Connect with us

ከሞጣ የቤተእምነት ውድመት ጋር በተያያዘ የታሰሩት ሰዎች ቁጥር 36 ደረሰ

ከሞጣ የቤተእምነት ውድመት ጋር በተያያዘ የታሰሩት ሰዎች ቁጥር 36 ደረሰ
Photo: Facebook

ህግና ስርዓት

ከሞጣ የቤተእምነት ውድመት ጋር በተያያዘ የታሰሩት ሰዎች ቁጥር 36 ደረሰ

ከሞጣ ከተማ አስተዳድር በሃይማኖት ተቋማትና የገበያ ማዕከል ማቃጠል ድርጊት ጋር በተያያዘ 36 ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አበረ አዳሙ አስታወቁ፡፡

የሞጣው ክስተት ወደ ተባባሰ ደረጃ እንዳይሸጋገር የአማራ ፖሊስና ልዩ ኃይል ፈጥነው በመድረስ ችግሩን በማርገብ ከፍተኛ ኃላፊነት እንደተወጡም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡ በድርጊቱ ተሳትፈዋል የተባሉ 36 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር እንደዋሉም ኮሚሽነር አበረ አዳሙ አስታውቀዋል፤ የተዘረፉ ንብረቶች እየተመለሱ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

በሞጣ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ ማኅበረሰብ ክፍሎችን በማወያየት የተፈፀመው ድርጊት የአማራን ሕዝብ ሥነ-ልቦና የማይወክል መሆኑን በመገንዘብ ችግሩ እየተፈታ ስለመሆኑም አመላክተዋል፡፡ ወጣቶች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች መድረክ ተፈጥሮ መወያዬታቸውንና ሞጣ አካባቢ ችግሩ መፈታቱን ነው ያስታወቁት፡፡

በሀገሪቱ ያለውን ለውጥ ማደናቀፍ የሚሻ አካል በመኖሩ ችግሮች እንዲፈጠሩና ሲፈጠሩም ለማባባስ እየተሞከረ መሆኑን ያገነዘቡት ኮሚሽነሩ በሃይማኖት ተከታዮች ስም መጥፎ ታሪክ እንዳይመዘገብ ጥንቃቄ እንዲያደርጉም አሳስበዋል፡፡

የሃይማኖት አባቶች ችግሮች እንዳይባባሱ የራሳቸውን ጉልህ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱም ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ማኅበረሰቡ መረጃ በመስጠት፣ በጋራ በመሥራትና ፖሊስን በመደገፍ እንዲተባበርም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ጉዳዩን በማባባስ ለማትረፍ የሚጣጣሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡም አሳስበዋል፡፡ ‹‹አንድ ቦታ ላይ ግጭት ቢፈጠር አትራፊ አይኖርም፤ የሚያተርፈው ሰይጣን ብቻ ነው፤ ለሰይጣን ደግሞ አገልጋይ መሆን አይገባም›› ያሉት ኮሚሽነሩ ማንኛውም ሰው በሃይማኖትም ሆነ በሌላ እምነት የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ከፖሊስ ጋር አብረው እንዲሠሩም ከአማራ ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ ጥሪ አድርገዋል፡፡

በዚህ ጊዜ የአማራ ክልል የፀጥታ ሁኔታ አልፎ አልፎ ከሚፈጠሩ ክስተቶች በስተቀር በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ኮሚሽነሩ ‹‹በግድ ‹ይህ ክልል ካልፈረሰ› የሚል ምኞት ያለው አካል ካለ ተስፋ ይቁረጥ›› ብለዋል፡፡

በግልፅና በስውር የተደራጁ ኃይሎች የጥፋት እጃቸውን ከክልሉ ማንሳት እንዳባቸውም አስጠንቅቀዋል፡፡

የአማራን ሕዝብ ሥነ-ልቦና የማይመጥኑ የተሳሳቱና የተዛቡ ዘገባዎች መስተካከል እንዳለባቸው ያሳሰቡት ኮሚሽነሩ ‹‹ክልሉ በልማትና ስልጣኔ ጎዳና እንዲጓዝ እንሻለን›› ብለዋል፡፡(አማራ መገናኛ ብዙሃን ድርጅት)

ይህ በእንዲህ እዳለ በሞጣ በቤተእምነት ላይ የተሰነዘረውን ጥቃት በማውገዝ በአዲስአበባ በአንዋር መስጊድ እና በአማራ አንዳንድ አካባቢዎች ሰላማዊ ሰልፎች ተካሂደዋል፡፡

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top