የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ከአገር የሸሹ ሀብቶችን ለማሰመለስ፤ የሀብት ማሰመለስ ስትራቴጂ ማዘጋጀቱን፣ ሀብቱ የሸሸባቸው አገራትን የመለየት ሥራ መሰራቱንና ከአገራቱም ጋር ውይይት መጀመሩን ገልጿል።
በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዝናቡ ቱኑ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ሀብቱ ከሸሸባቸው አገራት ጋር የተደረገው ውይይት ሁሉም አገራት በሚባልበት ደረጃ ሰምምነት ላይ መደረሱን ጠቅሰው በወንጀል የተገኘ ሀብት የማስመለስ ዳይሬክቶሬት መቋቋሙንም ተናግረዋል።
ከአገራቱ ጋር ባለው ንግግር የተዘረፈው ሀብት በምን መልኩ ይመለሳል? የሚለውን ለመወሰን ያሉ ዓለም አቀፍ ሕግጋትን እያጠኑ እንደሆነና በድርጊቱ ውስጥ የተሳተፉ አካላት በምን አግባብ እንደሚጠየቁ እየተሰራበት እንደሆነም ለቢቢሲ አስረድተዋል።
ገንዘቡ ወዴት ሀገር ሸሸ? ምን ያህል ገንዘብ ከአገር ወጥቷል? የሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ አግኝተዋል የሚሉት አቶ ዝናቡ፤ ምን ያህል የገንዘብ መጠን ወደ የትኞቹ አገራት ሸሽቷል? የሚለውን “እየተሰራ ያለውን ሥራ ያደናቅፋል” በሚል ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
አቶ ዝናቡ ቱኑ በዚህ ወንጀል የተሳተፉ ተጠርጣሪዎችን ለሕግ የማቅረብ፣ ገንዘቡን የማስመለስ ዝርዝር መረጃዎችን ጊዜው ሲደርስ ይገለፃል በማለት ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
“አሁን ባለው መረጃ ሀብቶቹን የማሸሽ ተግባራት ላይ ተሳትፈው የነበሩት የመንግሥት መዋቅር ውስጥ የነበሩና ተባባሪዎቻቸው ናቸው” ያሉት አቶ ዝናቡ፣ “ሀብቱን የመዘበሩ አካላት ለሕግ መቅረባቸው አይቀሬ ነው” ብለዋል።
አቶ ዝናቡ እነዚህን ግለሰቦች በሕግ ፊት አቅርቦ ለመጠየቅ የሚያስችል ጥናት እየተካሄደና ማስረጃ ተሰባስቦ እየተደራጀ መሆኑንም ጨምረው በመግለጽ “ማንም በዚህ ወንጀል የተሳተፈ ሳይጠየቅ አይቀርም” ብለዋል።
ይህ ሥራ ከዚህ በፊት ተጀምሮ ቢቆይም በልምድ ማነስ ምክንያት የሚፈለገውን ውጤት አለመምጣቱን በመግለጽም አሁን ግን ሀብት የማስመለስ ስትራቴጂ መቀረጹን ገልፀዋል። ይህንን ሊመራ የሚችል የሥራ ክፍል መዋቀሩንም ኃላፊው ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
ሀብት ማሸሽ በርካታ መልኮች እንዳሉት የጠቀሱት አቶ ዝናቡ “ከአገር የወጣ ሀብት በተለያየ መልኩ ለወንጀል ተግባራት ውሏል፣ በሕገ ወጥ መንገድ የወጣ ሀብትን መልሶ ሕጋዊ በማስመሰል የመጠቀም አዝማሚያ ነበር” ብለዋል።
መንግሥት ከገንዘብ ዝውውርና መሰል ተግባራት ጋር ከሚሰሩ አጋር ድርጅቶች ጋር በመስራቱ የኢትዮጵያ ስም ከእነዚህ አገራት ተርታ እንዲሰረዝ ማድረጉንም አቶ ዝናቡ ተናግረዋል።
“ፋይናንሻል አክሽን ታክስ ፎርስ” የተባለው ተቋም ኢትዮጵያ ሀብት ከሚሸሽባቸው አገራት ዝርዝር ውስጥ ለመውጣት እየሰራችው ያለው ሥራ የሚያስመሰግን ነው በሚል ስሟን ሀብት ከሚሸሽባቸው አገራት መካከል እንድትወጣ መደረጉን ገልጸዋል።