አንጋፋው ጋዜጠኛ፣ ደራሲና የታሪክ ተመራማሪ ጳውሎስ ኞኞ የተወለደው ከ86 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ኅዳር 11 ቀን 1926 ዓ.ም ነበር።
ጳውሎስ ከግሪካዊው መርከበኛ ኞኞና ከኢትዮጵያዊቷ ወይዘሮ ትበልጫለሽ አንዳርጌ ቁልቢ ገብርኤል አካባቢ ተወለደ። በልጅነቱ እጅግ መልከመልካም ስለነበረ እናቱ ያወጡለት የመጀመሪያ ስሙ “አማረ” የሚል ነበር። በኋላ የበኩር ስሙን በመጽሐፍ ቅዱሱ ጳውሎስ ተኩት።
ጳውሎስ ትምህርቱን የተከታተለው እስከ አራተኛ ክፍል ድረስ ብቻ ነበር። ነገር ግን በተፈጥሮ የታደለውን የማንበብ፣ የመጠየቅና የመመራመር ተሰጥኦ በሚገባ በመጠቀም ራሱን በራሱ አስተምሮ በትምህርት ገፍተው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከደረሱት በላይ ለአገርና ለወገን የሚጠቅም ስራ ማበርከት ችሏል።
በኢትዮጵያ ድምፅ ጋዜጣ፣ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እንዲሁም በኢትዮጵያ ራዲዮ ለአመታት መረጃ በመስጠት፣ በማስተማርና በማዝናናት ህዝብን በማንቃት በጋዜጠኝነት ሙያው አንቱታን አትርፏል። የመማርን ትርጉም የምስክር ወረቀትና የደመወዝ ጭማሪ ከማግኘት ጋር ብቻ አያይዘው ለሚመለከቱ ሰዎች ጳውሎስ ህያው ወቃሽ ነው። ራስን በማብቃት ህልምን ማሳካት እንደሚቻል ከጳውሎስ ህይወት መማር ይቻላል።
ጳውሎስ የታሪክ ድርሳናትን በመመርመር በርካታ የታሪክ መጽሐፍትን ጽፏል። ልቦናውን በማንቃት የጻፋቸውን የፈጠራ ጽሁፎችንም ማሳተም ችሏል። የሴቶች አምባ፣ አጤ ምኒልክ ፣ አጤ ቴዎድሮስ ፣ አስደናቂ ታሪኮች ፣ የኢትዮጵያና የጣሊያን ጦርነት፣ አራዳው ታደሰ ፣ የኔዎቹ ገረዶች ፣ የጌታቸው ሚስቶች ፣ ምስቅልቅል፣ እንቆቅልሽ ፣ ከውጭ ሀገራት የተፃፃፏቸው ደብዳቤዎች፣ አጤ ምኒልክ በሀገር ውስጥ የተፃፃፏቸው ደብዳቤዎች፣ እውቀትና ሌሎች መጽሐፍቶችን አሳትሞ ለአንባቢያን የቀረባቸው ናቸው።
ለሕትመት ከበቁት ስራዎቹ በተጨማሪም የአጤ ዮሐንስ ታሪክ፣ የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ፣ የአዲስ አበባ ታሪክ፣ የልጅ ኢያሱ ታሪክ፣ አዜብና ሰዎቹ የተሰኙ ያልታተሙት ስራዎች እንዳሉት ይነገራል።
ጳውሎስ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በፀሃፊነት ለረጅም አመታት፤ በአዘጋጅነት ደግሞ ለጥቂት ወራት ያገለገለ ሲሆን፤“ደብዳቤዎቹ” እና «አንድ ጥያቄ አለኝ” የተሰኙ አምዶችን ያዘጋጅ ነበር።
በርካቶች ጳውሎስን የሚያስታውሱት ትልቅ ተወዳጅነትንና ዝናን ባተረፈበት አንድ ጥያቄ አለኝ በሚለው የአዲስ ዘመን የጋዜጣ አምዱ ነው። ጳውሎስ ኞኞ ተወዳጅ በነበረው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የ‹‹አንድ ጥያቄ አለኝ›› አምድ የካቲት 1964 ዓ.ም እትም ላይ አንድ አንባቢ “እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ በብዛት የሌለው ስም የቱ ነው?” የሚል ጥያቄ ቀርቦለት ፣ “ኞኞ” ሲል መልሶ ነበር።
ጳውሎስ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ እየሰራ ፈለቀች ከተባለች ቆንጆ ጋር ፍቅር ሲይዘው አንድ ማህበራዊ ጉዳይ ላይ የሚያተኩር ግጥም ይጽፋል። የግጥሙ የመጀመሪያ ፊደሎች ከላይ ወደታች ሲነበቡ ፈለቀች ትወደኛለች እኔም እወዳታለሁ የሚል ዓረፍተ ነገር እንዲሰጡ በማድርግ ፍቅሩን በዘዴ እንደገለጸ ይነገራል። አጼ ኃይለስላሴ በአንድ ወቅት “ዳንስ አገርን አይገነባም” በሚል ርዕስ የጻፈውን ጽሑፍ አንብበው ደስ ስለተሰኙ 300 ብር ሸልመውታል።
እግሩ ላይ የተከሰ ተው የአጥንት ካንሰር ህመም ቀስ በቀስ ጳውሎ ስን እንዳይንቀሳቀስ አደረገው። ወዳጆቹና አድናቂዎቹ ሳይነግሩት ገንዘብ አሰባስበው ፓስፖርት አውጥተው ወደ ጀርመን ተጉዞ እንዲታከም አደረጉት። የጀርመን ህክምናውን አጠናቅቆ ከተመለሰ በኋላ ህመሙ አገርሽቶበት አላላውስ ሲለው ሼክ ሙሃመድ አሊ አል-አሙዲ አሜሪካን አገር ወስደው አሳከሙት። ጤናውን ለመመለስ ብዙዎች የደከሙት ድካም ፍሬ ሳያፈራ ግንቦት 29 ቀን 1984 ዓ.ም ይህቺን ምድር ተሰናበተ።
አለቃ ተገኝ ታምሩ ሩህ መጽሄት ቅጽ አንድ ቁጥር አራት ላይ የጳውሎስን ህልፈት አስመልክተው ተከታዩን ስንኝ ቋጥረውለታል።
… በሺ ዘጠኝ መቶ በሃያ ስድስት
በዘመነ ማርቆስ በጥቢ ወራት
የምስራቁ ኮከብ ያ ጳውሎስ ኞኞ
በህዳር አስራ አንድ ተወለደ ሰኞ
ብሩህ ኮከብ ሆኖ ለሁሉም ሲያበራ
በጥበብ ጎዳና ህዝቡን እየመራ
ታሪክ እየለየ ጣፋጭ ከመራራ
አንድ ቀን ሳይሰለች ለቁም ነገር ስራ
የጳውሎስ አይነት ጸባየ ወላንሳ
ቀድሞም አልነበረ ኋላም አይነሳ
አጣነው በድንገት በግንቦት ሰላሳ
መሬት ምን ቸገራት ብትሰጠን መልሳ።
… ውድ ጳውሎስ ኞኞ የአበሻው ፈረንጅ
የጽሑፍ የቃላት ያ የታሪክ ባለጅ
ሌይት ቀን ረፍት የለው ሁሉን ሲያዘጋጅ
የስንፍና ጠላት የስራ ወዳጅ
የድካሙን ፍሬ ትቶ ለልጅ ልጅ
በስነ ተፈጥሮ በስላሴ አዋጅ
በግንቦት ሰላሳ ፈሰሰ እንደጠጅ
ግን መሞቱ አይደለም ረፍቱ ነው እንጂ።
ምንጭ አዲስ ዘመን ረቡዕ ህዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም ዕትም ማረፊያ ዓምድ