Connect with us

የአገሪቱን ሀብት ሲበዘብዙ የነበሩ ኃይሎች …

“ክልሎችን እኛ እናውቅልሃለን በማለትና የአገሪቱን ሀብት ሲበዘብዙ የነበሩ ኃይሎች
Photo: Facebook

ፓለቲካ

የአገሪቱን ሀብት ሲበዘብዙ የነበሩ ኃይሎች …

“ክልሎችን እኛ እናውቅልሃለን በማለትና የአገሪቱን ሀብት ሲበዘብዙ የነበሩ ኃይሎች ዛሬ ደርሰው ለፌዴራሊዝም ጠበቃ ነን ሲሉ ለእኔ የሚመስለኝ ኢትዮጵያውያን ላይ ማሾፍ ነው” ዶክተር ዓለሙ ስሜ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ግንባታ ማዕከላት አስተባባሪ

• ለፌዴራሊዝም ጠበቃ ለመቆም የሚጥረው ኃይል ትላንት እዚህ አገር እውነተኛ ፌዴራሊዝም እንዳይሰፍን ሲያደርጉ ከነበሩት ውስጥ ግንባር ቀደም ሚና ሲጫወት የነበረው ሀይል ነው፤

• የኢትዮጵያ ህዝብ የጠየቀው እውነተኛ ፌዴራሊዝምን እንጂ ፌዴራሊዝም አልጠቀመኝምና ወደኋላ ይመለስ አላለም። በመሆኑም አዲሱ ፓርቲ ፌዴራሊዝምን ወደኋላ የሚተው ጅላጅል ፓርቲ አይደለም፤

• የብልፅግናን ፓርቲን የተቀላቀልነው እውነተኛ የፌዴራሊዝም አቀንቃኞች ነን። ሶስቱ በኢህአዴግ ውስጥ የነበሩና አምስት አጋር የነበሩ ድርጅቶች ናቸው፣

• በኢህአዴግ የተዛባውን የፌዴራሊዝም ስርዓት ለማስተካከል የታገሉ፣ ለውጡን በማምጣት ግንባር ቀደም ሚና የተጫወቱ በመሆናቸው ፌዴራሊዝምን ለማስተካከል ይሰራሉ።

• ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ ፌዴራሊዝምን ሳይቀበል የሚንቀሳቀስ ግለሰብም ይሁን ፓርቲ ራሱን በራሱ የሚያጠፋ ነው። ህዝቡ አይከተለውም።

• አሁን ያለው የለውጥ አመራር ፌዴራሊዝምን ለማፍረስ ነው የሚሰራው የሚለው ክስ ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ይመስለኛል።

• ባለፉት 28 ዓመታት በፓርቲ ማዕከላዊነት የተጠረነፈ፣ ክልሎች ነፃነት የሌላቸው፣ የራሳቸውን የክልል መስተዳድር፣ ካብኔ ነፃና ህገ መንግስታዊ በሆነ መንገድ ማዋቀር የማይችሉበት ፌዴራሊዝም ነበር፣

• በፌዴራል ደረጃ እኩል የመወሰን እድል የተነፈገበት ስርአት ነበር፤ ብዙ ቋንቋ ተናጋሪ እያለን እንኳን በፌዴራል ደረጃ አንድ ቋንቋ ብቻ ነው ስራ ላይ የዋለው፤

• ችግሮች ከፈጠሩት መካከል ግንባር ቀደሙ በአሁኑ ወቅት የፌዴራሊዝም ጠበቃ እኔ ነኝ የሚለው። ይህ ጠበቃ ነኝ ባይ የፌዴራሊስት ኃይሎች በሚልም ደጋፊ ለማሰባሰብ ጥረት እያደረገ ነው፤

• ከዚህ አንፃር ጠበቃ ነኝ ባዩ የሞራል ብቃት የለውም። በጥቅሉ የፌዴራሊዝም ጠበቃ እኔ ነኝ የሚለው አካል ግንባር ቀደም ችግር ፈጣሪ ነበር።

• አጋር ፓርቲዎች ሲባሉ የነበሩት ከማንም በላይ እውነተኛ ፌዴራሊዝም ባለመኖሩ የተጎዱት ናቸው፤ እውነተኛ ፌዴራሊዝምን ፍለጋ ውህድ ፓርቲውን ፍለጋ እየተንቀሳቀሱ ያሉት።

• ስለዚህም በአሁኑ ወቅት አዲሱን ፓርቲ የመሰረቱት ለእውነተኛ ፌዴራሊዝም የታገሉ ናቸው።

• ፌዴራሊዝም በኢትዮጵያ ህገ መንግስታዊ ነው። ማንም ተነስቶ ፌዴራሊዝምን በማፍረስ አሃዳዊ መንግስት ሊመሰርት አይችልም፤ህገ መንግስቱ በፍፁም አይፈቅድም።

• የውሸት ምርጫና መድብለ ፓርቲ ነበር ያለው። በአሁኑ ወቅት ለውጡ ከሌሎች ጥያቄዎች ጎን ለጎን በዋነኝነት ምላሽ የሰጠው ለዴሞክራሲ ጥያቄ ነው።

• ዴሞክራሲ እንደሚታወቀው በሂደት የሚመጣ ነው። ባህሉን ገና አላጎለበትንምና ብስለትና ቁርጠኝነት ከሁሉም ዜጎች ይጠበቃል።

• መንግስት ዴሞክራሲን ተገን በማድረግ የሚፈጸሙ ወጣ ያሉ ነገሮችን በትዕግስት በማለፉ ትዕግስቱ ወሰን እንዳጣ አድርገው የተናገሩ አሉ፤

• መንግስት ወደ ድሮ ማንነቱ ማለትም አስሮ ገራፊነት እንዲመለስ የሚገፋፉም አልታጡም።ጉዳዩ የህዝብንና የመንግስትን ማስተዋል ይጠይቃል።

• የሃይማኖት መሪዎች፣ ምሁራን፣ ህዝቡ ሁሉ ከለውጡ ጎን ቢቆሙ መልካም ነው።

• ኢትዮጵያ ውስጥ በተደጋጋሚ የለውጥ እድሎች መጥተዋል፤ ግን አልተጠቀምንባቸውም። ሁሉም የለውጥእድሎች በአግባቡ ስላልተመሩ ለውጦቹ አልጠቀሙንም፤ እንዲያውም ከመፍረስ አፋፍ እየተመለስን ተርፈናል ማለት ያስደፍራል።

• አብዮታዊ ዴሞክራሲ ያጎደለው አንዱ ህብረተሰብን በጎራ መለየቱ ነው። ለምሳሌ ባለሀብትን ብንወስድ ልማታዊ ባለሀብት ይላል፤ ኪራይ ሰብሳቢ ባለሀብትም ይላል። ሁለቱ የተለዩበት ግልፅ የሆነ መስፈርት የለም።

• ነገር ግን ልማታዊ የተባለው በላቡና በድካሙ ያገኘ የሚመስል ሲሆን፣ ኪራይ ሰበብሳቢው ደግሞ አጭበርባሪውን ለማለት ሊሆን ይችላል።

• ይሁንና በተጨባጭ ሲታይ ግን ልማታዊዎቹ ወደኢህአዴግ የተጠጉ ሲሆኑ፣ ኪራይ ሰብሳቢ የሚባሉት ደግሞ ኢህአዴግን ያልተጠጉት ናቸው።

• ከለውጡ በኋላም ሆነ ወደ ለውጡ ስንሄድ እውነታው ግን ሌባ በመሆን የበዛው መንግስትን የተጠጋው ነው።

• ልማታዊ ባለሀብቱ ከመንግስት ሹማምንት ጋር የተጠጋው ነው። በማጭበርበርና በመስረቅም ይታወቃል።

• አብዮታዊ ዴሞክራሲ ምሁራንንም ተራማጅ እና ወላዋይ በማለት ይጠራቸዋል። ይህም ከኢህአዴግ ጋር ካለው ቅርበትና ርቀት ይነሳል። ምንም መስፈርት የለውም፤

• ኢህአዴግን የተጠጋው ምሁር አልምጥም ይሁን ለአገር አሳቢም ይሁን ተራማጅ ይባላል፤ ከኢህአዴግ የራቀው ደግሞ የቱንም ያህል ታታሪ ይሁን እንደጠላት ተቆጥሮ ወላዋይ ይባላል።

• የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አግላይነት ነው። አርብቶ አደሩ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ማህበራዊ መሰረት ሊሆን አይችልም የሚል ነው።

• እንዲህም ሲባል አርብቶ አደሮች ገና ያልነቁና በጎሳም የሚተተዳደሩ ስለሆኑ ማህበራዊ መሰረትን ሊሸከሙ አይችሉም በሚል ነው።

• ይሁንና አርብቶ አደሮች በኦሮሚያም ሆነ በደቡብ ክልል አሉ፤ እነዚህ ግን አልተገለሉም።

• አርብቶ አደሮች የደኢህዴን የኦዲፒ ማዕከላዊ ኮሚቴ አልፎ ተርፎ የኢህአዴግ ምክር ቤት አባል ሆነው ሲያገለግሉ ይስተዋላል።

• ሐረሪን ብንወስድ እንኳን አርብቶ አደር ቀርቶ አርሶ አደር እንኳ የሌላትና በንቃተ ህሊና ከተባለ ከሌሎች ተሽላ የምትገኝ ናትና የሚሰራ አይደለም፤ ስለዚህ አርብቶ አደር ስለሆኑ ነው የተውኳቸው የሚለው አመክንዮ አይሰራም።

• ብልፅግና ፓርቲ አካታች ነው ሲባል የሚቀር የለም ለማለት ነው። ለሁሉም በሩ ክፍት ነው። በጥቅሉ ይህንን አያቅፍም ተብሎ የሚገለል የለም።

• መደመር የዜጎችን ጤና እንደ አንድ ግብ የሚይዝ ሲሆን፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግን የዜጎችን ጤና የምጠብቀው እንዲያመርቱ ነው ይላል። በዚህም ነው ብልፅግና ሁሉን አቀፍ ነው የሚባለው።

• መደመር ከዴሞክራሲ አኳያ የዜጎች፣ የቡድንና የግለሰብ መብቶች እኩል መከበር አለባቸው ይላል። መደመር ከሰው ማንነት ይጀምራል።

• ብልፅግና ፓርቲ ስልጣን ላይ ለመቆየት የሚያስችለው ህጋዊ ምክንያት አለው። የመጀመሪያው ብልፅግና ፓርቲ የኢህአዴግ ወራሽ ነው። ይህን የመረጠው ኢህአዴግ ራሱ ነው። በውስጡ ያሉ ከሞላ ጎደል የኢህአዴግ አባላት ናቸው።

• በሐዋሳ በተካሄደው 11ኛው የኢህአዴግ ጉባኤም የኢህአዴግ ምክር ቤት አዲሱን ፓርቲ እንዲመሰርት ውክልና ሰጥቶታል።

• ውህደት ምክር ቤቱ ኢህአዴግ ያለው መብትና ግዴታ በሙሉ ወደ አዲሱ ፓርቲ እንዲዞር ስላደረገ ህጋዊም ፖለቲካዊም ስልጣን አለው ማለት ነው።

• የአገሪቱን ሰላምና ህልውና ለአደጋ ለሚዳርግ ሁኔታ ያበቃው አንዱ ችግር የሌሎች መብቶች አለመከበር ነው፤ይህ እንዳለ ሆኖ በልዩነት ላይ የተሰራው ስራም ዛሬ እያየን ያለነውን በጎ ያልሆነ ነገር አስከትሏል።

• በ27 ዓመት ውስጥ በሰራናቸው ልዩነቶች ሳቢያ በሁለት ግለሰቦች መካከል ግጭት ሲፈጠር ወይ ወደ ሃይማኖት አሊያም ወደ ብሄር ግጭት እንዲለወጥ የሚያደርጉ ነገሮች እየተፈጠሩ ነው።

• ሙስሊም ከክርስቲያን ፣ ኦሮሞው ከአማራው እንዲሁም ትግራዩ ከሌላው ጋር ተጋብቷል። አንዱ ብሄር ከሌላው ብሄር ጋር በመጋባት ተሰናስሏል። በዚህም ሁሉም ተጋምዷል ማለት ይቻላል።

• ብቻውን እንደ ደሴት የተገነጠለ ዘር የለም። ከመተሳሰሩም የተነሳ የአንዱን ሃይማኖት በዓል የሌላ ሃይማኖት ተከታይ ያከብረዋል።

• አብዮታዊ ዴሞክራሲ ያጎደላቸውንና መደመር የሞላቸውን በመያዝ ልዩነቱን ለማሳየት ያህል የመደመር ሐሳብ ያለፈውን በጎ ነገር በማስቀጠል ስህተቶችን ያለማወላወል በማረም ለመጪው ትውልድ ጥቅምና ፍላጎት አሟልቶ አቅርቧል።

ምንጭ አዲስ ዘመን ታህሳስ 7 ቀን 2012 ዓ.ም

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top