Connect with us

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሀገር ውስጥ የበረራ አገልግሎቱን 30 በመቶ አሳደገ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሀገር ውስጥ የበረራ አገልግሎቱን 30 በመቶ አሳደገ
Photo: Facebook

ኢኮኖሚ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሀገር ውስጥ የበረራ አገልግሎቱን 30 በመቶ አሳደገ

ህዳር 19 ቀን 2012 ዓ.ም፣ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የሀገር ውስጥ የበረራ አገልግሎት አቅሙን 30 በመቶ በማሳደግ የአገልግሎት አሰጣጡን በይበልጥ እያጠናከረ ይገኛል።

የስካይ ትራክስ የባለ 4 ኮከብ ደረጃ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሀገር ውስጥ ተጨማሪ የበረራ መዳረሻዎችን በመክፈትና እለታዊ የበረራ ቁጥሮችን በመጨመር፣ እንዲሁም የአየር ማረፊያዎችን መሰረተ ልማት በማስፋፋትና በማዘመን፣
አዳዲስና ዘመናዊ በሆኑ አውሮፕላኖቹ የተለያዩ የአገራችንን ክፍሎች በማገናኘት የህዝብ ለህዝብ ትስስርን በማጠናከር ላይ ይገኛል።

በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በተደገፈው የደንበኞች አገልግሎት በበጀት ዓመቱ 2ነጥብ8 ሚሊየን ለሚሆኑ የሀገር ውስጥ መንገደኞች የአየር ትራንስፖርት አገልግሎትን ለመስጠት እየሰራ ይገኛል። አየር መንገዱ የመንገደኞችና የጭነት አገልግሎትን በመስጠት የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን በማሳለጥ ሀገራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል። በተጨማሪም በተመጣጣኝ ክፍያ የሚሰጠውን የበረራ አገልግሎት ወደሌሎች የአገሪቱ መዳረሻዎች ለማስፋፋት ዝግጅቱን አጠናቋል።

አቶ ተወልደ ገብረማርያም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ በሰጡት አስተያየት “አየር መንገዳችን የሀገር ውስጥ የበረራ አማራጮችን በማስፋትና በቴክኖሎጂ የታገዘ የጉዞ አገልግሎት በመስጠት በሀገራችን የቱሪዝም እድገትም ሆነ በአጠቃላይ ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ ጉልህ ሚና ይጫወታል። የቱሪስት ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር በማድረግ፣ የውጭ ምንዛሬን ሃገር ውስጥ በማስቀረትና የግብይት ዑደቶችን በማፋጠን የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት የሚኖረውን አይተኬ ፋይዳ በመረዳት አገልግሎታችንን በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረባችንን እንቀጥላለን። “ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ 22 የሀገር ውስጥና 125 ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች ያሉት ሲሆን፣ በቀን ከ51 በላይ፣ በሳምንት ደግሞ ከ350 በላይ የሀገር ውስጥ በረራዎችን በማቅረብ ደንበኞቹን በማገልገል ላይ ይገኛል። አየር መንገዱ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት አየር መንገዶች በተሻለ ደረጃ ሰፊ የሀገር ውስጥ የበረራ አገልግሎትን በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያቀርብ አለማቀፍ አየር መንገድ ነው።

 

Click to comment

More in ኢኮኖሚ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top