Connect with us

እመጓ ኡራኤል-ምስጢርም ተአምርም

እመጓ ኡራኤል-ምስጢርም ተአምርም

ባህልና ታሪክ

እመጓ ኡራኤል-ምስጢርም ተአምርም

ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም እመጓ ኡራኤል ደርሷል፡፡ ከመንዝ ሸለቆዎች ግርጌ ወደሚገኘው ታሪካዊ ስፍራ ያደረገውን ቆይታ ምስጢርም ተአምርም ሲል ቀጣዩን የጉዞ ክፍል ለዛሬ እንዲህ ያካፍለናል፡፡| ከሄኖክ ስዩም በድሬቲዩብ

ደክሞኛል፡፡ ቀና ብዬ ሰማዩን አየሁት፤ ከሰማዩ ወዲህ ያለው ኮረብታ የወረድኩበት ተራራ ነው፡፡ የማይሰለች ሩቅ መንገድ ነው፡፡ ከባድ ቢሆንም ማንም ይወርደዋል፡፡ ዓይን ቢፈራውም ልብ ይደፍረዋል፡፡ ምክንያቱ መድረሻው ቁልቁል ሲታይ ያጓጓል፡፡ የመንዝ ቤቶች ውበት፣ የተፈጥሮው ሳቢነት ልብን ያጀግናል፡፡ እንዲህ ኾኜ ደረስኩ፡፡

እመጓ ኡራኤል በጣም ጠባብ ቅጥር ውስጥ አርፏል፡፡ ግራና ቀኙ የገበሬ ማሳ ነው፡፡ ሽቦው አጥር ውቡን ህንጻ ቤተ ክርስቲያን አልከለለውም፡፡ ምን እንዳመሳሰላቸው አላውቅም እንጂ አዲሱ ህንጻ ቤተ ክርስቲያን በብዙ መልኩ ከአዲስ አበባው ኡራኤል ጋር ይመሳሰላል፡፡

አንዲት ግራር ከቤተክርስቲያኑ ቅጥር ውጪ ቆማለች፡፡ ዙሪያዋ ጠፍ ስለኾነ ጥሩ ማረፊያ ኾነችን፡፡ የቤተስኪያኑን ደጃፍ ተሳልመን ከመግባት አረፍ ማለትን መርጠናል፡፡ የመንዝ መንደር የከበባት ደብር ናት፡፡

የኡራኤል ቤተ ክርስቲያንን ህንጻ ጥቂት የጥድ ዛፎች ከበውታል፡፡ አንዷ ጥድ አንዳች ሳትነካ በእብነ በረድ የታነጸው አውደ ምህረት መካከል ላይ ዘመም ብላ ቆማለች፡፡ ህንጻው በቅርቡ የተሰራ ነው፡፡ እመጓ ኡራኤል ሲነሳ የወላይታ የልማት አርበኛው ታላቁ ሰው ደጃዝማች ወልደሰማያት አብረው ይነሳሉ፡፡ ይህንን ውብ ቤተ ክርስቲያን ያሰሩት እሳቸው መሆናቸው ተነገረኝ፡፡

እሞሃይ መጡ፡፡ እመጓ ለሚመጣ ሰው እንደ ሣራ ደግ እናት ልባቸውን ከፍተው የሚጠብቁ እናት ናቸው፡፡ በእናት ስስት ያለ እረፍት እንክብካቤ አደርገው ለተቀበሉት እንግዳ ቆላው ደጋ ይኾናል፡፡

ቀና ብዬ አየሁ፡፡ በጥዱ መካከል አሻግሮ ቆጵሮስ ታየኝ፡፡ ምስጢራዊ ተራራው ነው፡፡ አስቀድሞስ መቀመጫውን ሳይነቅል ከግራ ቀኝ እየተወነጨፈ የሚኖር አስገባሪ ዘንዶ የነበረበት ተራራ ነበር፡፡ ድርሳነ ኡራኤልን የሚጠቅሰው የስፍራው ታሪክ ይህ ዘንዶ በመልአኩ በቅዱስ ኡራኤል የተመታበት ስፍራ ሲሆን ቅዱሱ ጽዋ የተሰወረበት እንደሆነ ይታመናል፡፡

ወዲያ ካሊና ይታያል፡፡ ደብረ ካሊና እንደ ቆጵሮስ የራሱን ታሪክ ያለው አምባ ነው፡፡ እንደምን ቢሉ አስቀድሞ ፍየል የሚያኽል ጉንዳን በአናቱ ነግሶ ሀገር ያመሰበት ነበር፡፡

ያለሁት የታላቁ ምድር መንዝ የስሙ መነሻ የኾነ ከቅዱሱ ደም መነዛት በመነሳት መንዝ የሚለውን ስም ያገኘበት ምስጢራዊና ተአምራዊ ስፍራ ነው፡፡ ከድካም አርፌ ከበረታሁ ወደ ዋሻው እንወርዳለን፤ ጸበሉን አይተን ቀጭን አምባ ማርያምን እንሳለማለን፡፡

የምለውን አብልጦ ለመረዳት የደጉን ሰው ድንቅ ስራ የዶክተር አለማየሁ ዋሴን እመጓ ብታነቡት ሸጋ ነው፡፡ ኑ ወደ አብረሃም ቤት እንግባ፤ የእመጓ እናት የአብረሃም ቤት ባለቤት የኔ ዘመን ሳራ ናቸው፡፡

ወደ እመጓ መሄድ ራሱ የመድረስን ያኽል ነው፤
በመንዝ ማማዎች አናት፤
****
ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ወደ ታሪካዊቷ እመጓ ያደረገውን ጉዞ እየተረክልን ነው፡፡ ከሞላ እስከ እመጓ ያለውን የጉዞ ምዕራፍ የመድረስን ያኽል ረካሁበት ሲል እንዲህ ተርኮታል፡፡ | ከሄኖክ ስዩም በድሬ ቲዩብ

የመንዝ ኮረብታዎች አናት ነኝ፡፡ ወዲያ ማዶ የዘብርን አድማስ አየዋለሁ፡፡ ቀያ ማርያም ባሻጋሪ ናት፡፡ ከፍታማው ስፍራ ግራና ቀኙ ሩቅ ገደል ነው፡፡ በዚህ አናት ላይ መሄድ በገመድ በተዘረጋ የፈረንጆቹ መንሸራሸሪያ ከመጓዝ የሚበልጥ ሀሴትን ያጭራል፡፡
ወደ እመጓ ቆላው እየወርድሁ ነው፡፡ ለመውረድ በሚወጣበት ቀጭን መንገድ ላይ ነኝ፡፡ እየተሰማኝ ያለውን ስሜት ለመግለጽ እቸገራለሁ፡፡ መንዝ የተባረከ ምድር ነው፡፡ ዓይኖቼ ቁልቁል ቆላው ሜዳ ከተንጠባጠቡት ቅንጡ ሎጂ መሳይ የመንዝ ገበሬ ቤት አልተነቀሉም፡፡ እማየውን እስካሳያችሁ ቸኩያለሁ፡፡

ቀጭን መተላለፊያዎች ያሉዋቸው ሦስት ኮረብታዎች ወደ እመጓ ለመግባት ጠባብ በሮች ናቸው፡፡ ዙሪያው በምድር ጠረጴዛ ተከቧል፡፡ ቁልቁል ወደ ሚታየኝ ምድር እንደምጓዝ ቢነገረኝም አልራቀብኝም፡፡ እመጓ ምስጢራዊ ስፍራ ናት፡፡ ወደምስጢራዊቷ ስፍራ ለሚጓዝ ሰው በምድር የማይከብድ መንገድ ቢኖር ይሄ ገደል አፋፍ በቀጭኑ የተዘረጋ ጎዳና ነው፡፡

ዓይን ስስታም ነው፡፡ የኔ ደግሞ ሆዳም ሆኖ አስቸገረኝ፡፡ የቱን አይቶ የቱ ጋ አደብ ይግዛ፤ ተንቀዠቀዠ፡፡ አንዴ እዚያ ሌላ ግዜ እዚህ ወረወርኩት፡፡ ጥልቅ ገደል ባፈጠጠበት ጠባብ ጎዳና ብጓዝም የምመለከተው ማዶውን ነው፡፡ ማዶ ተአምር አለው፡፡ ማዶ ድንቅ ሸለቆ ነው፡፡ ማዶው የመንዝ ገጠር ቤቶች በፈጠሩት መንደር የተዋበ ሩቅ ነው፡፡

የመጨረሻዋን ቁልቁለት ስወርድ መድረስ ሳያስፈልግ መርካት በሚቻልበት የእመጓ ቆላ ተፈጥሮ ተሸንፌ ነበር፡፡ የለሁም፡፡ በተፈጥሮው ውበት በመልካዓ ምድሩ አፈጣጠር፣ በሰው ልጅ እንዲህ ባሉ ስፍራዎች የመኖር ጥበብ እጅ የሰጠሁ ምርኮኛ ሆኛለሁ፡፡

የእመጓ ኡራኤል ደብር ዛፎች መታየት ጀመሩ፡፡ ቆጵሮስና ከሊና ከነ ሞገሳቸው ስቀርብ ይገዝፉ ጀመር፡፡ ቀጭን አምባ ማርያም መሸሸግ ጀመረች፡፡ ቁልቁል ያየሁበትን ተራራ ሽቅብ አየሁት፡፡ ርቀታችን ወደ እመጓ መቅረቤን ነገረኝ፡፡

የድንጋይ ኮረት በተነጠፈበት ጠባብ ተዳፋታማ መንገድ ጉዞው ቀጠለ፤ ግራና ቀኝ የስንዴ ማሳ ተኝቷል፡፡ የደረሰው ሰብል አቧራ መልክ አለው፡፡ የሚያጭድ ገበሬ እንጉርጉሮ ይሰማኝ ጀመረ፡፡ በእጽዋት የተሸፈነው ደብር ጉልላቱ ታየኝ፡፡ እመጓ ኡራኤል ነው፡፡

===

እመጓን ፍለጋ፤ ሞላሌ የመንዝ ማማዎች ጌጥ

ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ታሪካዊቷን የእመጓ ቤተ ክርስቲያን ፍለጋ ወደ መንዝ ወርጃለሁ ይለናል፡፡ በመንዝ ማማ ዋና ከተማ በሞላሌ ያደረገውን ቆይታ የትረካው መጀመሪያ አድርጎታል፡፡ | ከሄኖክ ስዩም በድሬቲዩብ

ይበርዳል ግን ደግሞ እንደ መሀል ሜዳ አይደለም፡፡ ከአምስቱ መንዞች አንዷ በኾነችው ማማ ምድር ነኝ፡፡ የመንዝ ስም ምድርን ያስከትላል፡፡ ማማ ምድር፣ ጌራ ምድር፣ ቀያ ምድር፣ ላሎ ምድር፤ መንዝ ግሼ ከአምስቱ መንዞች በቁጥር አንዷ ናት፡፡ ሞላሌ ሰው አታጣም፡፡ ዘብር ገብርኤልን ብሎ የመጣ ሲመጣም ሲሄድም ያርፍባታል፡፡ መንገዷ ዛሬም አበሳ ነው፡፡ ከተማዋ ግን እየሞቀች ነው፡፡ እዚህም እዚያም ፎቅ ይታያል፡፡

እነኚህን ፎቆች ያበዙላት ዘንድ ተመኘሁ፡፡ ሰው ፎጣ ለብሷል፡፡ ከንፈር የሚሰነጥቀው ብርድ ጥቅምት ይብሳል፡፡ ዙሪያው በቀደሙ ገዳማት የታጠረ ነው፡፡ መንዝ መንዛት ከሚለው የመጣ ነው፡፡ ቃሉ ከክርስቶስ ደም መረጨት ጋር ይገናኛል፡፡ የታላላቆቹ ገዳማት መገኛ ነው፡፡ እዚህ ሁለትና ሦስት መቶ ዓመት እድሜ ማስቆጠር ከቀደሙት አያስቆጥርም እዚህ ብዙ መቶዎችን መኖር ብርቅ አይደለም፡፡ እመጓን ፍለጋ ነው የመጣሁት፡፡

እመጓን ፍለጋ የመጣ ሞላሌ አድሮ መሄድ ግድ ይለዋል፡፡ ሞላሌ ያደረ ደግሞ የማማዎችን ጌጥ የስስታቸውን ከተማ እንደልቡ ያያታል፡፡ ፍስክ የደረሰ ሁሉ ነገር ቀላል ነው፡፡ ያን ጦስኝ የበላ በግ በግላጭ ለማግኘት ይረዳል፡፡ መንዞች እምነት አጥባቂ ናቸው፡፡ በፆም ያን በግ ልቅመስ ብሎ መመኘት ሞኝነት ነው፡፡

እዚህ እምነት በአፍ ብቻ ሳይኾን በተግባርም ከፍ ብሏል፡፡ ቤቶቻቸው ደስ ይላሉ፡፡ የመንዝ ባህላዊ መንደሮችን ያየ ሞላሌ ሲደርስ ለምን ያ የጎጆ አሻራ ዘምኖ አላየውም ሲል ይቆጫል፡፡ ሞላሌ አዲስ አበባንና ደብረ ብርሃንን ለመመስል የምትመኝ ከተማ ስለሆነች የባህላዊ ቤታቸው አሻራ አይታይባትም፡፡ እኔ ግን እመክራታለሁ ራስን እየመሰሉ መዘመን፣ የራስ ጥበብን ማግዘፍ፣ የራስ ዲዛይንን ከፍ ማድረግ ስልጣኔ እንደሆነ፡፡ ሊቀ ካህናት ኢሳያስ የወረዳው ቤተ ክህነት የሥራ ኃላፊ ናቸው፡፡ ቀጠሯቸውን አክብረው መጡ፡፡ የቆምኩት ሀረር ሆቴል የሚል ጽሑፍ ያለበት የሞላሌ ከተማ ጎዳና ላይ ነው፡፡ ጉዞ ወደ እመጓ ይቀጥላል፡፡

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top