አገር የምትለማው በተማሩት ትምህርት እና በቀሰሙት ዕውቀት ትውልድን የሚጠቅም ምሁራን ሲኖሯት ነው። ትውልድን የሚጠቅም ነገር ይገኛል ተብሎ የሚታሰበው ከተማረው የማኅበረሰብ ክፍል ነው። ለተፈጠረ ችግር መፍትሔ የሚገኘው ብቻ ሳይሆን ችግር እንዳይፈጠር ጥንቃቄ እንዲደረግ አስቀድሞ የማንቂያ ደውል የሚመታው ከተማረው ወገን ነው። ከችግር መውጫ ብልሃቱን እና ከመከራ ማምለጫ መንገዱን የሚያመለክቱት የአገራቸው ጉዳይ የሚመለከታቸው እና የትውልድ በሰላም ውሎ መግባት የሚያሳስባቸው ምሁራን ናቸው። ምሁራን በሚያስተምሩባቸው መካነ አእምሮዎች የነገዎቹን አገር ተረካቢ ወጣቶች በቀለም ትምህርት ከመኮትኮት በተጨማሪ ችግር ሲፈጠር እንዴት መቋቋም እንደሚጠበቅባቸው፣ የተጎዱ ወገኖቻቸውን እንዴት መርዳት እንደሚኖርባቸው ኃላፊነትን ማለማመድ ይጠበቅባቸዋል። በርትተው ተምረው ነገ ለሚረከቧት አገራቸው ዛሬ መሠረት እየጣሉ፣ ከቀደምቶቻቸው እየተማሩ እንዲሔዱ ማገዝ ከምሁራን የሚጠበቅ ተግባር ብቻ ሳይሆን አገራዊ ኃላፊነትም ጭምር መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን መካነ አእምሮዎቻችን(universities) ዕውቀት የሚገበይባቸው ከመሆን ይልቅ የልዩነት መፈጠሪያዎች፣ ጥቃቅኑ ጉዳዮች ሁሉ እየገዘፉ እና እየከረሩ ከሚበጠሱበት ደረጃ የሚደረሱባቸው የልዩነት ማቀጣጠያዎች እየሆኑ መጥተዋል። እንዲህ መሆኑ ደግሞ የአገርን ሰላም የበለጠ እያደፈረሰ፣ መፍትሔ ሊገኝለት የነበረውን ችግር እያወሳሰበ ይሔዳል እንጂ ለተከሠተ ችግር መፍትሔ አያመጣም። መፍትሔ የሚሆነው ችግር ሲፈጠር የበለጠ የሚያወሳስብ እና ልዩነትን የሚፈጥር ተግባር ከመፈጸም በመታቀብ ቁጭ ብሎ መወያየትና መፍትሔ መፈለግ ብቻ ነው።
ሰሞኑን በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የተፈጸመውን ግጭት ተከትሎ በሌሎችም ዩኒቨርሲቲዎች ማለትም በሃረማያ፤ በመቱ፤ በደምቢዶሎ፤ በባሌሮቤ፤ በጅማና በሌሎችም ዩኒቨርሲዎች ግጭቶች ተፈጥረው የሕይወት መጥፋትና የአካል ጉዳት ችግሮች ተከሥተዋል። በተጨማሪም ይህንን ግጭት እንደምቹ ሁኔታ በመጠቀም ከዩኒቨርሲቲዎች ውጭ በአካባቢ ነዋሪችም ላይ ብሔርና ሃይማኖትን በመለየት በተለይም በጥቅምት 2012 ዓ.ም ጥቃት በደረሰባቸው ምዕራብ ሐራርጌ አካባቢዎች ዳግመኛ ጥቃት እንደተፈጸመ መረጃዎች እየወጡ ይገኛል፡፡ በአንዳንድ ዩኒቨርስቲዎችም በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ሸሽተው ከዩኒቨርስቲው በመውጣት በተለያየ ቦታ የተጠለሉ ተማሪዎች በምግብና ውሀ እጦት እየተቸገሩ የሚገኝ ሲሆን ይህንን ችግር ለመቅረፍ ድጋፍ እያደረጉ ያሉ የአካባቢው ነዎሪዎች የሚመሰገኑና በአደረጉት አርአያነት ባለው ተግባራቸው ሊኮሩ የሚገባ ቢሆንም ከተማሪዎች ብዛትና ከነዎሪዎች አቅም አንጻር በቂ ሊሆን ስለማይችል ዩኒቨርስቲዎችና የመንግስት አካላት አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሠጡ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
አንድ አካበቢ ችግር ሲፈጠር በሌሎች አካባቢዎች ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር ሊሰራ ሲገባ ይበልጥ ለማባባስ የሚሰሩ ሚዲያዎችና አካላትን ማየት የአገራችን ትውፊት ባይሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከፍተኛ ስጋትን እየፈጠረ መጥቷል፡፡ ለተፈጠረ ችግር ሁሉ የዘር፣ የአካባቢ፣ የቋንቋ እና ሌላም ታርጋ በመለጠፍ ማባባስን ስራቸው አድርገው የያዙ አካላት እስከመቼ ዝም እንደሚባሉ ግልጽ አይደለም። በመሆኑም እሳትን በውኃ እንጂ እሳትን በእሳት ማጥፋት እንደማይቻል ማንኛውም ጤናማ አስተሳሰብ ያለው ሰው የሚረዳው በመሆኑ ይህንን ዓይነት ድርጊት ሊያወግዘውና ችግሩ እንዳይባባስ በእንጭጩ እንዲቀጭ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ እናቀርባለን፡፡ በተለይም የሀገር ሽማግሌዎች፤ የሃይማኖት አባቶች፤ የአካባቢ ወጣቶች፤ በተለያየ መልኩ የተደራጁ ማህበራት፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ችግሩ እንዳይባባስና ውድ የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት እንዳይቀጥፍ የድርሻውን እንዲወጡ፤ እንዲሁም ለትምህርት ብሎ ከቤተሰቦቹ ርቆ የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ፤ መንግስትንና የአካባቢውን ማህበረሰብ ተማምኖ ለመማር የመጣን ተማሪ በማስጠለል ከአደጋ እንዲከላከሉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
መካነ አእምሮዎቻችንን(Universities) የመታገያ እና የድብቅ ዓማላችሁ ማስፈጸሚያ የምታደርጉ ወገኖቻችን አሁንም ደግመን የምናሳስባችሁ ለነገ አገር ተረካቢ በሆኑ አእምሯቸው ባልበሰለ ወጣቶች ሕይወት ላይ ቁማር ከመጫወት እንድትታቀቡ ነው። የራሳችሁን ኑሮ ለማመቻቸት እና እንጀራችሁን ለማብሰል ብላችሁ በቢሊዮን የሚቈጠር ገንዘብ በየዓመቱ እየመደበች አገራችን የምታስተምራቸውን ልፋቷን ከንቱ ከማድረግ እንድትቆጠቡም እናሳስባችኋለን።አገራችን ይህን የምታደርገው የነገ አገር ተረካቢዎች መሆናቸውን አስባ መሆኑን ማሰብ እና በራሳችሁ ሊደርስባችሁ የማትፈልጉትን በድሃው ወገናችሁ ላይ ላለመፈጸም ሞራልም አገራዊም ኃላፊነት እንዳለባችሁ ማመን ይገባችኋል። ጥፋት እንዲፈጸም ተደብቃችሁ የምታቀነባብሩ ወገኖች በራሳችሁ ልጆች ሊደርስባቸው የማትፈልጉትን መጥፎ ነገር የገጠር እናቶች ያልፍልናል ብለው ወገባቸውን አስረው፣ የከተማ እናቶች ጉልት ቸርችረው እና በየሰው ቤት ተቀጥረው እየሠሩ አስተምረው ነገ ይደርሱልናል ብለው በተስፋ የሚጠብቋቸውን ተስፋቸውን ከማምከን ታቅባችሁ ያለፈው መከራ እንዲበቃ ልብ ትገዙ ዘንድ እንማጸናችኋለን።
ማንም ሰው ከየትም አካባቢ ይምጣ፣ ምንም ቋንቋ ይናገር ሲያጠፋ በሕግ ይጠየቃል እንጂ ጉዳት ሊደርስበት፣ በደቦ ፍርድ ልንበቀለው እንደማይገባ እኛ ብቻ ሳንሆን አገራችን ፈርማ የተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ሕግጋትም እንዲህ አይነቱን እኩይ ተግባር ይከለክላል። በወልድያ ዩኒቨርሲቲ የተፈጸመውን አደጋ ተከትሎ የክልሉ መንግሥት አጥፊዎችን ተከታትሎ በመያዝ ለፍርድ ማቅረቡ የሚያስመሰግን እንደሆነ ሁሉ ያልተያዙትን ለመያዝ እና በሌሎች ሰቆቃ ለማትረፍ የሚፈልጉትን ለፍርድ ማቅረብ ይኖርበታል።
በሌሎች አካባቢዎችም በተፈጠረው ችግር የተሳተፉ አካላትን የመለየትና ሕግ ፊት ማቅረብ፤ እንዲሁም ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ የተጠናከረ ጥበቃ ማድረግ ከአከባቢው መንግስትም ይሁን ከፌዴራል መንግስት የሚጠበቅ ግዴታ በመሆኑ ጊዜ ሣይሰጠው በከፍተኛ ትኩረትና ጥንቃቄ መፍትሔ እንዲጠሰው ጥሪ እናቀርባለን፡፡ ችግር ሲፈጠር አይመለከተኝም ሊል የሚችል የኅብረተሰብ ክፍል ሊኖር እንደ ማይችል ሁሉ ለሚፈጠር ችግር አፋጣኝ መፍትሔ አለመስጠትም ችግር እንዲፈጠር ካደረጉት አካላት ተለይቶ የሚታይ ባለመሆኑ በየደረጃው የምትገኙ የፍትሕ አካላት ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የሰው ልጅ ሁሉ ርትዕት የሆነች ፍትሐችሁን እደሚጠብቅ አውቃችሁ ለሚፈጠሩ ችግሮች አጥፊዎችን የሚያስተምር፣ ሌሎችን የሚያስጠነቅቅ መፍትሔ እንድትሰጡ እንጠይቃለን።