የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ቀንድ ታሪክ በሚል ርዕስ ለዩኒቨርስቲ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች ማስተማሪያ እንዲሆን የተዘጋጀ ሞጁልን ይመለከታል፡፡
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታው በተቀመጠው ምክረ ሃሳብ መሰረት በ2012 የትምህርት ዘመን አዳዲስ የአንደኛ ዓመት ተማሪዎች ፕሮግራምና ኮርሶች ተቀርፀው በመንግስት ዩኒቨርስቲዎች በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡
በአንደኛው መንፈቅ ዓመት ወደስራ የገቡት ኮርሶች የተማሪዎችን እውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት ለማሳደግ ያላቸው ሚና አዎንታዊ እንደሆነ ይታመናል፡፡
ይሄንንም ተማሪዎች ራሳቸው በተለያዩ መንገዶች በሰጡት ምስክርነት ለመረዳት ተችሏል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ በሁለተኛው መንፈቅ ዓመት ከሚሰጡት ኮርሶች መካከል አንዱ ለሆነው የኢትዮጵያና የአፍሪካ ቀንድ ታሪክ ሞጁል ረቂቅ ተዘጋጅቶ ተጨማሪ ግብዓት ማሰባሰብ ይቻል ዘንድ ለዩኒቨርስቲዎች ተልኳል፡፡
በዚህ ሞጁል ላይ ከዩኒቨርስቲዎች የተሰባሰበውን ግብዓት በማካተትና በወርክሾፕ የጋራ በማድረግ ለመጀመሪያ ዓመት የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ማስተማሪያነት የሚያገለግል የኢትዮጵያና የአፍሪካ ቀንድ ታሪክ በሞጁል መልክ አዘጋጅቶ ለማውጣት ታህሳስ 16፣17 እና 18 ቀን 2012 ዓ.ም ቀጠሮ ተይዟል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም በመነሻ ሰነዱ ላይ ግብዓት ማሰባሰብ ይችል ዘንድ ሰነዱን ወደ ዩኒቨርስቲዎች ለአስተያየት ሲልከውም ሆነ ይሄንን መድረክ ሲያመቻች የሞጁሉ ዝግጅትና ይዘት በጥንቃቄ መታየት እንዳለበት በማመን ነው፡፡
ይህን ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች በተውጣጡ የታሪክ ባለሙያዎች ተፅፎ በረቂቅ ደረጃ ያለውን ሞጁል ያለቀለትና ለማስተማሪያነት የተላከ በማስመሰል እየቀረበ ያለው መረጃ ስህተት መሆኑን እናሳውቃለን፡፡
በተጨማሪም እስከ ታህሳስ 16 ቀን 2012 ዓ.ም የሚሠጡ ግብዓቶች ተካትተው ከሁሉም ዩኒቨርስቲዎች በወርክሾፑ በሚገኙ የታሪክ ትምህርት ክፍል ኃላፊዎችና መምህራን፣ የታሪክ ምርምር ማህበራት፣ የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ስራ ላይ የሚሰሩ፣ እንዲሁም ሌሎች በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት ስምምነት ላይ የደረሱበት የመጨረሻው ሰነድ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ይቀርባል፡፡
ስለሆነም ሁሉም የታሪክ ተመራማሪዎችና መምህራን በሞጁሉ ላይ ያላችሁን አስተያየት በinfo@ethernet.edu.et በመላክ ሙያዊ ግዴታችሁን እንድትወጡ እንጠይቃለን፡፡
ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር