Connect with us

ከቸልተኝነታችን እንንቃ!

ከቸልተኝነታችን እንንቃ!
Photo: YouTube

ህግና ስርዓት

ከቸልተኝነታችን እንንቃ!

ከቸልተኝነታችን እንንቃ!
(ሙሼ ሰሙ)

ከጥቂት ወራት በፊት በኢ.ቢ.ኤስ የቴሌቪዝን ጣቢያ፣ “ከተዘጋው ዶሴ” በሚል መጠርያ በሚቀርብው ፕሮግራም ላይ አንድ የወንጀል ምርመራ ስርጭት ተከታትዬ ነበር፡፡ ፕሮግራሙ ሲጠናቀቅ እውነቱን ለመናገር እንደዛ ቀን እጅግ የተሸማቀቅኩበትና ያፈርኩበት ጊዜ ኖሮ አያውቅም፡፡ ፕሮግራሙን ካየሁ በኃላ የተፈጠረብኝ ስሜት፣ እንደ ሕዝብም ሆነ እንደ ማህበረሰብ ያለ አንዳች ፍርሃት፣ ሃፍረትና ማድበስበስ እራሳችንን መገማገም እንደሚኖርብን ነዉ።

ፕሮግራሙ በአጭሩ እንዲህ ነው፡፡ ለጎረቤት በአደራ የተሰጠች አንዲት የስምንት ዓመት ልጅ እስከ አስራ አራት ዓመቷ ድረስ፣ ስምንት ዓመት ሙሉ ወደ ትምህርት በምትሔድበት ሰዓት በሰፈሩ ጎረምሶች፣ በስራ አጥ አባወራዎችና በጉልበት ሰራተኞች በተደጋጋሚ የመደፈሯ ወሬ በሰፈሩ ውስጥ በስፋት ቢናኝም ልጅቱን ሊታደጎት የሚፈልግ ሰው መጥፋቱ ሳያንስ እስከነ ጭራሹ፣ ልጅቱ ተደፍራ ሳይሆን በፍላጎት ነው የሚል ስም የማጠልሽት ተግባር ውስጥ መግባት ጀምረው ነበር። በመጨረሻ ላይም ሰቆቃውን መሸከም ያንገፈገፋቸው አንድ እናት በጉዳዩ ጣልቃ በመግባት የልጅነቷን የሰቆቃ ሕይወት ሕግ ፊት በማድረስ፣ ልጅቱን ከገሃነም ሕይወት መታደጋቸውን ከነዝርዝር ሂደቱ ይተርካል፡፡ እናት ሰለባ የሆነችውን ልጃቸውን በአደራ የሰጡት ለጎረቤታቸው ነበር፡፡ በተለምዶ እንደምናውቀው ግን ሀገራችን ውስጥ የልጅ አደራ፣ የአካባቢው ነዋሪና የማህበረሰቡም አደራ ጭምር እንደሆነ ነበር ፡፡ ማህበራዊ መስተጋብራችን ይህ ከነበረ የእናት አደራቸው ተበልቶ ከሞራል እሴትም ሆነ ከሃይማኖተኝነት መሰረት የወጣ እንደዚህ ዓይነት ተግባር እንዴት ሊፈጸም ቻለ? ተጠያቂውስ አካል ማን ነው? እንደ ማህበረሰብስ በሰብአዊነት የተሞላ የትልቅ ባህልና ታሪክ ወራሽ ነን የምንል ከሆነ ምን ዓይነትና አንዳች ከይሲ ነገር ተጠናውቶን ነው እዚህ ውስጥ የተገኘ ነው ? ህሊና ላለው ሰዉ ጥያቄ የሚያጭር ጉዳይ ነው፡፡

ይህንን ፕሮግራም ካየሁት ቢቆይም ለዚህ ጽሁፍ መነሻ ያደረግኩት፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን እየተከሰተ ያለው ነፍስ ማጥፋት፣ ጭካኔና ግፍ ባለቤት ማጣቱና አብዛኞቻችን ደግሞ የተጠመድንበት ቸልተኝነት ከክስተቱ ጋር ስለተዛመደብኝ ነው።
በየትኛውም ማህበረሰብ ውስጥ አቅመ ደካሞችንና ለጉዳት የተጋለጡ ሰዎችን ለዚህ ዓይነት ነውረኛ ተግባር የሚዳርጉ ግለሰቦች መኖራቸው አዲስ ጉዳይ አይደለም፡፡ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች ከማህበረሰባቸው አፈንግጠው በመውጣት ወንጀለኞችና ግፈኞች መሆናቸውም የተለመደ ጉዳይ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን ሁልጊዜ ለእንደዚህ አይነት ሰዎች ማነቆውና መግቻው መሳርያ ማህበረሰቡ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህ እውነተኛ ታሪክ ውስጥ ግን፣ ማህበረሰቡ ከዚህ በተቃራኒው ቆሞ በዝምታውና በቸልተኛነቱ የወንጀሉና የሰቆቃው ተባባሪ ሲሆን መመልከቱና መስማቱ እጅግ በጣም ተስፋ የሚያስቆርጥና የሚያሰጋ ጉዳይ ነው፡፡

ማህበረሰቡ በዚህች ጨቅላ ህጻን ልጅ ላይ የተፈጸመውን ኢ-ሰብአዊ ድርጊት፣ ያሳለፈችውን መከራና ሰቆቃ በዓይኑ እያየ፣ በጆሮው እየሰማ የግፉ ተዋናዮች “የኔ ጉዶች” ናቸው ከሚልና የአደራ ልጁን ባዕድ ናት ከሚል አግላይ ስሜት በመነሳት “በደቦ ዝምታ” ከነዋሪው ተነጥላ በመታየት በነሱና በልጆቻቸው እንዲደርስ የማይፈልጉትን ግፍ ለስምንት ዓመት እንድትቀበል አደርገዋታል፡፡

የአካባቢው ነዋሪዎች መስሏቸው ሊሆና ይችላል እንጂ በዚህ አሳፋሪ ድርጊት የተጠቃችውና የተዋረደችው ልጅቱ ብቻ ሳትሆን ሁሉም የሰው ልጅ በተለይ ደግሞ እኛ ኢትዮጵያዊያን ነበርን፡፡ ሌላው አሳዛኙ ነገር ደግሞ፣ ማህበረሰቡ ይህች ጨቅላ ልጅ ብቸኛና ባዕድ መስላ በመታየቷ ምክንያት ብቻ ሰቆቃውን ለማስቆም ወገንተኝነት ተጠናወቷቸው አቅም ያጠራቸው ቢሆንም እንኳ ጉዳዩን የሃይማኖት አባቶች፣ የአካባቢው አረጋውያን ለፍትሕ አካላት አቤት የሚሉበት የሞራል ከፍታ ማጣታቸው፣ በየትኛውም መለኪያ ጤናማ አዕምሮ ሊቀበለው የሚችለው ጉዳይ አልነበረም፡፡

በአንድ ወቅት ጆሴፍ ስታሊን “የአንድ ሰው ሞት ዜና ነው፣ የሺህ ሰው ሞት ግን ቁጥር ነው” ብሎ ነበር፡፡ ዛሬ ላይ እንደዚህ ዓይነትና ከዚህ እጅግ የከፉ በርካታ የተዘገቡም ሆነ ያለተዘገቡ ኢ-ሰብአዊና አሰቃቂ ድርጊቶች በሃገራችን በየክልሉ በስፋት መዛመታቸው እየታየ ነው፡፡ የአንዱ በረድ ሲል የሌላው መተካት ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በዶዶላ፣ በድሬደዋ፣ በአዳማ፣ በቢሾፍቱ፣ በቅማንት፣ በከሚሴ፣ በራያ፣ በቤንሻንጉል፣ በሱማሌና በጋምቤላ ወዘተ… በየጊዜው በሚቀሰቀሱት ግጭቶች ምክንያት የሚሰማው እግዚኦታ፣ ለቅሶና ዋይታ ገደብ አልፏል። መንስኤውም ከፖለቲካና ከሃሳብ ልዩነት ይልቅ በማህበራዊ መሰረታችን መናጋት ላይ የተንጠለጠለ መሆኑን ለመገንዘብም ሆነ ለመገመት አዳግቶናል፡፡ የንጹኃን ዜጎች ሞትና ሰቆቃ የፖለቲካ ሂሳብ ማወራረጃና የጅምላ ሕዝባዊ ተቀባይነት ማግኛ መንገድ ማድረግንም በስፋት እየተለማመድነው ነዉ፡ ፖለቲካዊ አለመግባባቶች ሲፈጠሩም መፍትሔ ለመሻት የሚያስችሉ በርካታ ሕጋዊና ሰላማዊ አማራጮች እያሉ ሰው ሆነን መፈጠራችንን እንስክንጠላ ድረስ የሚፈጸሙት አሰቃቂ ድርጊቶችን እያየንና እየሰማን እንደ ሕዝብ በቸልተኝነት ማለፋችን ሳያንሰን በንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈፀመውን ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ሰበብ ስንደረድርለት መገኘታችን፣ ነገ ላይ ከአሁኑ በእጅጉ የከፋ ሁኔታ ሊመጣ አንደሚችል ማሳሰቢያ ሊሆነን የሚገባ ጉዳይ መሆኑንም ዘንግተናል፡፡ ፖለቲካን በፖለቲካ መድረክ ላይ በመደማመጥና በመከባበር ከመጫወት ይልቅ የግፍ መናሃርያና የሞት ድግስ መወናኛ እያደረግነው ነው።

በዓለም ላይ እንዳየነው ከሆነ ግፈኞችና የነገ ፋሽስቶች የሚደበቁት ሞራሉ በላሸቀና ግድ የለሽ በሆነ ማህብረሰብ ውስጥ መሆኑን ታሪክ ደጋግሞ አስተምሮናል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ቡድኖችም ሆኑ ግለሰቦች በማህበረሰቡ ውስጥ ሃይ ባይ አለመኖሩ ከለላ የፈጠረላቸው ስለሚመስላቸው ድርጊታቸው ነውር የሌለውና ደግመው፣ ደጋግመው መፈጸም የሚችሉት ተግባር እንደሆነ በመቁጠር ፣ የተፈጠረውን አሳሳቢ ሁኔታ በመጠቀም የስልጣን ፋላጎታቸውን ማሳኪያ ከማድረግ ውጭ፣ ለሰው ልጅ ሕይወት ደንታ የሌላቸው መሆኑን እያስመሰከሩ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ግፈኞች የሚፈሩበትና የግፍ ሰለባዎች ደግሞ በተቃራኒው የሚሸማቁበትና የሚሽሹበት ዘመን ላይ ደርሰናል። ይህ ሁሉ እንደ ሕዝብ በግለኝነትና በፍርሃት ተሸብበን ለፈጠርነው ዝምታና ቸልተኝነት የምንከፍለው ዋጋ ነው።

እርግጥ ነው፣ እንደ ሃገር ከድብርታችንና ከቸልተኛነታችን ከነቃን እንደ ሀገር ለመቀጠል በርካታ ተስፋ ሰጭ እድሎች ከፊታችን አሉ። ነገር ግን ከእልቂት በሚተርፈው ሕዝብ ላይ ተመስርተን ሃገርን እንደ አዲስ እንገነባለን ብለው የመተላለቅ እልህ ውስጥ የገቡ ሃይሎችን በዝምተኝነትና በቸልተነኝነት በማለፍ በዚህ መንገድ እንደ ሕዝብ ለመቀጠል ከወሰንን፣ እንደ ሀገርም ሆነ አንደ ሕዝብ ከፍተኛ የሆነ ሰብአዊና ቁሳዊ ዋጋ መክፈላችን የማይቀር ነው፡፡

የኛ፣ የብዙሃኖቹ ቸልተኝነት እና ገፋ ሲልም “ሲበቃ ይበቃል” ማለት አለመቻል ለእንደዚህ ዓይነት ተግባር አቀነባባሪዎችም ሆነ አስፈጻሚዎቻቸው መደላድል እየፈጠርንላቸውና እያመቻቸናቸው መሆኑ ግልጽ ሊሆንልን ይገባል፡፡ ሌላው ሁሉ ቢቀር እንኳን፣ እንደ ሀገር መቀጠል ከቻልን፣ ይህ ሁሉ ግፍ ሲፈጸምና የሰው ልጅ ደም በከንቱ ሲፈስ የት ነበራችሁ የሚል የሞራልም ሆነ የሕግ ጥያቄ የሚያነሳ ቀጣይ ትውልድና ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ መምጣቱ እንደማይቀር ተረድተን ከዝንት ዓለም ውርደት እራሳችንን ልንታደግ ይገባል፡፡

ዛሬ ላይ በነፍስ ወከፍ የታደለ ይመስል በየማህበራዊ ሚዲያው በሚሰራጨው የጥላቻና የተነስ፣ ታጠቅ ዝመት ቅስቀሳና ማነሳሳት እየተጋጋልን በወገንተኝነት፣ በቁጣ፣ በቂም በቀል ስሜትና በፍራቻ ተሸብበን ወገን በወገኑ ላይ የሞት ድግስ ሲደገስ እያየንና እየሰማን ቸልና ዝም በማለታችን ምክንያት አንዳች ዓይነት ፖለቲካ ለማራመድ የጠቀመን ወይም ለአንድ የፖለቲካ ዓላማ መዳረሻነሰ የስልጣን ግብ መቆናጠጫነት እየተገለገልንበት መስሎን ከሆነ እራሳችንን እያታለልን ነው፡፡ በየክልሉ እየተንተከተከ ያለው ጉዳይ አንዳችም ፖለቲካ ሽታ የሌለበት፣ በምክንያት ያልተነሳ፣ በምክንያት የማይመለስ ቀቢጸ ተስፋና ጭፍን የእልቂት ድግስ ነው።
በጥቅሉ ግን በጀመርነው በዚህ የቸልተኝነትና የዝምታ ጉዞ ከቀጠልን እለት ከእለት ሀገሪቱን አንዳችም ትርፍ ወደ ሌለው ምጽአት እያንደረደርናት መሆኑ አሁንና ዛሬ ሊገለጽልን ይገባል እላለሁ፡፡

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top