Connect with us

የጥላቻና የሐሰተኛ መረጃ ረቂቅ ሕጉ መጣልን ወይስ መጣብን?

የጥላቻና የሐሰተኛ መረጃ ረቂቅ ሕጉ መጣልን ወይስ መጣብን?
Photo: University of Oxford

ህግና ስርዓት

የጥላቻና የሐሰተኛ መረጃ ረቂቅ ሕጉ መጣልን ወይስ መጣብን?

የጥላቻና የሐሰተኛ መረጃ ረቂቅ ሕጉ መጣልን ወይስ መጣብን?
(ጫሊ በላይነህ በድሬቲዩብ)

የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመቆጣጠር የወጣ ረቂቅ አዋጅ እነሆ ፓርላማ ደርሷል፡፡ በቅርቡም እንደሚጸድቅ ይጠበቃል፡፡ ረቂቁን ሳየው አንዳንድ ወሳኝ ጥያቄዎችን አጭሮብኛል፡፡ ከዚያ በፊት አዋጁ የሚያተኩርባቸው “የጥላቻ ንግግር” እና “ሐሰተኛ መረጃ” የሚሉ ቃላትን ምንነት እንመልከት፡፡ “ንግግር” የሚለው ቃል እንዲሁ መታየት ይኖርበታል፡፡

በረቂቅ አዋጁ ትንታኔ መሠረት “ንግግር” ማለት በቃል፣ በጽሑፍ፣ በምሥልና ሥዕል፣ በቅርጻ ቅርጽ እና በሌሎች ተመሳሳይ መንገዶች መልዕክትን የማሰራጨት ተግባር ነዉ፡፡ እንግዲህ ንግግር ውስጥ ጣት መቀሰር ጭምር በጥላቻ ንግግርነት ሊያስጠይቅ እንደሚችል ስናስብ የሕጉን ጥብቅነት እንረዳለን፡፡

“የጥላቻ ንግግር” ን በተመለከተ ረቂቁ እንዲህ ይፈታዋል፡፡ የጥላቻ ንግግር ማለት የሌላን ሰዉ፤ የተወሰነ ማህበረሰብን ብሄርን፤ ሀይማኖትን፤ ጾታን ወይም አካል ጉዳተኝነትን መሰረት በማድረግ ጥላቻን፣ መድሎን ወይም ጥቃትን የሚያበረታታ ንግግር ነው።
“ሐስተኛ መረጃ” ውሸት የሆነና የመረጃውን ውሸት መሆኑን በሚያውቅ ወይም የመረጃውን ውሽት መሆን ማወቅ በሚገባው ሰው የሚሰራጭ ሁከት ወይም ግጭት የማስነሳት፣ ወይም ጥቃት እንዲደርስ የማድረግ እድሉ ከፍ ያለ ንግግር ነው።

ከአዋጁ ዓላማዎች መካከል ሰዎች ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብታቸውን ተግባራዊ ሲያደርጉ ሰብዓዊ ክብርን፣ የሌሎችን ደህንነትና ሠላም አደጋ ላይ ከሚጥል ንግግር እንዲቆጠቡ ማስቻል የሚለው በእኔ ዕይታ ትክክለኛ ነው፡፡ ግን ችግሩ የሌሎችን መብት በማስከበር ስም ሐሳብን በነጻ የመግለጽ ነጻነት ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ አፈና እንዳይኖር ማስቻል ላይ ነው፡፡
ሕጉ ሊተገበር የታሰበው በየትኞቹ ሚዲያዎች ላይ ነው ሲባል በረቂቅ ሕጉ በብሮድካስት፣ በህትመት ወይም በማህበራዊ ሚድያ መሆኑን ተቀምጦ እናገኛለን፡፡

ከአዋጁ አንቀጾች መካከል እንደጉድለት ከሚነሱት አንዱ በተለይ ማህበራዊ ሚዲያው የሚመራበት ራሱን የቻለ ሕግ ሳይኖረው የቁጥጥር ሕጉ መቅደሙ ከፈረሱ ጋሪውን የማስቀደም ያህል ሆኖ ታይቶኛል፡፡ መጀመሪያ ማህበራዊ ሚዲያው የሚመራበት ሕግ መኖር ነበረበት፡፡ ይህ ሕግ ባለመኖሩ መዝግቦ፣ የህግ እውቅና ሰጥቶ የሚንቀሳቀስ ማህበራዊ ሚዲያ መፍጠር አልተቻለም፡፡

በአሁን ሰዓት በሀገር ውስጥ ያሉትም ሕጉ ባለመኖሩ ምክንያት እየተመዘገቡ ያሉት ተያያዥነት ባላቸው እንደፕሬስ ፣ የማስታወቂያ እና የፕሮሞሽን ፈቃዶችን በመያዝ ነው፡፡ እናም መንግሥት የማያውቃቸውን ወይንም ያልመዘገባቸውን የማህበራዊ ሚዲያዎች ለመቆጣጠር መነሳቱ አስገራሚ የሚያደርገው ለዚህ ነው፡፡

ሌላው በረቂቅ አዋጁ ትኩረት ከሚስቡ ጉዳዮች አንዱ ተከታዩ አንቀጽ ይመስለኛል፡፡ “…በዚህ አዋጅ…የተከለከለ ተግባር የፈጸመው ሰው ድርጊቱን የፈጸመው ከአምስት ሺ በላይ ተከታይ ባለው የማህበራዊ ሚድያ ገጽ ከሆነ ወይም በብሮድካስት አገልግሎት ወይም በየጊዜው በሚወጣ የህትመት ውጤት ከሆነ ሶስት አመት በሚደርስ በቀላል እስራት ወይም ከብር 100,000 ባልበለጠ መቀጮ ይቀጣል፡፡…”ይላል፡፡ ይህ አንቀጽ ከአምስት ሺ በላይ ተከታይ ያላቸው የማህበራዊ ድረገጾች ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ የሚል ግንዛቤን መነሻ ያደረገ ይመስለኛል፡፡ ግን የማህበራዊ ሚዲያ አሰራርን ጠንቅቆ ለሚያውቅ ሰው ይህ አረዳድ በጣም የተሳሳተ ነው፡፡ አንድ መቶም ይሁን አንድ ሺ ተከታይ ያለው የማህበራዊ ድረገጽ ተከታይ ሆን ብሎም ይሁን ባለማወቅ በብዙ ሚሊየን ወገኖች ላይ ጉዳት የሚያደርስ መረጃ በሽርፍራፊ ደቂቃዎች ውስጥ ለመልቀቅ ምንም የሚከለክለው ነገር አይኖርም፡፡

ይህን አባባል ትንሽ እናፍታታው፡፡ አንድ ሰው አንድ መቶ የፌስቡክ ተከታይ አለው እንበል፡፡ አንድ መረጃ ወይንም የጥላቻ ንግግር ለፌስቡክ ኩባንያ በመክፈል (ቡስት በማድረግ) ለሚሊዮኖች እንዲዳረስ ማድረግ ይችላል፡፡ በተለይ ዓለም አቀፍ የባንክ ሒሳብ (አካውንት) ያላቸው ይህ ዓይነቱ አሰራር በጣም የሚቀላቸው መሆኑም የሚታወቅ ነው፡፡ ለዚህም ነው፤ አዋጁ ከአምስት ሺ በላይ የማህበራዊ ድረገጽ ያላቸው ሰዎች ለየት ባለ መልኩ ከባድ ጉዳት እንደሚያደርሱ አስቦ መነሳቱ አለማወቅ የሚሆነው፡፡

ሌላውና ትልቁ ነገር ይህን የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃ የሚለቁ በርካታ ቁጥር ያላቸው ወገኖች በብዕር ስም እና በውሸት ፎቶግራፍ የሚገኙ እንዲሁም ነዋሪነታቸውም በውጪ ሀገር የመሆናቸው ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች ለሚያሰራጩት የጥላቻና የሐሰተኛ መረጃ በምን መልኩ ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ የሚለው ረቂቅ አዋጁ አይመልሰውም፡፡ ይህ ሲታሰብ ደግሞ በሀገር ውስጥ ያሉትን ወገኖች ጸጥ ለማሰኘት አቅም ያለው ሕግ ሆኖ እንዳይቀር ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባል፡፡

ዋናው ነገር እንደፌስቡክ ያሉ ማህበራዊ ድረገጾች የተመሰረቱበት ዋንኛ ዓላማ የሰዎችን የመረጃ ጥማት ለማርካት ነው፡፡ ኩባንያዎቹ ሀሳብን በነጻ ለመግለጽ ነጻነት ትልቅ ዋጋ የሚሰጡ ናቸው፡፡ እንዲህ ዓይነት ገዳቢ ሕጎች በእነሱ ዘንድ እንደምን ይታያል የሚለውም ወሳኝ ጥያቄ ይሆናል፡፡ መንግሥት ገዳቢ ሕግ ለማውጣት ከሚጣደፍ ይልቅ የጥላቻና የሐሰተኛ መረጃን በተመለከተ ከእነዚህ ዓለምአቀፍ ኩባንያዎች ጋር ተባብሮ ቢሰራ ይበልጥ አትራፊ ይሆናል፡፡

ሌላውና መዘንጋት የሌለበት ትልቁ ቁምነገር ቢኖር፤ የጥላቻ ንግግር በማሰራጨት ረገድ መንግሥት እና በመንግሥት ውስጥ የተሰገሰጉ አንዳንድ ባለሥልጣናት ያላቸው ሚና አሳንሶ ማየት ተገቢ አለመሆኑን ነው፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት ህወሓት መራሹ ኢህአዴግ “ጠላቴ” ያላቸውን ሁሉ በጅምላ ሲፈርጅ፣ ሲያጥላላ መክረሙ አይረሳም፡፡ በሕግ የፖለቲካ ድርጅት መስርተው፣ ሕግና ሥርዐት አክብረው የሚቃወሙትን ወገኖች ሳይቀር በጅምላ “ነፍጠኛ፣ አክራሪ፣ ግንቦት ሰባት፣ የሻዕቢያ ተላላኪ፣ ኦነግ…” እያለ ሲያጥላላና ሲያሸማቅቅ መኖሩ ስናስታውስ የጥላቻ ንግግር መሠረቱ የት እንደነበር ቁልጭ ብሎ ይታየናል፡፡ ዛሬም ይህ ክፉ ደዌ ያለቀቃቸው ሹማምንት ወይንም አመራሮች በኢህአዴግ ውስጥ ፈልጎ ማግኘት ያን ያህል አስቸጋሪ አይደለም፡፡ እናም መንግሥት ሕጉን ለማስከበር ከመንቀሳቀሱ በፊት ሕግና ሥርዓትን ማክበሩን ወይንም የሚያከብሩ ሹማምንት በየደረጃው መያዙን እርግጠኛ ሊሆንም ይገባል፡፡

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top