Connect with us

የጋራ መኖርያ ቤቶችን ጉዳይ እንዲፈታ የተቋቋመው ኮሚቴ ኃላፊነቱን መወጣት አልቻለም

የአዲስ አበባና የኦሮምያን የአስተዳደር ወሰን ውዝግብና የጋራ መኖርያ ቤቶችን ጉዳይ እንዲፈታ የተቋቋመው ኮሚቴ ኃላፊነቱን መወጣት አልቻለም
Photo: Facebook

ህግና ስርዓት

የጋራ መኖርያ ቤቶችን ጉዳይ እንዲፈታ የተቋቋመው ኮሚቴ ኃላፊነቱን መወጣት አልቻለም

የአዲስ አበባና የኦሮምያን የአስተዳደር ወሰን ውዝግብና የጋራ መኖርያ ቤቶችን ጉዳይ እንዲፈታ የተቋቋመው ኮሚቴ ኃላፊነቱን መወጣት አልቻለም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የኦሮምያ ክልልን የአስተዳደር ወሰን ውዝግብን በመፍታት እጣ ወጥቶባቸው እንዳይተላለፉ የተደረጉ የጋራ መኖርያ ቤቶችን ጉዳይ እንዲፈታ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተቋቋመው ኮሚቴ ሀላፊነቱን መወጣት ተስኖት በቂ ስብሰባ እንኳ ማድረግ አለመቻሉን ዋዜማ ራዲዮ ሰምታለች።

ባለፈው አመት የካቲት 27 ቀን 2011 አ.ም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ51 ሺህ 229 የጋራ መኖርያ ቤቶችን እጣ ማውጣቱ ይታወሳል። ከዚህ ውስጥ 18 ሺህ 576ቱ የ40/60 የጋራ መኖርያ ቤቶች ሲሆኑ : ቀሪዎቹ 32 ሺህ 653ቱ ደግሞ የ20/80 የጋራ መኖርያ ቤቶች ናቸው። የ40/60 የጋራ መኖርያ ቤቶቹ ከፍተኛ የማጠናቀቅ ችግር ቢኖርባቸውም የቤቶቹ እድለኞች የስልሳ በመቶውን ብድር ውል ፈርመው ወደ ክፍያ ገብተዋል ; ምንም እንኳ ቤቶቹን ለመረከብ ቢያንስ አንድ አመት ይወስዳል ቢባልም።

ለባለ እድለኞች እጣ ወጥተው የነበሩት 32 ሺህ 653 የጋራ መኖርያ ቤቶች ጉዳይ ግን : ከቤቶቹ ውስጥ የአዲስ አበባን ወሰን በማለፍ ኦሮምያ ውስጥ የገቡ አሉ እንዲሁም ቤቶቹ ሲሰሩ ለተነሱ አርሶ አደሮች በቂ ካሳ አልተከፈለም በሚል በተነሳ አመጽ : የጋራ መኖርያ ቤቶቹ እጣ ቢወጣባቸውም ለእድለኞች አልተላለፉም ። የኦሮምያ ክልል መንግስትም በወቅቱ በክልሉና በአዲስ አበባ መካከል ያለው የወሰን ይገባኛል ችግር ካልተፈታ የጋራ መኖርያ ቤቶቹ እንዳይተላለፉ የሚጠይቅ መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል።

በከተማ አስተዳደሩና በኦሮምያ ክልል መካከል የአስተዳደር ውዝግብን ያስነሳው የኮዬ ፈጬ ኮንደሚኒየም ፕሮጀክት ነው። በወቅቱ በርካታ የ20/80 የጋራ መኖርያ ቤቶች እጣ የወጣውም ከዚሁ ሳይት ነው።

የእጣ ማውጣቱን ስነ ስርአት ተከትሎ በብዙ የኦሮምያ ክልል ከተሞች የተነሳው ተቃውሞ ተከትሎ ቤቶቹን የማስተላለፉ ሂደት በመቆሙ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደና የኦሮምያ ብሄራዊ ክልላዊ አስተዳደርን የአስተዳደር ወሰን ውዝግብን በዘላቂነት የሚፈታ ከሁለቱም አስስተዳደር ካቢኔ የተውጣጣ ስምንት አባላት ያሉት ኮሚቴ ማቋቋማቸውን የሚያትት መግለጫ ከጽህፈት ቤታቸው ወጣ።

የኮሚቴው ስራም በጥቅሉ ለበርካታ ጊዜያት መግባባት ሊፈጠርበት ያልቻለው የሁለቱን አስተዳደሮች የወሰን ውዝግብ በመፍታት የሁለቱ አስተዳደሮች ግንኙነት የልማት እንዲሆን የውሳኔ ምክረ ሀሳብ ማቅረብ መሆኑን ይገልጻል። መግለጫው የአስተዳደር ውዝግቡ የጋራ መኖርያ ቤቶቹ ለባለ እጣዎቹ እንዳይተላለፉ እክል መሆኑንም ያነሳል።

ውዝግቡን እንዲፈታ የተቋቋመው ስምንት አባላት ያሉት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ኦሮምያ ክልል የተውጣጡት የኮሚቴ አባላት ፣ሙፈርያት ካሚል በሰብሳቢነት ፣ ታከለ ኡማ ፣ ጠይባ ሀሰን ፣ ሰለሞን ኪዳኔ ፣ እንዳወቅ አብጤ ፣ አህመድ ቱሳ ፣ ግርማ አመንቴ እና ተስፋዬ በልጅጌን በአባልነት አካቷል።

ለኮሚቴው አባልነት በኦሮምያ ክልል ካቢኔ አባልነታቸው የተመረጡት ጠይባ ሀሰን ከክልሉ ሀላፊነታቸው ሲነሱ እንኳ ማን እንደተካቸው አልተገለጸም።

ይህም ሆኖ ከተቋቋመ ከዘጠኝ ወር በላይ የሆነው ኮሚቴ : ባለእድለኞች የወጣላቸውን የጋራ መኖርያ ቤት እንዲረከቡ የሚያደርግ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርንና የኦሮምያ ክልልን የአስተዳደር ውዝግብን የሚፈታ ምክረ ሀሳብ ሊያቀርብ ይቅርና በቅጡም ተሰብስቦ እንደማያውቅ ነው ዋዜማ ራዲዮ የኮሚቴው አባል ከሆኑ ታማኝ ምንጮቿ መረዳት የቻለችው። የኮሚቴው አባላት ስራቸው በምን ደረጃ ላይ እንዳለ እንኳ ሪፖርት አላቀረቡም : ተጠይቀውም አያውቁም።

የቤቱ እድለኛ ለመሆን የሚያበቃቸውን የሀያ በመቶ መዋጮ ቆጥበው እድለኛ የሆኑ ግለሰቦች ዛሬ ላይ ዘጠኝ ወር አልፎ እንኳ እድለኛ የሆኑበትን ቤት አለመረከባቸው ከፍተኛ ቅሬታ እንደፈጠረባቸውም ለዋዜማ ራዲዮ አስተያየታቸውን የሰጡ የቤቶቹ እድለኞችም ገልጸዋል። ይህም ብቻ ሳይሆን መንግስት ቤቶቹን ለማስረከብ ምንም አይነት ምልክት አለማሳየቱ በቀጣይ የቤት እድለኛ ለመሆን ሲቆጥቡ የነበሩ ተመዝጋቢዎችን ከፍተኛ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ በመጨመር ሲያደርጉ ከነበረው ቁጠባ እንዲታቀቡ አድርጓቸዋል።

ከ32 ሺህ በላይ የ20/80 ቆጣቢዎች ቤታቸንን ከአሁን አሁን እንረከባለን ብለው በሚጠባበቁበት በዚህ ጊዜ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳርደር የልማት ተነሽ ላላቸው 23 ሺህ አርሶ አደሮች ፣ ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው የጋራ መኖርያ ቤቶችን በፍጥነት አከፋፍሏል። የልማት ተነሽ ለተባሉት ግለሰቦች የጋራ መኖርያ ቤቶችን ብቻ ሳይሆን የንግድ ቤቶችን የማስተላለፍ ሰፊ ስራም ተሰርቷል።

የልማት ተነሺ ተብለው አሁንም የድርብርብ ካሳ ተጠቃሚ ከሆኑት ውስጥ የማይገባቸው ሰዎች እንዳሉ ዋዜማ ተጨማሪ መረጃዎች አሁንም ደርሰዋታል። የልማት ተነሽ ለተባሉት አርሶ አደሮች ቀድሞ ሲሰጥ ከነበረው የተሻለ ካሳ ከተሰጠ : ለበርካታ አመታት ገንዘባቸውን ቆጥበው የቤት እድለኛ ለሆኑት ዜጎች በእጣ የደረሳቸውን ቤት የማስረከቡ ስራ በከፍተኛ ደረጃ መዘግየቱ ከፍ ያለ ቅሬታን አስከትሏል።

የነበሩ ውዝግቦችን እንዲፈታ ከተቋቋመው ኮሚቴ እጅግ አዝጋሚ የስራ አፈጻጸም ባሻገር መንግስት አንድም ቀን እጣ ወጥቶላቸው ቤታቸውን ስላልተረከቡ እድለኞች እጣ ፈንታ መረጃ ሰጥቶም አያውቅም። [ዋዜማ ራዲዮ]

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top