የኢፌዲሪ ጉምሩክ ኮሚሽን ከስፖትላይት ማርኬቲንግና ኮሚዩኒኬሽንስ ጋር በመተባበር በህገወጥ ንግድ አፈጻጸም አደጋዎችና የመከላከያ መንገዶች ዙሪያ ከሚመለከታቸው የመንግስት መስሪያ ቤቶችና የባለድርሻ አካላት ጋር በሐረሪ ክልላዊ መንግስት በሐረር ከተማ ውይይት አካሄደ፡፡
በ ወንደርላንድ ሆቴል ሰሞኑን በተካሄደው ውይይት የኢፌዲሪ ጉምሩክ ኮሚሽንን ጨምሮ የሐረርና የድሬዳዋ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች፣ የንግድና ኢንደስትሪ ቢሮ፣ የጤና ቢሮ፣ የገቢዎች ቢሮ፣ የፖሊስና የመከላከያ ጨምሮ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት ባለስልጣናት ተወካዮችና የንግዱ ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
የሐረር ከተማ ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጀማል አህመድ ስብሰባውን ባስጀመሩበት ወቅት ሲገልጹ “ኮንትሮባንድ ለሃገራችን ዕድገትና ልማት ፀር ከመሆኑም በላይ በየዕለቱ ጥራታቸውን ባልጠበቁና ጊዜያቸው ባለፈባቸው ምርቶች ህጻናትና እናቶች፣ ሁላችንም ሰለባ እየሆንን ነው”በማለት ኮንትሮባንድ እያደረሰ ያለውን መጠነ ሰፊ ጉዳት አብራርተዋል፡፡ አክለው ሲናገሩም “ይህ ችግር ለመንግስት ብቻ የሚተው ሳይሆን ሁላችንንም የሚመለከት ነው፡፡ ሁላችንም የአደጋውን ጥልቀትና ስፋት ተመለክተን የድርሻችንን ልናደርግ ይገባል፤ ዛሬ ይህን ሥራ ከሐረር ከተማ ጀምረን እናወያይ ብላችሁ መርጣችሁን ስለመጣችሁ በጣም ደስ ብሎናል” ብለዋል፡፡
የኢፌዴሪ ጉምሩክ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሙሉጌታ በየነ በበኩላቸው ኮንትሮባንድ ከዕለት ወደዕለት እያደገና አፈጻጻሙም እየረቀቀ የሚገኝ የእድገት ፀር ህገወጥ ድርጊት መሆኑን የገለጹ ሲሆን አክለውም ይህንን ችግር ለመከላከል መንግስት ከምንግዜውም በላይ ቁርጠኛ ሆኖ እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡ ምክትል ኮሚሽነሩ በመንግስት በኩል ስላለው ቁርጠኝነት ሲያብራሩም “ይህንን የህገወጥ ንግድ ለመዋጋት ትልቅ ቦታ ሰጥተን እየሰራን ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ከእለት ተእለት የጉምሩክ ኮሚሽኑ የህገወጥ ንግድ ክትትልና ቁጥጥር በተጨማሪ በምክትል ጠቅላይሚኒስትሩ የሚመራ ብሔራዊ ታስክ ፎርስ ተቋቁሞ እየተሰራ ይገኛል” ብለዋል፡፡ ምክትል ኮሚሽነር ሙሉጌታ በተጨማሪም ኮንትሮባንድን ለመግታት በሚደረገው ጥረት የሁሉም አካላት ሚና ከፍተኛና አስፈላጊ መሆኑን ሲያሰምሩ “በሁሉም የችግሩ ዘርፎች ላይ ሁላችንም ርብርብ የምናደርግ ከሆነ ህገወጥ ንግድን በእጅጉ መቀነስ እንችላለን” በማለት ገልጸዋል።
ምክትል ኮሚሽነሩ አክለውም “ህገወጦችን በማጋለጥ፣ ለህግ አሳልፎ በመስጠት፣ ህገወጥ ምርቶችን ባለመግዛት፣ የፍትህ አስፈጻሚ አካላትም እርምጃ በመውሰድ ብንረባረብ ቤተሰቦቻችንን፣ እህት ወንድሞቻችንን ከተበላሹ፣ ግብአታቸው ከማይታወቅ፣ ጥራታቸው ካልተረጋገጠና ከፎርጂድ የታሸገ ምግብ፣ መድኃኒት፣ ቅባት፣ ኮስሜቲክስና ህገወጥ የሲጋራ ምርቶች መጠበቅ እንችላለን” ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በኮንትሮባንድ በከፍተኛ ደረጃ ወደ ሀገር ውስጥ ከሚገቡ ምርቶች አንዱ የሆነው የትምባሆ ምርት ሲሆን በኢትዮጲያ የማምረትና የማከፋፈል ብቸኛ መብት ያለው ብሄራዊ የትምባሆ ድርጅት አ.ማ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በድርጅቱ የፀረ ህገወጥ ትምባሆ ክፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ ሰለሞን ሀይሌ ስለጉዳዩ ሲናገሩ “40 በመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ ትምባሆ ንግድ በተለይም ደግሞ በዚህ በምስራቅ ኢትዮጲያ 90 በመቶ የሚሆነው የትምባሆ ንግድ በኮንትሮባንድ በሚገቡ የሲጋራ ምርቶች የተያዘ ነው። በዚህም ምክንያት ህግን በማክበር የሚንቀሳቀሰውን በውጪ ኢንቨስተሮች ከሁለት
አመት በፊት በአንድ ቢሊዮን ዶላር ፕራቬታዝ የተደረገውን ድርጅት ኢንቨስትመንትና ገቢ ብሎም መንግስት ከዘርፉ በህጋዊ መልኩ መሰብሰብ የነበረበትን ግብር የሚቀንስና የሚያዳክም ነው” ብለዋል።
የባለድርሻ አካላት ውይይቱ በጉምሩክ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሙሉጌታ በየነ እንዲሁም በሓረር ከተማ የጠቅላይ አቃቢ ህግ ቢሮ ምክትል ሓላፊ በሆኑት አቶ በክሪ አብያላ በቀረቡ የመነሻ ሃሳቦች ላይ ከሁሉም የባለድርሻ አካላት በተነሱ የመፍትሄ ሃሳቦች ዙሪያ ከመከረ በኋላ የባለ ስድስት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል፡፡