የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በከተማዋ በአገልግሎት ብዛትና በተለያዩ ምክንያቶች ለጉዳት የተዳረጉ መንገዶችን መልሶ በመጠገን እና በማደስ የተሻለ የትራፊክ እንቅስቃሴ እንዲኖር ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡
ባለስልጣኑ አሁን ላይ ከ6 ኪሎ ወደ ሚሊኒክ ሆስፒታል የሚወስደውን መንገድ የእድሳት ስራ እያከናወነ ይገኛል፡፡ ከ6 ኪሎ አደባባይ እስከ ሚሊኒክ ሆስፒታል ድረስ ያለው ነባር መንገድ በአገልግሎትና በልዩ ልዩ ምክንያቶች የተነሳ ለብልሽት በመዳረጉ አልፎ አልፎ በሲሚንቶ ኮንክሪት ጥገና ተደርጎለት መቆየቱ ይታወሳል፡፡
አሁን ላይ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ መንገዱ ለትራፊክ እንቅስቃሴ አስቸጋሪ መሆኑን በመገንዘብ ከሚሊኒክ ሆስፒታል እስከ ጃን-ሜዳ ያለውን የተበላሸ የአስፋልት መንገድ በመለየትና ቆርጦ በማንሳት የእድሳት ስራ እያከናወነ ይገኛል፡፡
ባለስልጣኑ ከቀጣይ አጭር ቀናት በኋላም ከጃን ሜዳ እስከ 6 ኪሎ አደባባይ ድረስ ያለውን ቀጣይ የመንገዱን ክፍል ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የእድሳት ስራ ያከናውናል፡፡
አጠቃላይ እድሳት የሚደረግለት የ6 ኪሎ አደባባይ ሚሊኒክ ሆስፒታል የአስፋልት መንገድ 1.3 ኪ.ሜ ርዝመት ያለው ሲሆን እስከ ህዳር 30 ድረስ ሙሉ ለሙሉ የእድሳት ስራውን ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡
ከመንገዱ እድሳት በኋላ ከ6 ኪሎ በሚሊኒክ ሆስፒታል አድጎ ወደ መገናኛና ሌሎች አካባቢዎች የሚደረገውን ጉዞ በተሻለ ደረጃ የተሳለጠ እንዲሆን ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በተያዘው በጀት ዓመት ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ 110 ኪ.ሜ የአስፋልት፣ 100 ኪ.ሜ የጠጠር፣ 50 ኪ.ሜ የኮብል መንገዶች፣ 225 ኪ.ሜ የድሬኔጅ መስመሮች፣ 30 ኪ.ሜ የእግረኛ በድምሩ 515 ኪ.ሜ መንገዶችን ለመጠገን እቅድ ይዟል፡፡ በተያዘው እቅድ መሰረትም ከሀምሌ ወር ጀምሮ እስከ ጥቅምት 30 ድረስም 16 ኪ.ሜ የሚጠጋ የአስፋልት መንገድ የጥገና ስራ አከናውኗል፡፡
ባለስልጣኑ በተለይ ከጥቅምት 1 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ የጥገና ስራ ካከናወነባቸው መንገዶች መካከል ከ6 ኪሎ – ሽሮ ሜዳ፣ ከሂልተን – ቤተ መንግስት፣ ከውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት – ቤተ መንግስት፣ ከገላን ኮንደሚኒየም ቃሊቲ ቶታል፣ ከኮካ – ኮላ መሳለሚያና ሌሎችም በርካታ አካባቢዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡
በመጨረሻም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የመንገድ ጥገና ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግና በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ እንዲያስችለው በተለያዩ አካባቢዎች ላይ በምሽትና በሌሊት የጥገና ስራ ስለሚያከናውን አሽከርካሪዎችና የትራፊክ ተቆጣጣሪዎች የተለመደውን ትብብር እንዲታደርጉ ባለስልጣኑ ጥሪውን ያቀርባል
(የአዲስአባ መንገዶች ባለስልጣን)