Connect with us

እያናወጠን ያለው ቡድን ኦሮሞንም ኢስላምንም አይወክልም

እያናወጠን ያለው ቡድን ኦሮሞንም ኢስላምንም አይወክልም
Photo: Facebook

ህግና ስርዓት

እያናወጠን ያለው ቡድን ኦሮሞንም ኢስላምንም አይወክልም

እያናወጠን ያለው ቡድን ኦሮሞንም ኢስላምንም አይወክልም፤ ሀበሻን የሚጠላ ኢስላም፣ ለኦሮሞ ኦርቶዶክስ ወንድሙ እምነት የማይገደው ኦሮሞ የለምና፤ **** ከስናፍቅሽ አዲስ

እየሆነ ያለው ነገር ሰከን ብለን እንድናስብ የሚያስገድደን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ጠላቶች እድላቸውን እየሞከሩ ነው፡፡ ቁማራቸው የሰው ነፍስ ስለሆነ ሀገር እንድትጠፋ እዚህም እዚያም የማይጠፋ እሳት ይለኩሳሉ፡፡ ችቦው አንዳንዴ የመብት ጥያቄ ነው፤ የኦሮሞ ገበሬ ከቦታው ተፈናቅሏል የሚል የመብት ጥያቄ እውነት የመሰለው ደግሞ ይከተላል፡፡

ጉዳዩ በኢንዱስትሪ ስም መሬቱን የተነጠቀውን የአዳአ ገበሬ የገላን አርሶ አደር መካስ አይደለም፡፡ እሱን አነሳስቶ ሀገር ማፍረስ ነው ካልተሳካና ውጤት ካመጣ ውጤቱን የሚያጣጥመው የአደአው ገበሬ አይደለም፤ ለኦሮሞ ታግሏል በሚል ስም ቡድኑ ያደራጀው ሃይል ነው፡፡

ሌላው የእሳቱ ማቀጣጠያ ችቦ እንደ ኦነግ ያሉ ተቃዋሚዎችን እንደግፋለን የሚል ሽፋን ነው፡፡ ኦነግ ዛሬ ከምን ያክል ደጋፊዎቹ ስንት ብር ለትግሉ እያገኘ እንደሆነ አላውቅም ስሙን ሽፋን ያደረጉት ሃይሎች ግን የእሳት ችቦ ሊያደርጉት እንዳሰቡ የሚያስታውቀው ድርጅቱ በሚከፍታቸው ቢሮዎችና አደረጃጀቱ ነው ምክንያቱም የፋይናንስ እጥረት አለበትና፤ እዚህም እዚያም የሚነሱ አመጾች ምክንያተ ብዙ መሆናቸው አንዱም ምክንያት ከዓላማው ጋር እንደማይገናኝ ማሳያ ነው፡፡

ብዙዎች የምናየውን ነገር የኦሮሞን ስምምነት ያገኘ የኦሮሞ ህዝብ የሚያደርገው አድርገው ያዩታል፡፡ ግን አይደለም፡፡ ኦሮሞ ደብረ ሊባኖስን ያኖረ፣ ዝቋላን የጠበቀ፣ ኢቲሳን ያስከበረ፣ የረርን የቀጠረ፣ አሰቦትን ያከረመ ህዝብ ነው፡፡ ቁልቢን የተንባከበ ህዝብ ነው፡፡

እነኚህ ወገኖች ለኦሮሞ ቢሆን የሚያስቡት ወንድም የኦሮሞ ህዝብ የሚያመልክበትን ቤተ እምነት ባላቃጠሉ፤ ኦሮሞ ኦርቶዶክሳውያን የሚከተሉትን እምነት እናጥፋ ባላሉ ነበር፡፡ ግን ከኦሮሞነት ጋር ዝምድናም ውግንናም የላቸውም፡፡

በሌላ በኩል የቤተክርስቲያንን ቃጠሎ ከእስልምና ጋር የተገናኘ የሚመስላቸው ወገኖች አሉ፡፡ ይሄም ደባ እንጂ እውነት አይደለም፡፡ እነኚህ ቤተ ክርስቲያን አቃጣዮች ቁርአን ባለፈበት ያላለፉ አረማዊያን ናቸው፡፡ ሙስሊምም ቢሆን በሀበሻነቱ ይጠሉታል፡፡ ሀበሻን የሚጠላ ሙስሊም ከነብዩ ምክር ያፈነገጠ የጨለማ መንፈስ ነው፡፡ በኢስላም ሀበሻ ክቡር ነው፡፡ ስሙን በታላቅ ክብር የሚነሳ ቢሆንም ለእነኚህ ቡድኖች ሀበሻነት ስድብ ነው፡፡

እነኚህ ቡድኖች ግባቸው ኢትዮጵያን ማፍረስ ነው፡፡ አረማመዳቸውን አይቶ መድረሻቸውን መረዳት አያዳግትም፡፡ ኢትዮጵያ ተተራምሳ አፈር ልሳ ማየት የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ገበሬን የሚወድ በአጨዳ ወቅት ሀገር አያተራምስም፡፡

ለኦሮሞ ወጣት የሚሳሳ ከተሞች በኢኮኖሚ እንዲደቁ አዋጅ አያውጅም፡፡ ለኦሮሞ ክብር የሚጠነቀቅ በገዳ የተከበረውን ባህል በቅጥረኛ ጎረምሶች አያምስውም፡፡ እናም ሰከን ብለን እናስብ፡፡ ሁላችንም ካላሰብን ሁላችንም እንከስራለን፡፡ ኪሳራችንን ስለሚያተርፋቸው እነሱ ይሳካላቸዋል፡፡

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top