Connect with us

ለእኔ የህዳር ትልቁ ዜና …

ለእኔ የህዳር ትልቁ ዜና ...
Photo: Facebook

ባህልና ታሪክ

ለእኔ የህዳር ትልቁ ዜና …

ለእኔ የህዳር ትልቁ ዜና የአክሱም ወጣቶች የእንግዳ እግር ያሳጠበ ትህትና እና የጎንደር ወጣቶች ገበሬ ማሳ ላይ የዋሉበት የአጨዳ ውሎ ነው፡፡ | ከሄኖክ ስዩም በድሬ ቲዩብ

የግለሰብ ዜና ምኔም ነው፡፡ ስለ ግለሰብ አውርተናል፡፡ ግለሰብ አግንነን ግለሰብ ነግሶብን ኖሮብናል፡፡ ዛሬም በሰለጠነው ዓለም ከህዝብ ይልቅ የእከሌ ከእከሌ ጋር ጓደኝነት ማቋረጡ ያሳስበናል፡፡ እንዲህ ኾነን የምንፈልጋት ሀገር ከገነት እንደምትርቅ ማመን አለብን፡፡ ቅርብ ያለውን ጀግንነታችንን ማወደስ ይገባናል፡፡

የኦቦ ለማ መደመርን እንቢ ማለትም ሆነ የጠቅላዬ ደማሪነት ለእኔ አንዳች ትርፍ አይኖረውም፡፡ የእኔ ትርፍ ሰው ሲተርፍ ማየት ነው፡፡ ሰው አንድም በባህሉ አንድም በስራው ይተርፋል፡፡ በዚህ ምክንያት የህዳር ድንቅ ዜናዬ ሳጣጥመው መክረም የምሻው የአክሱም ወጣቶችን ትህትና ነው፡፡

አክሱም እንደ አባቶቹ በሚኖር ተተኪ ትውልድ ዘንድሮም ህዳርን ደምቃች፡፡ ለሺህ አመታት እንደሆነው እንግዳ እግር ስር ተንበርክኮ እንኳን ደህና መጣህ የሚል ወጣት በእኔም ትውልድ ያየንባት፣ በእኔም ትውልድ መቀጠሉን ዳግም ያረጋገጥንባት ህዳር ናት፡፡

አየህ እግር ስር የሚወድቅ ትሁት ወጣት አናት ላይ ልውጣ የሚልን መንፈስ የመስበር ሃይል አለው፡፡ እናም በአክሱም ወጣቶች ኮርቻለሁ፡፡ እንደ አምናው ዘንድሮም በቀደመው ትውልድ ዳና በመሄዳቸው ነፍሴ ደስ ተሰኝታለች፡፡ የቀደሙትን ከመሰልን የቀደመውን የሚመስል ሸጋ ዘመን ከፊታችን ይመጣል፡፡

ጽዮን በነገሠች ማግስት የጎንደር ወጣቶች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ለመፋለም ገበሬ ማሳ ላይ መዋላቸው ሌላው የምስራች ነው፡፡ የኔ ትውልድ ማጭድ ይዞ ገበሬ ጉያ መዋሉን ካላወደስን፣ እንዲህ ላለው ትውልድ አይዞህ ባይ ካልሆንን ሌላው ሁሉ ነገን የማያሳይ ፖለቲካ ነው፡፡

እኔ መጮህ የሚሻው ለሚደመጠው ድምጽ ነው፡፡ በዚያ በሚሰማው ድምጽ ሀገር ትድናለች፡፡ በዚያ በሚሰማው ድምጽ ትውልድ ምግባር ይማራል፡፡ በዚያ በሚሰማው ድምጽ የኔ ትውልድ ራሱን ከዘመኑ ፈተና ይታደጋል፡፡

የዘመኑ ፈተና የሰው አንገት ቀንጥሶ መጣል መሻት ከሆነ የኔ ትውልድ ያን ሰው እግር ስር ጎንበስ ብሎ እግር አጥቦ ድል ያደርገዋል፡፡

ይህ የታየበት ሳምንት ከዚህ የሚበልጥ ዜና የለውም፡፡ የኔ ትውልድ ፈተና ተፈጥሮም ከሆነ ከተፈጥሮ የሚጋጠም እጁ አፈር የማይጠየፍ፣ የገበሬ ኑሮ ኑሮው የሆነ ትንታግ ድል ያደርገዋል፡፡ ያን ፍልሚያ ካየንበት ከዚህ ሳምንት ከዚህ ዜና የሚበልጥ ዜና የለም፡፡ ዜናችንን ከመሻታችን ካላጣጣምነው በሚያመልጠንም አንጎዳም በሚያገኘንም አንጠቀምም፡፡

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top