የህወሓት ልሳን የሆነው ወይን መጽሄት በትናንትናው ዕለት ይዞት በወጣው 48 ገጽ ያለው ዕትም በሀገር ደረጃ በዘንድሮው ዓመት ሊካሄድ ዕቅድ የተያዘለት ሃገራዊ ምርጫ በተለያዩ ምክንያቶች የሚስተጓጎል ከሆነ ትግራይ ክልል የራሱን ክልላዊ ምርጫ በማካሄድ ‘ዲ ፋክቶ ስቴት’ ለመሆን ወደ የሚያስችለውን ‘ቁመና’ (status) ለመገንባት ምክረ ሀሳብ አቅርቧል።
ዕትሙ የዘንድሮ ሀገራዊ ምርጫ በተያዘለት ቀነ ገደብ እንዲካሄድ የሚያትት ሲሆን፣ ቢስተጓጎል ግን ሕገ-መንግስቱን መጣስ ብቻ ሳይሆን ‘ወደ ለየለት የፖለቲካ አለመረጋጋት’ ሊያመራ እንደሚችል ገልጿል።
አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞች፣ በሀገር ውስጥ የተንሰራፋውን የፖለቲካ አለመረጋጋት እና ግጭት ሳይቆም ሃገራዊ ምርጫ ሊካሄድ ስለማይችል ጊዜው መራዘም እንዳለበት ያሳስባሉ።
በተቃራኒው ደግሞ በሕገ-መንግስቱ መሠረት የተመረጠ መንግስት ካልቀጠለ ሁኔታው ከዚህ ወደ ባሰ ቀውስ ስለሚገባ ምርጫ መካሄድ እንዳለበት የሚናገሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ። ከእነዚህም መካከል ህወሓት አንዱ ሲሆን በተደጋጋሚ ምርጫው መካሄድ አለበት በማለት አጥብቆ ሲሞግት ይደመጣል።
ይህንን አቋሙን ትናንት በታተመው ወይን መጽሔትም ላይ ሲያስቀምጥ “ምርጫው ከተራዘመ ሊፈጠር የሚችለውን የሕጋዊ ቅቡልነት እጦት (Legitimacy crisis) መላ የትግራይ ህዝብ ባሳተፈ እና በትግራይ ህዝብ ህልውና እና ደህንነት ጽኑ እምነት ያላቸውን በክልሉ የተቋቋሙት የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በመሆን በክልሉ ህጋዊ ምርጫ በማካሄድ እንፈታለን” ብሏል።
“እንደ ሃገር ሊያጋጥም ከሚችለው የፖለቲካ አለመረጋጋት በተነጻጻሪ የተሻለ እና መንግሥታዊ መዋቅርን (Institutions) የገነባ እንዲሁም ራሱን ችሎ የቆመ መንግሥት (De facto state) ለመመስረት የሚያስችል ስራዎች ማሳለጥ ተገቢ ነው” ይላል በመፅሔቱ ላይ የሰፈረው ሀሳብ።
በወይን መጽሔት ላይ የሰፈረው ይህ ጽሁፍ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ‘አምባገነን’ ሲል የገለፀ ሲሆን፤ “ዋነኛው አጀንዳችን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዓላማ ‘ሃገራዊ ምርጫውን አራዝሞ የፌደራል ስርዓቱን በመገርሰስ በአንድ ግለሰብ የሚመራ ስርዓት የማቆም ፍላጎት መሆኑን’ ሁሉም እንዲረዳው ማድረግ ነው” ካለ በኋላ ይህን አስተሳሰብ የሚሸከም ምቹ ሁኔታ እንዳይኖር አስፈላጊዉን የፖለቲካ እና የሚድያ ስራዎች እንደሚሰራ አትቷል።
“የቡድኑ መሪ ፍላጎት ቢቻል ቢቻል ፍጹም አምባገነናዊ አካሄድ የተረጋገጠበት አሃዳዊ ስርዓትን ለማቆም መሆኑን ፍጹም ጥራጣሬ ሊገባን አይገባም” ሲልም ጽሁፍ ያስረግጣል።
ኢህአዴግን ከግንባርነት ወደ ውሁድ ፓርቲነት ለመቀየር የተለያዩ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲገልፁ እንደነበር ይታወሳል።
ህወሓት ከዚህ በፊት በአቋም ደረጃ የውህደቱ ደጋፊ እንደነበር ቢገልፅም፣ ከጥቂት ወራት በፊት ባወጣው መግለጫ ግን “የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች አይደለም ውሁድ ፓርቲ ሊሆኑ ከዚህ ቀደም የነበራቸውን ግንኙነት እየሻከረ መጥቷል” በማለት ውህደቱ ግዜው እንዳልሆነ ገልጿል።
ህወሓት አክሎም በይፋም የውህደቱ አካል እንዳማይሆን በተደጋጋሚ አስታውቋል።
ጽሁፉ በመጨረሻም “ትግራይ መንግስታዊ ቁመና (Defacto state – ራሱን ችሎ የቆመ ነገር ግን በዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ እውቅና ያላገኘ መንግሥት) ያላት ክልል የማድረጉ ስራ የትግራይ ምሁራን እና ተመራማሪዎች ጥናት አካሂደውበት በአፋጣኝ ወደ ተግባር ሊቀየር እንደሚገባ” አስፍሯል።(ምንጭ፡- ቢቢሲ አማርኛ)