Connect with us

ያልተገኘችውን የጎንደርን እህት ሲግቱናን በሲውዲን አገኘኋት

ያልተገኘችውን የጎንደርን እህት ሲግቱናን በሲውዲን አገኘኋት

ባህልና ታሪክ

ያልተገኘችውን የጎንደርን እህት ሲግቱናን በሲውዲን አገኘኋት

ያልተገኘችውን የጎንደርን እህት ሲግቱናን በሲውዲን አገኘኋት
እዚህ ኾኜ ያን ያስናፈቀችኝ የከተማ ሸጋ

ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም በአውሮፓ የተለያዩ ከተሞች ቆይታ እያደረገ ነው። በሲውዲን ከሚገኙ ቀደምት ከተሞች ቀዳሚዋን ጎንደርን መስላ አገኘኋት ሲል ሲግቱናን ከጎንደር እያዛመደ እህትነታቸውን በተመኘበት ዘገባው ምልከታውን እንዲህ ያካፍለናል፡፡)
ከሄኖክ ስዩም በድሬ ቲዩብ

ከፍራንክፈርት ኪነ ሕንፃ ውበት ምሳጤ አልወጣሁም። የከተማ ውበት ከፀሐይ መሽኮርመም በልጦ በሰው ልጆች መላ ሀገር ፈክቷል። ውሃ ዳርቻ ነኝ። በመብራት ያሸበረቀችው ከተማ እናትም ሙሽራም ናት።

” አረጀች እያሉ ሰዎቹ ቢያሙሽ ሙሽራ ነሽ ጎንደር ይሰፋ ልብስሽ” ሲባል ለእኔም ያለች ይመስለኛል። በጨለማ ነው የደረስኩት። መሽቶብኝ አይደለም። የመጣሁት ቀን ነበር እግዜር የሰማይን ብረሃን ሸሸገ። ሳይመሽ በሚጨልምበት ሀገር ታሪኳ ሲንቦገቦግ በሚኖር ጥንታዊ ከተማ ተገኝቻለሁ።

ንጉሥ ኤሪክ ነው የመሰረታት ከሺህ አመታት በፊት። ወቅቱ 970 በእነሱ ዘመን። ልጄ እሷ ዛሬም ሙሽራ ናት ዓይኗን የምትኳል። ቅንድቧን ተቀንድባ በውሃ ዳርቻዋ ሽር ብትን የምትል። ጉንጮቿ ብርቱካን የመሰሉ። ስለ ሲውዲን ሴት አይደለም የማወራው የሲውዲን የቀድሞ መናገሻ ስለነበረችው ሲግቱና እንጂ።

ጎዳናዎቿ ልቤን ገዙት። አርምሞ ላይ ያለች ብትመስልም ታሪኳና ውበቷ ይጮሃል። እዚህ ኾኜ ጎንደርን አሰብኳት የጠፋችባት እህቷ መሰለቺኝ። እህትማማችነታቸውን ተመኘሁ። ሀገሩ ለየቅል ይሁን እንጂ እንደ ሲግቱና ጎንደርም የሀገር መናገሻ ነበረች። እንደ ቫይኪንጎቹ የጎንደር ነገሥታትም ህይወትና ውበት ያስተረፉ ባለፀጋዎች ናቸው። እንደ ኤሪክ በፋሲል ስም የምትምል ከተማም ናት።

ቤቶቿ ጥንታዊ ናቸው። ዛሬም ጀግና ትውልድ ስለተረከባቸው እንኮዬ መስክን የሚመስል ታሪክ ቢኖራቸውም በውበት በፅዳትና በዝማኔ ሰማይ ቧጥጠዋል። ያም ሆኖ ጎዳናዋ ላይ ቆሜ ቆብ አስጥል የምጓዝ እስኪመስለኝ አንድም ሁለትም እያልኩ ከተማ አዛምዳለሁ።

መቶ ዘጠኝ አመት በኾነውን ሆቴሏ ደጃፍ ላይ ቆሜ ልቤን ሀገሬ ሰደድኩት ሙርፊ የምትባል የኔ ቢጤ ቀዝቃዣ የዛሬ ሰማኒያ አመት ገደማ ጎንደር መጥታ ያየችው ውቡ እቴጌ ሆቴል አለመኖሩን አሰብኩ። አንገቴን ደፋሁ የጎዳናዋ ምንጣፍ መልሶ ጎንደር አደረሰኝ።

መሃል ጎዳናዋ የተቀጠረው አደባባይ ፋሲል እግንቡ ስር ያለውን መስቀል አደባባይ መስሎኛል። አሁን ደግሞ አጣጣሚ ሚካኤል አጠገብ የተሰራው የህዝብ ማረፊያ ይበልጥ አዛምዶብኛል።

ሲግቱና ነኝ። የቅዱስ ጴጥሮስ ቤተክርስቲያን ሞገሷ ነው። ጠባብ ጎዳናዎቿ ሰፊ ታሪክ ያስጋልባሉ። ጥንታዊ ቤቶቿ ዘመናዊውን የዓለም ትውልድ ያንበረክኩታል። መስታወት መቀጠል ብቻውን መሰልጠን እንዳልኾነ ዓለምን ታስተምራለች። መጀመሪያ ደኑን መጠበቅና ማልማት እንዲህ ያለ ውብ የእንጨት ቤት ከተማ ለማኖር ይረዳል። የነዋሪዋ ብዛት ትንሽ ነው። ረዥሙን ሰዓት በሚጨልምበት ወቅት በመምጣቴ የብርሃን ፎቶ ማንሳት አልቻልኩም። የለጠፍኩላችሁ ጎግል አግዞኝ ነው። የምሽቱን ድባብ ደግሞ ከእኔ ምስሎች ተጋሩዋቸው። ስመለስ ስለ ብዙ ነገሯ ብዙ አወራችኋለሁ።

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top