይህ ሁሉ ሲሆን የጠ/ሚ ዐብይ አስተዳደር የትግዕስት ጠቀሜታ ሰባኪ ከመሆን በዘለለ የወገኖቻችንን እምባ ማበስ አልቻለም። ዘረኞችና ህገወጦች ግለሰቦችና ቡድኖች ከክልል ክልል፣ ከከተማ ከተማ ስፖንሰር እየተደረጉ የአገር ሀብት ሲያወድሙ፣ የዜጎችን ህይወት ሲቀጥፉ የጠቅላያችን አስተዳደር ህግና ስርአትን ስለማስከበር ሌክቸር ከመሰጠት የዘለለ የሚታይ የሚዳሰስ ስራ ማከናወን አልቻለም።

ይገርመሀል!…ለውጡ ገና ለጋ ነው በሚል ነገሮች ከዛሬ ነገ ይስተካከላሉ በሚል አፌን ዘግቼ ብዙ ታግሼ ነበር። ግን ነገሮች ከቀን ወደቀን ከመርገብ ይልቅ እየተባባሱና እየተወሳሰቡ መምጣት እንዳስደነገጠኝ መካድ ራስን መዋሸት ይሆናል። ሌላው ቀርቶ በአገሪቱ ምን እየሆነ እንዳለ፣ ከዚህ ሁሉ ግጭትና ደም መፋሰስ ጀርባና ፊት ማን ተሰልፎ እንዳለ ሚስጢር ተደርጎ መያዙ ምቾትን አልሰጠኝም።

እናም ወገኔ፤ ያመንኩት፣ ዓይኔን ጨፍኜ የተከተልኩት ጠቅላይ ሚኒስትሬ ህግና ስርአትን ማስከበር ሲሳነው መገንዘቤ ውስጤን እያቃጠለው ነው። ጥቂት የፖለቲካ ነጋዴዎች በግጭት ትርፍ ሲያጋብሱ እያየ፣ እየሰማ ዝምታን መምረጡ ቆም ብዬ ራሴን እንዳይ ገፋፍቶኛል።

እውነት ለመናገር ሩቅ ሳንሄድ ከአዲስአበባ – አዳማ ደርሶ ለመመለስ እንኳን ደህንነት እየተሰማኝ አይደለም። በተለይ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በሐረሪ…ክልሎች የሚታየው የፀጥታ ችግር እንደአገር ከፍተኛ አደጋን የደቀነ መሆኑን በግሌ ተረድቻለሁ።

እውነት እውነት እላችሀሃለሁ!… በአሁን ሰዓት በግፍ ተግባሩ የሚወገዘውን ህወሓት መራሽ መንግስት ማረኝ የምልበት ደረጃ ላይ መድረሴን ስናገር እያዘንኩኝ ነው። ህወሓቶች በአፈና አገዛዝም ቢሆን ወደ 27 አመታት ለሚጠጋ ጊዜ በመላ አገሪቱ ኮሽታ ሳይሰማ፣ ሰጥ ለጥ አድርገው መግዛታቸውን የማደንቅበት የንፅፅር ጊዜ ላይ ተገኝቻለሁ።ቢያንስ በዘመነ ህወሓት በሠላም ወጥቶ የመግባት ዋስትና ማግኘቴ ቀላል ግምት የምሰጠው አይደለም።

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top