Connect with us

ኢዴፓ እና ኢዜማ – ዳይ ከሽኩቻ ወደ ትብብር!

ኢዴፓ እና ኢዜማ - ዳይ ከሽኩቻ ወደ ትብብር!
Photo: Facebook

ፓለቲካ

ኢዴፓ እና ኢዜማ – ዳይ ከሽኩቻ ወደ ትብብር!

ኢዴፓ እና ኢዜማ – ዳይ ከሽኩቻ ወደ ትብብር!
(ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Email: ahayder2000@gmail.com

ሄኖክ ለይኩን (#Henok_Leykun) የተባለ የኢዜማ አባል የሆነ የፌስቡክ ወዳጄ የላከልኝ የሽምግልና መልእክት “አሁን ሀገራችን ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ያለ ስጋት ፖለቲካ የሚሰራበት ጊዜ አግኝታለች። ምናልባት ይህ እድል ዳግም የማናገኘው ብቻ ሳይሆን ከዚህ ቀደምም አግኝተነው የማናውቀው ነው… እናም ይህ ጊዜ እንዳያመልጠን ሁላችንም ልንጠብቀው ይገባል…” ካለ በኋላ “የቀድሞ ፓርቲያችሁ ኢዴፓ በጥረቱ ከምርጫ ቦርድ የሚያስደስት ውሳኔ አግኝቷል። ቦርዱም ኢዴፓውያን በሄዱበት ሁሉ አገልግሎት እንዲያገኙ ደብዳቤ ሰጥቶ ሸኝቷቸዋል… ቢሮን በተመለከተ ምርጫ ቦርድ በቀጥታ ለፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን አዞላቸዋል። ሆኖም… ኢዴፓዎች ለምንድን ነው ኢዜማ የወሰደባቸውን ቢሮ ይመለስልን የሚሉት?” በማለት ይጠይቅና “እስቲ ሳታዳሉ ተናገሩ” ብሎ “ፍርድ እንድንሰጥ” እኔና ሙሼ ሰሙን ይጋብዘናል፡፡

ሙሼ ሰሙ እዚያው ፌስ ቡክ ላይ መልስ ሰጥቷል፡፡ በእኔ በኩል በጉዳዩ ላይ ትንሽ አሰብኩበትና ይህቺን ማስታወሻ ለመክተብ ተነሳሁ፡፡ ሄኖክ ይህንን ማስታወሻ የጻፈበትን ምክንያት ከማየቴ በፊት የመንደርደሪያ ሃሳብ ላስቀድም…

ነገሩ እንዲህ ነው… ከዓመታት በፊት ኢዴፓ ውስጥ መከፋፈልና ሽኩቻ ነበር፡፡ ነገሩ እልባት ሳያገኝ የሀገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ተለዋወጠና “ኢዜማ” የተባለ ፓርቲ የምስረታ ሂደት ጀመረ፡፡ በወቅቱ የኢዴፓ ፕሬዝዳንት የነበሩት ዶ/ር ጫኔ ከበደ “ኢዴፓን አክስሜያለሁ፣ እኔም ከኢዜማ ጋር ተቀላቅያለሁ” ብለው አወጁ፡፡ የኢዴፓን ሀብትና ንብረት ይዘው ወደ ኢዜማ ገቡ፡፡ የኢዴፓን ቢሮዎች ለኢዜማ አስረከቡ…

በሌላ በኩል “የለም! ኢዴፓ አልከሰመም” የሚሉ የኢዴፓ አባላት አቤቱታቸውን ለምርጫ ቦርድ አቀረቡ፡፡ ለዓመታት ሲከራከሩ ቆዩና ሰሞኑን ምርጫ ቦርድ በሰጠው ውሳኔ “ኢዴፓ አልከሰመም” ተባለ፡፡ ይህንን ውሳኔ ያገኙት ኢዴፓዎች “ከ20 ዓመታት በላይ ስንጠቀምበት የነበረውን ቢሮ ኢዜማ ይመልስልን” ብለው ለኢዜማ ደብዳቤ ጻፉ፡፡

የፌስቡክ ወዳጄ ሄኖክ እንግዲህ በዚህ ላይ ነው አስተያየት እንድንሰጥ የጋበዘን፡፡ የወዳጄ ፍላጎት “ኢዜማ በያዘው ይርጋ፡፡ ኢዴፓ ሌላ ቢሮ ይፈልግ” የሚል ነው፡፡ ጥሪ ያደረገልን እኔና ሙሼ ይህንን ፍላጎቱን “ልክ ነው” እንድንለው ስለፈለገ ነው እንጂ መቼም መልሱ ጠፍቶት አይመስለኝም፡፡

በበኩሌ በዚህ ጉዳይ ላይ “ፍርድ መስጠት” አልፈለግኩም፡፡ ይልቁንም የቢሮውን ጉዳይ ትተን የፓርቲዎቹን ጉዳይ እንይ፡፡ እንደኔ እንደኔ የኢዴፓ እና የኢዜማ ነገር ከቢሮ “መልስ – አልመልስም” አታካሮ ፈቀቅ ያለ ነው፡፡ የችግሩ ምንጭ ሁለቱን ፓርቲዎች ከሚመሩት ከዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እና ከልደቱ አያሌው ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ሁለቱ ፖለቲከኞች ያላቸውን የግል “እልህ፣ ቂምና ቁርሾ” ወደ ፓርቲዎቹ ጎትተው በመውሰድ የፓርቲዎቹን አባላትና ደጋፊዎች በማያውቁትና በማያገባቸው ጉዳይ እንዲነታረኩ በር መክፈታቸው አሳሳቢ ነው፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች በዚህ ምርጫ በተቃረበበት ወቅት መተባበር ሲገባቸው፤ በቢሮ “መልስ – አልመልስም” አታካሮ ዶሴ ይዘው በየፍርድ ቤቱ የሚመላለሱ ከሆነ ለሀገርም ለህዝብም ኪሳራ ነው፡፡

ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እና አቶ ልደቱ አያሌው በአንድ ወቅት ወዳጆችና የትግል አጋሮች ነበሩ፡፡ በትግሉ ሂደት የሃሳብ ልዩነት ተፈጠረና ተለያዩ፡፡ ይሄ ከ15 ዓመታት በፊት የሆነ ነገር ነው፡፡ ያኔም ቢሆን ሁለቱ ፖለቲከኞች የሃሳብ ግጭት የፈጠሩት የጋራ ሀገር ስላላቸው እንጂ በግል ጉዳያቸው በተፈጠረ ፀብ አልነበረም፡፡ ደግሞም ልዩነቱ የተፈጠረው በግቡ ሳይሆን ወደ ግቡ በሚደረግ ሂደትና በስልቱ ላይ ይመስለኛል… ያኔ በነበራቸው እልህ የተሞላበት መገፋፋት የፓርቲያቸውን አባላት፣ ደጋፊዎች እና መላውን ህዝብ አስቀይመዋል፣ አስከፍተዋል፡፡ በወቅቱ በእጃቸው ገብቶ የነበረውን ድል እልህ ውስጥ ገብተው በፈጠሩት ገመድ ጉተታ መና አስቀርተውታል፡፡

እነዚህ ፖለቲከኞች የዛሬ 15 ዓመት የሰሩት “ስህተት” አልበቃቸው ብሎ ዛሬም የንትርክ ነጋሪት መጎሰማቸው አንዳች የተጠናወታቸው ጋኔን ቢኖር ነው እንጂ ሌላ ምን ይባላል? በእልህ ወደ ሌላ የጭቅጭቅ አዙሪት ውስጥ ለመግባት ሰበብ መፈለግ አንድም ህዝብን መናቅ አሊያም ካለፈ ስህተት አለመማር ካልሆነ በስተቀር ሌላ ትርጉም ሊሰጠው የሚችል አይመስለኝም፡፡
“በፖለቲካ ዘላለማዊ ወዳጅም ሆነ ዘላለማዊ ጠላት የለም” እንዲሉ ዛሬ ሁሉም ነገር ተለውጧል፡፡ ከስህተታቸው ተምረው፣ ለህዝብና ለሀገር ሲሉ ይቅር ተባብለው፣ እንደገና አብረው በመስራት በምርጫ 97 ያስከፉትንና ያስቀየሙትን ህዝብ ሊክሱት ይገባል፡፡ ስለሆነም፤ የሁለቱም ፓርቲዎች አባላትና ደጋፊዎች ዶ/ር ብርሃኑን እና አቶ ልደቱን “በቃችሁ፣ ተደራደሩና አብረን የምንሰራበትን መንገድ ፍጠሩ” ሊሏቸው ይገባል፡፡

መጪው ጊዜ የምርጫ ወቅት ነው፡፡ ፓርቲዎች ትልቅ ሥራ ይጠብቃቸዋል፡፡ በገዢው ፓርቲ በኩል “99% አሸነፍኩ” የሚባልበት ዘመን አብቅቷል፡፡ በተፎካካሪ ፓርቲዎችም በኩል ቢሆን እንደ ቀደሙት ዓመታት የኢህአዴግን ድክመት በመናገር የፓርላማ መቀመጫ ማግኘት የሚቻል አይሆንም፡፡ ብዙ ጥረት ያደረገ ብዙ ያገኛል፡፡ ያንቀላፋም በዜሮ ይወጣል፡፡ እናም በዋዛ ፈዛዛ የሚያልፍ የሴኮንዶች ቅንስናሽ ሊኖር አይገባም፡፡

በሌላ በኩል የፖለቲካ ፓርቲዎች በዝተዋል፡፡ ሀገሪቱ ወፈ-ሰማይ የፖለቲካ ፓርቲ የምትሸከምበት አቅም የላትም፡፡ ተፈጥሮ የቸረቻት የቋንቋ፣ የብሄር፣ የሃይማኖት፣… “ብዝሃነት” አልበቃት ብሎ ከመቶ በላይ የፖለቲካ ፓርቲ መፈልፈል ከድጡ ወደ ማጡ ከመሆን የዘለለ ፋይዳ ያለው ሆኖ አይታየኝም፡፡ ተመሳሳይ ዓላማ ያላቸው ፓርቲዎች መዋሃድ ወይም በትብብር መስራት ይገባቸዋል፡፡
ኢዴፓ እና ኢዜማ መሰረታዊ የሆነ የርእዮተ-ዓለም ልዩነት የላቸውም፡፡ እናም ዶ/ር ብርሃኑ እና አቶ ልደቱ ማላገጡን ትተው ሁለቱን ፓርቲዎች አዋህደው ጠንካራ አማራጭ ሆነው መቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ኢዴፓም ሆነ ኢዜማ ውዝግቡን በዚሁ ከቀጠሉ ግን ከጊዜና ከሃብት ብክነት በተጨማሪ ሕዝብ አንቅሮ ሊተፋቸው እንደሚችል ማሰብ ብልህነት ነው፡፡

ለቀድሞ የትግል አጋሮቼ ኢዴፓውያን አንድ መልእክት አለኝ፡፡ በፖለቲካ ዘላለማዊ ጠላት የለም፡፡ አብራችሁ ብትሰሩ የህዝብን ቀልብና ልብ ለመግዛት ትችላላችሁ፡፡ የህዝብ ቀልብና ልብ ትልቅ ቢሮ ነው፡፡ እሰጥ አገባ ውስጥ አትግቡ፡፡ ለመርህ ተገዢ ሁኑ፡፡ ትልቁን ስዕል ተመልከቱ፡፡ ቂም በቀልን አስወግዱ፡፡ ወደ ውስጣችሁም ተመልከቱ፡፡ ለሀገርና ለሕዝብ ክብርና ልዕልና ትኩረት ስጡ፡፡ ኢዜማ ውስጥ ላላችሁ ወዳጆቼም ይኸው መልእክቴ ይድረሳችሁ! – ዳይ ከሽኩቻ ወደ ትብብር!

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top