Connect with us

በመንዝ ማማዎች አናት፤ ወደ እመጓ መሄድ ራሱ የመድረስን ያኽል ነው

በመንዝ ማማዎች አናት፤ ወደ እመጓ መሄድ ራሱ የመድረስን ያኽል ነው

ባህልና ታሪክ

በመንዝ ማማዎች አናት፤ ወደ እመጓ መሄድ ራሱ የመድረስን ያኽል ነው

ወደ እመጓ መሄድ ራሱ የመድረስን ያኽል ነው፤
በመንዝ ማማዎች አናት፤
****
(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ወደ ታሪካዊቷ እመጓ ያደረገውን ጉዞ እየተረክልን ነው፡፡ ከሞላ እስከ እመጓ ያለውን የጉዞ ምዕራፍ የመድረስን ያኽል ረካሁበት ሲል እንዲህ ተርኮታል፡፡) | ከሄኖክ ስዩም በድሬቲዩብ

የመንዝ ኮረብታዎች አናት ነኝ፡፡ ወዲያ ማዶ የዘብርን አድማስ አየዋለሁ፡፡ ቀያ ማርያም ባሻጋሪ ናት፡፡ ከፍታማው ስፍራ ግራና ቀኙ ሩቅ ገደል ነው፡፡ በዚህ አናት ላይ መሄድ በገመድ በተዘረጋ የፈረንጆቹ መንሸራሸሪያ ከመጓዝ የሚበልጥ ሀሴትን ያጭራል፡፡

ወደ እመጓ ቆላው እየወርድሁ ነው፡፡ ለመውረድ በሚወጣበት ቀጭን መንገድ ላይ ነኝ፡፡ እየተሰማኝ ያለውን ስሜት ለመግለጽ እቸገራለሁ፡፡ መንዝ የተባረከ ምድር ነው፡፡ ዓይኖቼ ቁልቁል ቆላው ሜዳ ከተንጠባጠቡት ቅንጡ ሎጂ መሳይ የመንዝ ገበሬ ቤት አልተነቀሉም፡፡ እማየውን እስካሳያችሁ ቸኩያለሁ፡፡

ቀጭን መተላለፊያዎች ያሉዋቸው ሦስት ኮረብታዎች ወደ እመጓ ለመግባት ጠባብ በሮች ናቸው፡፡ ዙሪያው በምድር ጠረጴዛ ተከቧል፡፡ ቁልቁል ወደ ሚታየኝ ምድር እንደምጓዝ ቢነገረኝም አልራቀብኝም፡፡ እመጓ ምስጢራዊ ስፍራ ናት፡፡ ወደምስጢራዊቷ ስፍራ ለሚጓዝ ሰው በምድር የማይከብድ መንገድ ቢኖር ይሄ ገደል አፋፍ በቀጭኑ የተዘረጋ ጎዳና ነው፡፡

ዓይን ስስታም ነው፡፡ የኔ ደግሞ ሆዳም ሆኖ አስቸገረኝ፡፡ የቱን አይቶ የቱ ጋ አደብ ይግዛ፤ ተንቀዠቀዠ፡፡ አንዴ እዚያ ሌላ ግዜ እዚህ ወረወርኩት፡፡ ጥልቅ ገደል ባፈጠጠበት ጠባብ ጎዳና ብጓዝም የምመለከተው ማዶውን ነው፡፡ ማዶ ተአምር አለው፡፡ ማዶ ድንቅ ሸለቆ ነው፡፡ ማዶው የመንዝ ገጠር ቤቶች በፈጠሩት መንደር የተዋበ ሩቅ ነው፡፡

የመጨረሻዋን ቁልቁለት ስወርድ መድረስ ሳያስፈልግ መርካት በሚቻልበት የእመጓ ቆላ ተፈጥሮ ተሸንፌ ነበር፡፡ የለሁም፡፡ በተፈጥሮው ውበት በመልካዓ ምድሩ አፈጣጠር፣ በሰው ልጅ እንዲህ ባሉ ስፍራዎች የመኖር ጥበብ እጅ የሰጠሁ ምርኮኛ ሆኛለሁ፡፡

የእመጓ ኡራኤል ደብር ዛፎች መታየት ጀመሩ፡፡ ቆጵሮስና ከሊና ከነ ሞገሳቸው ስቀርብ ይገዝፉ ጀመር፡፡ ቀጭን አምባ ማርያም መሸሸግ ጀመረች፡፡ ቁልቁል ያየሁበትን ተራራ ሽቅብ አየሁት፡፡ ርቀታችን ወደ እመጓ መቅረቤን ነገረኝ፡፡

የድንጋይ ኮረት በተነጠፈበት ጠባብ ተዳፋታማ መንገድ ጉዞው ቀጠለ፤ ግራና ቀኝ የስንዴ ማሳ ተኝቷል፡፡ የደረሰው ሰብል አቧራ መልክ አለው፡፡ የሚያጭድ ገበሬ እንጉርጉሮ ይሰማኝ ጀመረ፡፡ በእጽዋት የተሸፈነው ደብር ጉልላቱ ታየኝ፡፡ እመጓ ኡራኤል ነው፡፡

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top