የመቀሌው ጉባኤ ሀገር ማዳን ወይስ ዛሬም ሀገር የሰራውን ምኒልክን መርገም፤
ባለፈ ታሪክ ለሚቆዝም መጪው ግዜ ጨለማ ነው፡፡
****
ከሰለሞን ሃይሉ
ህወሃት ሀገር ለማዳን መቀሌ ስብሰባ ጠርታለች፡፡ የፌዴራል ዘቦች ጥሪዋን ተቀብለው የገቡ ሲሆን አንዳንዶች ደግሞ የለም የሰራሽን ስራ የማይረሳ ነውና መጀመሪያ ይቅርታ ጠይቂ ብለዋታል፡፡ የመቀሌው ስብሰባ መበተንን የሚያቀነቅን ጸረ መደመር ነው፡፡
ተሰብሳቢዎቹ አጀንዳቸው ሀገረ መንግስቱን መታደግ ይባል እንጂ መርገመ ምኒልክ ቢባል የበለጠ ተስማሚ ስም ያለው ጉባኤ ይሆናል፡፡ ምኒልክን ሃያ ሰባት አመት እረግማ በምኒልክ መንፈስ ሆቴል ድረስ የሸሸችው ፓርቲ ከአራቱም አቅጣጫ ዛሬም ምኒልክ ጠል መንፈስ መቃረም እንዳላቆመች የመቀሌው ጉባኤ ምስክር ነው፡፡
ከደቡብ የመጡት የህገ መንግስቱ ዘብ በመቀሌ ብዙዎችን አስጨብጭበዋል፡፡ ዶክተር አብይን በማብጠልጠል ምኒልክን በመርገም የጥላቻ በሽታቸውን ያሳዩት ተሰብሳቢ ካዎ ጦናን እንደ ዲሞክራሲያዊ መንግስት ቆጥረው የነገሥታት ስርዓትን ለመቃወም ምኒልክን ሲያወግዙ ተደምጠዋል፡፡
አየለ ጫሚሶን ጨምሮ በርከት ያሉ የፌዴራል ስርዓቱ ጠባቂዎች የተሰበሰቡበት ጉባኤ ዛሬም ከጥላቻ ያልወጣ ፖለቲካ ርሃብ ላይ መሆናቸውን አሳይተውናል፡፡ የምኒልክ ቤተ መንግስት መጠገን በሽታ ላይ የጣለው ፖለቲከኛ ነገ ስልጣን በሚያገኝ ያን በማፍረስ የሚጠመድ እንጂ ሀገር በመስራት የሚደክም አይሆንም፡፡
ዳግማዊ ምኒልክ ሀገር ሰርተው ሄደዋል፡፡ ወላይታው ተሰብሳቢ መቀሌ የገባው ምኒልክ በፈጠሯት ሀገር በተፈጠረ አብሮነት ተጋምዶ ነው፡፡ ያማ ባይሆን የፌዴራሊስት ሃይሉ ከጅቡቲም ከሱዳንም ጋር አብሮ በተሰበሰበ ነበር፡፡
ምኒልክ ዛሬ አብረውን የሉም፤ መንፈሳቸው ለቅኝ ግዛት የማትንበረከክ አንዲት ስልጡን ነጻ ሀገር መፍጠር ነበር፡፡ እንዲህ የሚያስቡ ሚሊዮኖች አሉ፡፡ ብዙ ሚሊዮን ምኒልካውያን፣ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ጥቁሮች ያገነኑትን ንጉስ ሲያብጠለጥሉት ቢውሉ ከክብሩ ዝቅ አያደርጉትም፡፡ ይልቁንስ አፍ ሲከፈት ጭንቅላት ሞኝ ሲሰበሰብ ደግሞ እኩይ ዓላማው ይጋለጣል፡፡ የለውጥ ሃይሉን ለመደገፍ አንድ ሺህ ምክንያቶችን ያገኘነው ከሚጠላው እና ከምንጠላው የቀድሞ ስርዓት ነው፡፡
በመቀሌ ስለ ሀገር እመክራለሁ ብሎ የከተተ ሀገር የሰራ ንጉስ ሲረግም ውሎ መበተኑ የኢትዮጵያ ዘመን እንደመጣ የጠላቶቿ ሞት እንደቀረበ ነጻ ዲሞክራሲያዊትና ብዝሃነትን የምታከብር ሀገር ለመፍጠር መንገድ ላይ እንደሆንን ማሳያ ነው፡፡