Connect with us

ዶ/ር ደብረፅዮን የብልፅግና ፓርቲ ውሁድ ሳይሆን አዲስ ፓርቲ ነው አሉ

ዶ/ር ደብረፅዮን የብልፅግና ፓርቲ ውሁድ ሳይሆን አዲስ ፓርቲ ነው አሉ
Photo: Facebook

ፓለቲካ

ዶ/ር ደብረፅዮን የብልፅግና ፓርቲ ውሁድ ሳይሆን አዲስ ፓርቲ ነው አሉ

ዶ/ር ደብረፅዮን የብልፅግና ፓርቲ ውሁድ ሳይሆን አዲስ ፓርቲ ነው አሉ

(ትላንት ከሰጡት መግለጫ በከፊል እንደሚከተለው ቀርቧል)

“ወደ ኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ስንጠራ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ለመነጋገር ተብለን ነው የተጠራነው፡፡ ግን ያ ሳይሆን ቀርቶ እንወሃድ የሚል አጀንዳ ቀረበ፡፡ እዛ የተሳተፍን የህወሓት አመራሮች አሁን ባለንበት አገራዊ ወቅታዊ ሁኔታ ስለውህደት አይደለም መነጋገር ያለብን፡፡ ስለ ሰላም፣ ስለ አጠቃላይ አገራዊ ደህንነት፣ ስለ ህገ መንግስት መጣስ፣ ስለ ዜጎች መፈናቀል፣ ስለ ንሮ ውድነት ቅድሚያ ሰጥተን እንነጋገር የሚል ሀሳብ አቀረብን፡፡ ለዚሁ አልተዘጋጀንም፣ ሪፖርት የለንም፤ አሉን፡፡ ሪፖርት ብዙም የሚያስፈልገው ነገር አይደለም፤ ሁላችንም እዚሁ ስላለን፣ የማናውቀው ጉዳይም ስሌለ ተነጋግረን መፍትሄ ማስቀመጥ እንችላለን፤ ውህደት አጣዳፊ ጉዳይ አይደለም የሚል ሀሳብ አቀረብን፡፡

ይህ በምንልበት ጊዜ አይ የውህደት አጀንዳ ነው የምናየው አሉ፡፡ ስለዚ ገና ከአጀንዳው ጀምረን ነው ሰፊ የመከራከርያ ሀሳብ ያቀረብነው፡፡ አጀንዳው በአብላጫ ድምፅ ሲያፀድቁት ጀምረን እዛ የነበርን ስምንት የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ አባላት ተቃውመናል፡፡ የአብላጫ ደምፁን ውሳኔ አክብረን ወደ ውይይቱ ገባን፡፡ ስለ ውህደቱ በምንነጋገርበት ጊዜ በድፍኑ እንወሃድ ነው ያሉን፡፡ የምንወሃድበት ሀሳብ ምንድነው? እስከዛሬ ስንመራበት በነበርነው ፕሮግራም፣ ህግ ደንብ ነው ወይ የምንወሃደው የሚል ሀሳብ ስናቀርብ፣ አይ አሁን ዝምብላችሁ ተወሃዱና በኅላ እንነግራችኅለን አሉን፡፡ ሳናይ፣ በግልፅ ሳንነጋገር ዝምብለን ልንወሃድ ማለት ነው፡፡ እንኳንና ህዝብ የሚመራ ድርጅት ለመመስረት፣ ውህደት ስትፈፅም የሆነ ውል ተዋውለህ ለመፈረም እኮ አንብብህ አይተህ ነው የምትፈርመው፡፡

ሌሎቹ ሳያዩ ነው የወሰኑት፡፡ ምክንያቱም በተለይ የኢህኤደግ አጋር ድርጅት አመራሮች አስገድደውም አስቀድመው አስፈርምዋቸው ነበረ፡፡ ስላስገደድዋቸው ልክ ናቸው ማለቴ አደለም፡፡ እኛን ሊያስገድዱን አይችሉም፡፡

ስለዚህ የህወሓት አመራር ይህንን ጭፍንና የኢህአዴግ አሰራር የጣሰ አካሄድ ነው የተቃወመው፡፡ ይህንን ለማድረግ ትንሽ የፖለቲካ ሀ ሁ ነው የሚያስፈልገው፡፡ የህዝብ አደራ የተሸከምን፣ ህዝብ የምንመራ አመራሮች እንዴት ሳናይ እንወስናለን?

ችግሩ ይሄም ብቻ አይደለም፤ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ የውህደት ውሳኔ ለማስተላለፍ ስልጣን የለውም፡፡ የኢህአዴግ ምክር ቤትም እንደዚሁ ስልጣን የለውም፡፡ የአዋሳ ጉባኤ ለምክርቤቱ ውክልና ሰጥቶታል የሚል ሀሳብ ተደጋግሞ ሲቀርብ እየሰማን ነው፡፡ የኢህአዴግ ጉባኤ በእህት ድርጅቶች እጣ ፈንታ ለመወሰን በሌለው ስልጣን ለኢህአዴግ ውክልና ሊሰጠው አይችልም፡፡ ውህደቱ ተጠንቶ ይቅረብ የሚል ውሳኔ ነው ያስተላለፈው፡፡

ይሄ አንድ ጉዳይ ሆኖ የአዋሳው የኢህአዴግ ጉባኤ የኢህአዴግ ፕሮግራም ፕሮግራማችን ነው፤ አብዮታዊ ዴሞክራሲ መመርያችን ነው ብሎ ነው የወሰነው፡፡ አሁን እያየነው እንዳለ ግን ፕሮግራሙ ተቀይረዋል፡፡ የአዋሳው ጉባኤ ውሳኔ ተጥሰዋል፡፡ በመሆኑም አሁን ተዋሃደው “ብልፅግና” የሚል ፓርቲ የመሰረቱ አካላት አዲስ ፓርቲ ነው የመሰረቱት፡፡ አዲስ ፓርቲ መመስረት መብት ነው፡፡ ግን በኢህአዴግ ስም መሆን የለበትም፡፡ በመሆኑም ይሄ አዲስ ፓርቲ ኢህአዴግን መውረስ አይልም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ የኢህአዴግን ፕሮግራም ነው የመረጠው፡፡ በመሆኑም እኛ እያልን ያለነው፣ ይሄ አካሄድ እጅግ አደገኛ ነው፡፡ አገር ያለ መንግስት የሚያስቀር ነው፡፡ ስለዚህ አንዱን መያዝ ነው ያለበት፡፡ ወይ እስከ ምርጫ ኢህአዴግ መሆን ነው፤ ወይ ስልጣን መልቀቅ ነው፡፡ እንጂ በስመ ውህደት አዲስ ፓርቲ መስርተህ አገርን መምራት አይቻልም ነው፤ እያልን ያለነው፡፡

በግልፅ አካሄዱ የኢህአዴግ አስተሳሰቦችን በማፍረስ በኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች እጣ ፈንታ፣ ራስ በራስ የመወሰንና የማስተዳደር ዕድል ለመቀማት፣ በህዝቦች ትግል የተገረሰሰውን ስርዓት ለመመለስ እየተደረገ ያለ አካሄድ ነው፡፡ የህዝቦች እኩልነት የሚነጥቅ፣ ረገጣና የበታችነትን የሚያመጣ አካሄድ ነው፡፡ የህዝቦች በእኩልነት የመኖር መብት የሚነጥቅ አካሄድ ነው፡፡ ለዚሁ አካሄድ “አንድንድ አመራር ከራሱ ሁኔታ ተነስቶ ሊቀበለው ይችል ይሆናል፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ዳግመ ጭቆና፣ ረገጣና የበታችነት ይቀበላል ብየ አላስብም፡፡ ህውሓትና የትግራይ ህዝብ ይህንን አይቀበሉም፡፡

ለዚሁ አካሄድ የህወሓት ስራ አስፈፃሚ፣ የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ በሙሉ ድምፅ ተቃውሞታል፡፡ ይሁንና አጀንዳው ህጋዊ ስርዓቱ ጠብቆ እስከ ህዝብ የሚደርስ ነው የሚሆነው፡፡ በቅርብ ጉባኤ እንጠራለን፡፡ ጉባኤው ትክክል ናችሁ የሚለን ከሆነ ወደ ውሳኔያችን የሚደመር ይሆናል፡፡ አይ ተሳስታችኃል የሚለን ከሆነም የሚፈልገው ውሳኔ የሚያሳልፍ ነው የሚሆነው፡፡

ከዚሁ በተጨማሪ ህወሓት የማእከላዊ ኮሜቴውና የአባሉ ብቻም አይደለችም፡፡ ህወሓት በትግራይ ህዝብ ትግልና መስዋእትነት የተፈጠረች ድርጅት ናት፡፡ ስለዚህም የትግራይ ህዝብም ውሳኔው የሚያሳልፍበት ነው የሚሆነው፡፡ ምክንቱም እየተደረገ ያለው ነገር የአንድ ድርጅት ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ የህዝብ እጣ ፈንታ የሚወስን አጀንዳ ነው፡፡ በቀጥታ የትግራይ ህዝብ በትግሉ፣ በልጆቹ መስዋእትነት ከተከለው ስርዓት ጋር የሚተሳሰር ውሳኔ ነው፡፡ ስለዚህ የህዝቡ ፍላጎትም የሚሰማበት ጉዳይ ነው መሆን ያለበት፡፡”

Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top