Connect with us

ኦነግ ለሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች የአብረን እንስራ ጥሪ አቀረበ

ኦነግ ለሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች የአብረን እንስራ ጥሪ አቀረበ
Photo: Facebook

ፓለቲካ

ኦነግ ለሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች የአብረን እንስራ ጥሪ አቀረበ

– በይቅርታና በእርቅ ስም፣ ኣልያም የአብሮነትን ጥቅም መስበክና ማወደስን በመሳሰሉት ብቻ ያ የሚፈለገዉ እርቅ አያመጣም፣

– የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ችግር ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የፖለቲካ ኃይሎች ሁሉ ቁጭ ብለው በመነጋገር፣ መስማማትና መረዳዳት አለባቸው፣(ሙሉ መግለጫው እነሆ)

የመልካም ግንኙነት ጥሪ ለሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች !

(የኦነግ መግለጫ – ኅዳር 16 ቀን 2012 ዓ.ም.)

ወቅታዊዉ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ችግር ከመቼዉም ጊዜ ይበልጥ ገዝፎና አስጊ ሆኖ ይታያል። ባሁኑ ወቅት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት (ዩኒቨርሲቲዎች) እና ዓብያተ-አምልኮ ሳይቀሩ በመጠቀም ችግሩን ይበልጥ በማስፋፋት ወደ ሕዝቦች ግጭት ለመቀየር ሲሞከርም እየታየ ነዉ። እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት ሲበዛ አሳዛኝ ነዉ። ይህ ዓይነቱ አካሄድ ኢትዮጵያ ከተመሠረተችበት የተለያዩ አመለካከቶችን አጣምሮ ማስተናገድ ከማይችል ፀረ-ዴሞክራሲ የፖለቲካ ባህል የሚመነጭ መሆኑ የታወቀ ነዉ። በሕዝቦች ትግልና መስዋዕትነት የተጀመረዉን የለዉጥ ጅማሮ ደግፎ የለዉጡም አካል ሆኖ ለማስቀጠል ቃል ገብቶ ሥልጣኑን የተረከበዉ የዶ/ር ዐቢይ አህመድ አስተዳደር እየታዩ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት እያከናወናቸዉ ያለ ሥራዎች እንዳሉ ሆኖ፣ የተለያየ አመለካከት ያላቸዉ የፖለቲካ ኃይሎችም በመልካም ግንኙነትና በመደማመጥ ለሀገርና ለሕዝቦች ሰላም ስባል መወያየትና በሚቻላቸዉ ላይ በመተጋገዝ መንቀሳቀስ ወሳኝ ነዉ ብለን እናምናለን።

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ክፍለ-ዘመን ያስቆጠረዉ ይህ ውስብስብ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግር በሁሉም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ኃይሎች ተሳትፎ (All Inclusive) ካልሆነ በስተቀር ዘላቂ መፍትሄ እንደማያገኝ ያምናል። መፍትሄ ብሎ ያመነዉን ይህን ሁሉን አሳታፊ ጥረት ተግባራዊ ለማድረግም ከለዉጡ ዋዜማ ጀምሮ በይፋ ከብዙ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ኃይሎች ጋራ በትብብር ልሰራበት ከፍተኛ ጥረት ስያደርግ ቆይቷል።

ባሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ኃይሎች መካካል የሚታዩ የፖለቲካ አመለካከት ልዩነቶች እስከ ዛሬ በኢትዮጵያ በተለመደዉ መልኩ አንዱ ወገን ሌላዉን በኃይል ደፍጥጦና አፍኖ እልባት ያገኛል ብሎ ማሰብ ከከንቱ ህልምና ምኞት የሚያልፍ አይመስለንም። በሌላ በኩልም በቃላቶች ድለላና የተስፋ ዳቦ ብቻ፣ በይቅርታና በእርቅ ስም፣ ኣልያም የአብሮነትን ጥቅም መስበክና ማወደስን በመሳሰሉት ብቻ ያ የሚፈለገዉ እርቅ፣ የሕዝቦች ነፃነትና አብሮነት፣ ዴሞክራሲ፣ ዘላቂ ሰላምና ዕድገት ይመጣል ብሎ መመኘት ከምኞት ያልፋል ብሎ ማመኑም ይከብዳል።

ስለዚህ፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ችግር ዘላቂ ሰላም የሚያገኘዉ ያሉት የፖለቲካ ኃይሎች ሁሉ ችግሩን በተመለከተ ቁጭ ብሎ በመነጋገር እና በመወያየት ባለፉት ታሪኮች ላይ፣ ዛሬ ባለንበት ነባራዊ ሁኔታዎች ላይ፣ እንዲሁም ስለ ወደፊቱ መስማማት፣ መረዳዳትንና መተማመንን በመካከላቸዉ በመፍጠር ብቻ ሆኖ ይታየናል።

በመሆኑም፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር በበኩሉ በዚህች ሀገር የወደፊቱ የፖለቲካ ሂደት ዉስጥ የሕዝቦች ነፃነት፣ እዉነተኛ ዴሞክራሲ፣ ዘላቂ ሰላም እና ዕድገትን እዉን ለማድረግ ይረዳ ዘንድ ካሉት የፖለቲካ ድርጅቶችና ኃይሎች ሁሉ ጋር (የትኛዉንም ባላገለለ መልኩ) በመነጋገርና በመወያየት በሚያግባቡን ጉዳዮች ላይ በመተማመን አብረን እየሰራን ያሉንን ልዩነቶች ከመሠረታቸዉ እያጠበብን በመሄድ ለችግሮቻችን የተሟላ መፍትሄ ለማፈላለግ ዝግጁ መሆኑን ያረጋግጣል። ለዚህም ሲባል ለሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች መልካም ግንኙነትን በመካከላችን ማስፈን ቀዳሚ ዓላማዉ ያደረገ የትግል ጥሪ ያቀርባል። ለጥሪያችን መልስ ለመስጠት በፊንፊኔ/አድስ አበባ አራዳ ክፍለ-ከተማ በጉለሌ በሚገኘዉ ዋና ጽ/ቤታችን በኩል እንዲታገኙን ከዚሁ ጋር እናሳዉቃለን።

ድል ለሰፊዉ ሕዝብ !

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር

ኅዳር 16 2012 ዓ.ም.

Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top