የታንክስጊቪንግ ምክር ለአሜሪካውያን ተሰጠ
“ሆን ብላችሁ…” ሂዱ!
(ደረጄ ደስታ)
[ዛሬ] ሐሙስ እዚህ አሜሪካ በዓል ነው። ታንክስጊቪንግ (የምስጋና ቀን እንደማለት) ነው። ከሌሎች በዓላት በተለየ መልኩ ወዳጅ ቤተሰብ ከያለበት ስቴት ተሰባስቦ በአንድ ቤተሰብ ጋባዥነት እያወጋ ይመገባል። እንደመተሳሰቢያም ነው። ኢትዮጵያውያንም እንደ አገሩ ነውና እንዲሁ ይገናኛሉ። ናፍቆት በዓይን ጨዋታ በጆሮ ምግብ በአፍ ይገባሉ። ደስ ይላል። ታዲያ ሰሞኑን አንድ ሁለት የአሜሪካውያን ሬዲዮ ላይ የተደጋገመ ፕሮግራም ሰማሁ።
መጀመሪያ ጥቂት እማይባሉ አሜሪካውያን ወደ ዘንድሮው በዓል እንደማይሄዱና ከጥቂት ጊዜ ወዲህ እየጨመረ የመጣ ልማድ መሆኑን ተነገረ። ምክንያቱም እየተካረረ በመጣው ፖለቲካ (በትራምፕ እና ፀረ ትራምፕ) ብዙዎች መግባባት ቀርቶ መነጋገር እንኳ እሚችሉ ሆነው አልተገኙም። ቤተሰብ ሳይቀር የተካፋፈለበት፣ ክፉ የተነጋገረበት ፖለቲካ ከሆነ ቆየ። በአሜሪካ ባለቤቱ ፈቅዶ እስካላወራ ድረስ የፖለቲካና ሃይማኖት አቋምና እምነትን መጠየቅ እንደነውር እሚታይ ሆኖ ቆይቷል።
ዛሬ ዛሬ ግን የተቀሰቀሰው ቁጣ እማይደብቁት እየሆነ ሰው ሳይጠየቅ አቋሙን እየገለጸ ነው። ለፕሬዚዳንት ትራንፕ ያላቸውን ፍቅር ዓለም እንዲያውቅላቸው በሚፈልጉ ደጋፊዎች እና እንደ ትራምፕ ያለ ቆሻሻና ትንሽ ሰው መደገፍ ቀርቶ ስሙን እንኳ ማንሳት እንዴት እንደማይቀፋቸው በሚያስቡ ሰዎች መካከል፣ ያለው ፍጥጫ አገሪቱን ለሁለት የከፈለ መሆኑ እየታየ ይመስላል።
ይህን የተገነዘቡ ሰዎች፣ በተለይ የስነልቡና ባለሙያዎች ሬዲዮ ላይ ቀርበው ፣ በዘንድሮው በዓል ላይ ለሚገናኙ ወዳጅ ቤተሰቦች ምክር ሰጥተዋል። በዓሉን በሰላምና በደስታ ለማሳለፍ የማንንም ስሜት ሳይጎዱና እነሱም ሳይጎዱ ማድረግ ስላለባቸው ጥንቃቄ መክረዋል። ፍሬ ነገሩ እሚከተለው ነው።
ከዚህ ውስጥ ዋነኛው ወደ ግብዣው በምትሄዱበት ጊዜ “ሆን ብላችሁ” ከሚያጋጭ ንግግርና ክርክር ለመራቅ ወስናችሁ ሂዱ። እንድትናገሩ የተገደዳችሁ ከሆነ ደግሞ የሌላውን ሰው ስሜት በማይጎዳ መንገድ በአክብሮት ለማድረግ ሞክሩ። ሀሳቤን በነጻነትና ግልጽነት የመግለጽ መብት አለኝ ከሚል አጓጉል እልህ ተጠንቀቁ። በተለይ እምትለውጡት አስተሳሰብ ከሌለ ትርፉ ጸብና ራሳችሁንና ሌላውንም ከብስጭት የሚጥል ይሆናል። ከአቅማችሁ በላይ ሆኖ ዝምታው ካቃታችሁ ፈቀቅ ለማለት ሞክሩ።
የሰዎችን አቋምና አስተያየት አክብሩ። የራሳችሁንም ረጋ ባለ ትህትናና አክብሮት ግለጹ። ልብ አድርጉ ወደ ዘንድሮው በዓል ስትሄዱ “ሆን ብላችሁ” ግጭት አስወግዳችሁ በጥሩ መንፈስ መመለስን አቅዳችሁ ሂዱ። አባቶች “ምሳሌ ስጠኝ እንጂ ምሳሌ አታድርገኝ” ይላሉ። ጥሩ ምክር አይደለች?! መልካም በዓል!