“ለውጡ በከፍተኛ ፍጥነት ወደክሽፈት እያመራ ይገኛል”
አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት!!!
የመግባቢያ ሠነድ
በአገራችን በኢትዮጵያ ቢያንስ ላለፉት 50 ዓመታት የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአገዛዝ ወደ መዋቅራዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመሸጋገር በተደረገ ትግል ከፍተኛ መስዋትነት ሲከፍል ቆይቷል፡፡ ይሁንና በአንድ በኩል በአገራችን ተንሰራፍቶ በቆየውና የፖለቲካ ቅራኔዎቻችንን በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመፍታት ባላስቻለን ኋላቀር የፖለቲካ ባህላችን ምክኒያት፣ በሌላ በኩል ደግሞ በአገራችን የፖለቲካ ልሂቃን ባለው ከፍተኛ የአመራር ድክመት ምክኒያት የህዝባችን የለውጥ ፍላጎትና ትግል ስኬታማ ሳይሆን ቀርቷል፡፡
ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣት ጋር ተያይዞ የዛሬ 18 ወር በአገራችን የተከሰተው የለውጥ ሂደት በህዝባችን ውስጥ ከፍተኛ ተስፋ ፈጥሮ የነበረ ቢሆንም እንደአለመታደል ሆኖ ይህም የለውጥ ሂደት ወደ ስምረት ሳይሆን በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ክሽፈት እያመራ ይገኛል፡፡ ኢህአዴግ የለውጥ ሂደቱን ሁሉን አቀፍ በሆነ የጋራ የሽግግር ተቋምና ከእንዲህ ዓይነቱ ተቋም የውይይትና የድርድር ሂደት በመነጨ ፍኖተ-ካርታ እንዲመራ ማድረግ ሲገባው፣ በተለምዶ አምባገነናዊ ባህሪው “እኔ አሻግራችኋለው” በሚል መታበይ በራሱ ፍላጎትና መንገድ ብቻ ሊመራው በመሞከሩ የለውጥ ሂደቱ የመክሸፍ አደጋ ገጥሞታል፡፡
አገራችን ለገጠማት የፖለቲካ ቀውስ መነሻ ምክንያት ለሆኑ መዋቅራዊ ችግሮቻችን ትርጉም ያለው መዋቅራዊ መፍትሄ ለመስጠት ሙከራ ባልተደረገበት፣ በተካረረ የፅንፍ አመለካከት ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ሃይሎች ብሄራዊ እርቅ ሳያካሂዱና በብዙ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሄራዊ መግባባት ባልተፈጠረበት ሁኔታ በጥድፊያ ወደ አገራዊ ምርጫ ለመግባት እየተደረገ ያለው ሙከራ የተጀመረው የለውጥ ሂደት ተስፋ አስቆራጭ በሆነ መጠን የመክሸፍ አደጋ ውስጥ መግባቱን የሚያሳይ ነው፡፡
የተጀመረው የለውጥ ሂደት አግባብ ባለው መንገድ ባለመመራቱ ምክንያት አገራችን በአሁኑ ወቅት ህልውናዋን የሚፈታተን አደጋ ውስጥ ትገኛለች፡፡ ዛሬ በአገራችን በታሪካችን አይተነው በማናውቀው መጠን ብሄር ተኮር የሆነ የህዝብ ለህዝብ የእርስ በርስ ግጭት እየተከሰተ በብዙ ሺ ለሚቆጠሩ ዜጎቻችን መሞትና በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ዜጎቻችን መፈናቀልና ስደት ምክንያት ሆኗል፡፡ አሁንም በታሪካችን አይተነው በማናውቀው ሁኔታ ለበርካታ አብያተ ክርስቲያኖችና መስጂዶች መቃጠል ምክንያት የሆነ እና ፖለቲካዊ አጀንዳ ያዘሉ ግጭቶች በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች እየተከሰቱ ነው፡፡ የአገራችን የጸጥታ መዋቅሮች በአግባቡ ሃላፊነታቸውን መወጣት ባለመቻላቸው በአብዛኛው የአገሪቱ አካባቢዎች ህግና ስርዓትን ማስፈን ያልተቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በዚህም ምክንያት ዜጎች ከፍተኛ የህይወት ስጋት ውስጥ የገቡበትና በዕለት-ተዕለት ስራቸውና የወደፊት ህልውናቸውን በሚወስን የልማት ስራ ላይ ማተኮር የማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ ገብተዋል፡፡ በአጠቃላይም የለውጥ ሂደቱን በአግባቡ መርቶ ለስኬት እንዲያበቃ አደራ የተሰጠው ገዥው ፓርቲ በተለመደ ባህሉ የእርስ-በርስ የስልጣን ሽኩቻ ውስጥ በመግባቱ ምክንያት አገሪቱ ወዴት እንደምታመራ አቅጣጫ ያጣችበት እና በማንኛውም ከፊታችን ባለ አንድ አጋጣሚና ቅፅበት ወደ የእርስ-በርስ ጦርነት ወይም መንግስት የለሽነት አደጋ ልትገባ የምትችልበት ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች፡፡
ይህ የአገራችን የህልውና አደጋ በእጅጉ ያሳሰበንና አገራችንን ከዚህ የህልውና አደጋ መታደግ የአገሪቱ የፖለቲካ ሃይሎች ቀዳሚ ወቅታዊ ትኩረት መሆን ይገባዋል ብለን ያመን ሶስት አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይህንን የመግባቢያ ሰነድ በመፈረም የሚከተሉትን ተግባራት በጋራና በትብብር ለመስራት ወስነናል፡፡
በተለያዩ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ዙሪያ በመካከላችን ያሉና የሚኖሩ ልዩነቶች እንደተጠበቁ ሆነው የአገራችንን ህልውና መቀጠል በተመለከተ ግን አንድ የጋራ ኮሚቴ አቋቁመን በትብብር ለመስራት ተስማምተናል፡፡ ኮሚቴው ከአገራዊ ህልውና ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በተመለከተ የጋራ ምክክር በማድረግ የጋራ መግለጫዎች ያወጣል፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ህዝባዊ ስብሰባዎችንና ሰላማዊ ሰልፎችን በጋራ ያካሂዳል፡፡
የአገር ህልውናን በተመለከተ ተመሳሳይ አቋም ካላቸው ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ቀጣይ ግንኙነት በመፍጠር ይህንን በኛ የተጀመረ ግንኙነት በሂደት የበለጠ ለማስፋትና ለማጠናከር ተስማምተናል፡፡ ይህም ስምምነት በአሁኑ ወቅት እራሳቸውን በማሰባሰብ ለማጠናከር እየሞከሩ የሚገኙ የኮንፌዴሬሽን ኃይሎች በአገሪቱ ህልውና ላይ ሊፈጥሩ የሚችሉትን አደጋ ለመቋቋም የሚያስችል አንድ ጠንካራና እውነተኛ የፌደራሊስቶች ጎራ በአገሪቱ መፍጠርን ዓላማው ያደረገ ነው፡፡
ወደፊት በአገራችን በሚካሄደው አገራዊ ምርጫ (መቼም ይካሄድ መቼ) በአንድ የምርጫ ማንፌስቶ በጋራ ለመወዳደርና ምርጫውን ለማሸነፍ የሚያስችለንን ውይይትና ድርድር ከወዲሁ ለመጀመርና፣ ከምርጫው በኋላ የጥምር መንግስት ለማቋቋም የሚያስገድድ ሁኔታ ቢፈጠር ድርድርና ስምምነት ከምርጫው በፊት ለማካሄድ ተስማምተናል፡፡
ይህንን ውስን ለሆነ ነገር ግን ለታላቅ አገራዊ ዓላማ የጀመርነውን ትብብርም “አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት “(አብሮነት) ብለን ለመጥራት ተስማምተናል፡፡
በመጨረሻም አገራዊ ህልውናን በተመለከተ ከእኛ ጋር ተመሳሳይ አመለካከት ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመሳሳይ የመግባቢያ ሰነድ በመፈረም አብረውን እንዲሰሩ ጥሪያችንን እያቀረብን፣ ይህ ጥረታችን እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የአገር ህልውናን ከጥፋት ለመታደግ የሚደረግ መሆኑን በመገንዘብም አገር ወዳድ የሆነ ማንኛውም ዜጋ ሁሉ ሁለንተናዊ ትብብር በማድረግ ከጎናችን እንዲቆም ጥሪያችንን በዚህ አጋጣሚ እናቀርባለን፡፡
-ህብር ኢትዮጵያ
-ኢዴፓ
-ኢሀን