Connect with us

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሚዲያውን ከመሸሽ ውጪ ምን አማራጭ አለው?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሚዲያውን ከመሸሽ ውጪ ምን አማራጭ አለው?
Photograph: Tiksa Negeri/Reuters

ፓለቲካ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሚዲያውን ከመሸሽ ውጪ ምን አማራጭ አለው?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሚዲያውን ከመሸሽ ውጪ ምን አማራጭ አለው? (ጫሊ በላይነህ)

ማኀበራዊ ሚዲያውጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ የፊታችን ማክሰኞ የሠላም ኖቤል ሽልማቱን ሲቀበል ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት ወይንም ከጋዜጠኞች ጋር ፊት ለፊት ለመገናኘት ፍላጎት እንደሌለው መግለጹን በመጥቀስ ሲያብጠለጥሉት አያለሁ፡፡ ግን ዐብይ ይህ ከማድረግ ሌላ ምን አማራጭ አለው ብሎ የሚጠይቅ ደፋር ግን አላየሁም፡፡ እናም ከበድ ካለ ይቅርታ ጋር እውነታውን ልደፍር ነው፡፡

እስቲ አስበው?!… እሳት የላሱ የዓለም ተጽዕኖ ፈጣሪ ሚዲያ/ ጋዜጠኞች ተሰብስበው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የእንኳን ደስ አለህ እቅፍ አበባ ይዘው የሚጠብቁት ይመስልሀል? አትሞኝ፡፡ ጋዜጠኞቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይን አጥብቀው የሚፈልጉት የተቀበለውን ክብር በዘዴ ሊነጥቁት ነው፡፡ አዎ!… የሠላም ኖቤል ተሸላሚው ዐብይ በሚመራት ሀገር ሠላም መጥፋቱን እነዚህ ሚዲያዎች አሳምረው ያውቃሉ፡፡

ምንም እንኳን ብዙዎች ክስተቶች በዐብይ ፍላጎት የተፈጸሙ ባይሆኑም በሥልጣን ላይ ባሳለፋቸው 19 ወራት ኢ ሰብዓዊ ድርጊቶች ያውም ሰቅጣጭ በሀገራችን መፈጸሙን መካድ አይቻልም፡፡ የሠላም ሚኒስትር ባቋቋመች ሀገር ሠላም ብርቅ ሆኖ ከርሟል፡፡ ግለሰቦች ከሕግ በላይ ሆነው፣ ቡድን አደራጅተው በዘር፣ በጎሳ፣ በሀይማኖት ልኬት ዜጎችን ሲጨፈጭፉ ጠ/ሚኒስትር ዐብይ እርምጃ ወስዶ ነገሮች ከማስቆም ይልቅ ስለትግዕስት አስፈላጊነት ሲሰብክ እንደነበር እነዚህ ጋዜጠኞች ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ የአንድ ብሄር ተወላጆች፣ የአንድ ሀይማኖት ተከታዮች ተጠቁ ሲባል ግድያው ብሄር ብሄረሰቦችን እና ሁሉን ሀይማኖቶች ያማከለ መሆኑን ሊያሳየን የሟቾችን የብሄርና የሀይማኖት ስብጥር ይዞልን እንደመጣ እነዚህ እሳት የላሱ ጋዜጠኞች ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡

ጠ/ሚኒስትር ዐብይ የኢትዮ ኤርትራን ችግር ለመፍታት ላቡን ሲዘራ በሀገር ውስጥ ንጹሀንን በሠላም እጦት በጠራራ ጸሐይ መሞታቸውን፣ መሰደዳቸውን፣ መጠቃታቸውን፣ የእምነት ተቋማት መውደማቸውን እነዚህ እሳት የጎረሱ ጋዜጠኞች ያውቃሉ፡፡ በዐብይ አመራር ዘመን ባለሥልጣናት እርስ በርስ መገዳደላቸውን፣ እሱንም ተከትሎ ያለበቂ ማስረጃ ጅምላ እስር መፈጸሙን እነዚሁ ጋዜጠኞቹ ያውቃሉ፡፡ እናም ወዳጄ፤ ዐብይ አሕመድ የእነዚህን ትንታግ ጋዜጠኞች ጥያቄዎች በምን አቅሙ ሊመልስ የሚችል ይመስልኻል? ለእነዚህ ጋዜጠኞች ስለትግዕስት አስፈላጊነት ሰብኮ ሸውዶ ማለፍ እንደማይቻለውስ እንደምን ዘነጋኸው?

አንተም ቢሆን አትጃጃል፡፡ ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ እንዲሉ በአንድ ወቅት ኦባማ ኖቤል ሲቀበል መግለጫ አልሰጠም ነበርና ዛሬም ዐብይ አለመስጠቱ ትክክል ነው እያልክ ራስህን አታድክም፡፡ የዐብይ የሚዲያ ሽሽት መነሻው ሊመልሰው የማይችለው የጥያቄ ጎርፍ ጋዜጠኞቹ ጋር መኖሩን አስቀድሞ ማወቁ ነው፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች መቅረብ ብቻውን የሚረከበውን ትልቅ ሽልማት ዋጋ እንደሚያሳጡት አስቀድሞ መረዳቱ ነው፡፡

እናም ወዳጄ፤ እውነት… እውነት እልሃለሁ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ጋዜጠኞችን መሸሹ ትክክል የሚሆነው እንዲህ ነገሩን ጠለቅ ብለህ ስታየው ነው፡፡

ደህና ክረምልኝ፡፡

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top