“ጥንታዊው የሀሙራቢ ሕግ”
ከ ኪዳኔ መካሻ
—
“አይን ያወጣ አይኑን፣ ጥርስ ያወለቀ ጥርሱን’’
ከዛሬ 3800 ዓመታት በፊት በጥንቷ ባቢሎን (በአሁኗ ኢራቅ) ነግሶ የነበረዉ ንጉስ ሀሙራቢ ለ 46 ዓመታት የጥንቱን የሚሶፓታሚያ ግዛት ( ማለትም ከጤግሪስና ከኤፍራጥስ ወንዝ እስከ ሜዲቲራንያን ባህር ጠረፍ ) ድረስ ያስተዳድር ነበር። ይህ ንጉስ ‘የአለማችን ጥንታዊው ሕግ’ ተብሎ የሚጠራውን ሕግ የአንድ ጎልማሳ ቁመት ባላቸው ሀውልቶች ላይ አስቀርፆ በከተማ አቁሞ ነበር። 282 ህጎችን በተለያዩ የወንጀል ፣ የውል፣ የጋብቻ፣ የውርስ ጉዳዮች ላይ ያካተተው የሀሙራቢ እድሜ ጠገብ ሕግ ከምእተ አመታት በላይ በጥንታዊ የአለማችን ህግጋት ላይ የራሱን ተፅህኖዎች ሲያሳርፍ ኖሯል፡፡ አስቲ የዚህን ጥንታዊ ህግ አስገራሚ ነገሮችን እናንሳ
• የበቀልና የአሰቃቂ ቅጣቶች ህግ ፡- ጥፋተኛው ያደረሰውን ጥፋት ይቅመሰው ‘ሌላው ላይ እንዳደረክ አንተም ላይ ይደረግ’ በሚል የአቻ ምላሽ እሳቤ በሚመሩ ቅጣቶቹ የሀሙራቢ ሕግ ይታወቃል። አይን ያጠፋ አይኑ ይጥፋ፣ ጥርስ ያወለቀ ጥርሱ ይውለቅ፣ እግር የሰበረ እግሩ ይሰበራል ፡፡ እነዚህ አይነት ቅጣቶች ብቻ ሳይሆኑ ከጥፋቱ ጋር የማይመጣጠኑ አሰቃቂ ቅጣቶችም ነበሩበት። ለምሳሌ አባቱን የተማታ ልጅን የሀሙራቢ ህግ እጁ እንዲቆረጥ ያዛል፡፡’’
• አድሎአዊነቱ፡- የሀሙራቢ አሰቃቂ ቅጣቶች እንደ አጥፊውና እንደ ተበዳዩ ማንነት ይለያያሉ፡፡ ለምሳሌ በማህበራዊ ደረጃ እኩያው የሆነን ሰው ጥርስ ያወለቀ ሰው ጥርሱ ሲወልቅ ይህንኑ ድርጊት በወቅቱ ዝቅተኛ ደረጃ በነበራቸው ሰዎች ላይ የፈፀመ ሰው በገንዘብ ይቀጣ ነበር። ሌላ ምሳሌ ነፍሰጡር የሴት ባሪያውን የገደለ ሰው በገንዘብ ሲቀጣ ነፃ የሆነች ነፍሰጡር ሴትን የገደለ ሰው ደግሞ ለብቀላ ሴት ልጁን ትገደልበት ነበር፡፡ የፆታ አድሎም ነበረበት ያገባ ወንድ ከሴት ገረዶቹና ባሪያዎቹ ጋር መወስለት ይችላል። ያገባች ሴት ግን በትዳሯ ላይ ዘሙታ ከተገኘች ከነ ውሽማዋ በኤፍራጠስ ወንዝ ውስጥ ትጣል ነበር።
• ስራህ ያድንህ ቅጣት፡- በተጨባጭ ማስረጃ ሊረጋገጡ ያልቻሉ እንደ ጥንቆላ ያሉ ጥፋቶች ሲፈፀሙ ህጉ ተጠርጣሪውን የእውነትና የፍትህ አምላክ እንዲዳኘው ይፈቅዳል፡፡ ተከሳሹ ንፁህ መሆኑን ለማረጋገጥ ለሞት በሚያደርስ ሁኔታ ውስጥ እንዲገባ ይደረጋል በህይወት ከተረፈ ንፅህናው እንዳዳነው ይቆጠርለታል፡፡ ተከሳሹ ወደ ወንዝ ዘሎ እንዲገባ ተደርጎ ከሰመጠ ጥፋቱን እንደፈፀመ ተቀጥሮ ከሳሽ ንብረቱን ይወስዳል። የእውነት አማልክቱ ተከሳሹን ምንም ሳይጎዳ ካተረፉት ግን ንፁህነቱት ሰለተረጋገጠበሀሰት የወነጀለው ከሳሹ ይገደላል፡፡ ወደ ወንዝ ዘሎ ገብቶ በመትረፍ ንፁህነቱን ያረጋገጠው ተከሳሹ ደግሞ የከሳሹን ቤት ንብረት ይወርሳል፡፡
• በሕግ የተወሰነ ዝቅተኛ ደሞዝ፡- የሀሙራቢ ህግ ከጊዜው የቀደሙ አስደናቂ የህግ እሳቤዎችንም አካቷል ለምሳሌ ለተወሰኑ ስራዎች የሚከፈለውን ዝቅተኛ ደምዎዝ አስቀምጧል።የቀን ሰራተኛ፣ ከብት ጠባቂዎች፣ በሬ ነጂዎች አመታዊ ዝቅተኛ ደሞወዛቸው በህግ ተደንግጓል። ሀኪሞችም ደሞወዛቸው በህግ የተደነገገ ሲሆን ለነፃ ሰው፣ ከባርነት ነፃ ለወጣ ታካሚና ለባሪያ ግን ክፍያው የተለያየ ነበር።
• የንፁህነት ግምት፡- በጭካኔ ቅጣቶች የሚወሳው የሀሙራቢ ህግ ዘመን ተሻጋሪ ዋጋ ያላቸው ህጎችንም አካቷል። ህገ መንግስታዊው ’’ ማንም ሰው ጥፋቱ በፍርድ እስካልተረጋገጠበት ንፁህ እንደ ሆነ ይገመታል’’ የሚለው ዘመናዊ የህግ እሳቤ ያኔም ነበር፡፡ በርግጥ የአንድን ሰው ጥፋት የማረጋገጡ ሸክም በከሳሽ ላይ የተጣለ ሲሆን አንድ ከሳሽ በሞት የሚያስቀጣ ክስ አቅርቦበት ተከሳሹ ወንጀሉን መፈፀሙን ማረጋገጥ ካልቻለ እራሱ ከሳሹ በሞት ይቀጣ ሲል ሀሙራቢ በሕጉ ደንግጎ ነበር፡፡ በዳይና ተበዳይም ፍትህን ለማግኘት ከዳኛ ፊት ቀርበው ክሳቸውን ማሰማት ማስረጃና ምስክር አቅርበው ፍትህን የማግኘት መብታቸውንም ጥንታዊው ሀሙራቢ ከሁሉ ቀድሞ እወቅና ሰጥቶት ነበር።
በ1901 በ ፈረንሳዊው አርኪዮሎጂስት ከመገኘቱ በፊት ከ3000 አመታት በላይ በታሪክ ገፅ ተዘንግቶ የነበረው የሀሙራቢን ህግ በጥንታዊነቱ ተጠቃሽ ቢሆንም በመካከለኛው ምስራቅ የነበሩት የሱማሬያንና የሊፒት ኢሽታር ህጎች ከሀሙራቢ ቢያንስ በሁለት ክፍለ ዘመናት የቀደሙ እንደነበሩ በታሪክ ተመራማሪዎች ተረጋግጧል፡፡
ጥንታዊው የሀሙራቢን ህግ በአሰቃቂ ቅጣቶቹና ለዘመናዊ የህግ እሳቤዎች ባበረከተው አስተዋፅኦ በህግና በታሪክ ፀሀፍት እየተጠቀሰ እኛ ዘመን ደርሷል፡፡
#Ethiopia_ድሬቲዩብ_ሕጋችን