Connect with us

የከፍተኛ ትምህርት ዝቅተኛ ተማሪዎች

የከፍተኛ ትምህርት ዝቅተኛ ተማሪዎች
Photo: Ethiopian University Students' Dorm on Fire

ህግና ስርዓት

የከፍተኛ ትምህርት ዝቅተኛ ተማሪዎች

የከፍተኛ ትምህርት ዝቅተኛ ተማሪዎች።
ወላጅና መንግሥት ያልገራው ትውልድ።
ከስናፍቅሽ አዲስ

በተቃራኒ ሀገር መኖር ከባድ ነው። በሌላው ዓለም ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ከፍተኛ ደረጃ የደረሱ ተማሪዎች የሚማሩበት ነው። ከመፅሐፉም ከኑሮውም የማይማር ትውልድ ሕግ እየተማረ ነገ ዳኛ ሊሆን ዛሬ በጎጥና በብሔር ወንድሙን ይገድላል።

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪዎች ከኢትዮጵያ አፀደ ሕፃናት ተማሪዎች በበለጠ ለድብድብና ለጠብ የተጋለጡ ናቸው። ሰሞኑን እንኳን ሊያገዳድሉን የሚፈልጉ ኃይሎች አሉ ተጠንቀቁ ተብሎ ወዲያው ዩኒቨርሲቲን የጠብ ቀጠና ማድረግ አፀያፊ ነው። እንደ ዜጋ ግብር ከፍሎ ደንቆሮ መቀለብ ያሳዝናል። የሚበላው የሌለው ገበሬ ግብር ከፍሎ ሦስቴ በሚያበላው ተማሪ ፍዳውን እየበላ ነው።

እንዲህ ዓይነት ትውልድ አሳዳጊም የበደለው ነው። ወላጅ በልጁ ላይ ምግባርን ካላነፀ ውጤቱ ጥፋት ነው። መንግሥትም የገማ እንቁላልን ደህናው መካከል እየከተተ ትውልድ ካገማ ተጠያቂው ነው። አንዲት ቅጥር ግቢን ፀጥ ለጥ አድርጎ አለመምራት ትዝብት ውስጥ ይከተዋል።

ተማሪውን ይኼን ለመሰለ ትርምስ የዳረገው ውህደቱን ለማክሸፍ የሚደረግ የአልሞት ባይ ተጋዳይነት ትግል ነው። በዚህ ዳፋ ሀገር አምኖ ከጫፍ ጫፍ የሄደ የደሃ ልጅ ደመ ከልብ ይኾናል። መንግስት ይሄንን ግምት ውስጥ ከቶ መዘጋጀት ነበረበት ግን የሀዘን መግለጫ በመፃፍ ተጠምዶ ፋታ አጥቷል።

ጠቅላያችን እንደ እድር ዳኛ የሟች ቁጥር ይደምራሉ። እንደ እድር ጡሩንባ ነፊ በቴሌቪዥን መስኮት ሟች ያረዳሉ። ብዙ ተፎክሮ በተጀመረው የዘንድሮው የትምህርት ዘመን በመጀመሪያ ምዕራፍ ተቋማቱ ሲታመሱ ቀድሞም ዝግጅት ያልነበረ ወሬ ብቻ እሚያስብል ሆኖብናል።

ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ምንንም ምክንያት ያደረገ ጠብ ሊነሳ ይችላል ዱላ ተማዞ ተቀጣቅጦ እስከመገዳደል ምቹ ሁኔታ መፍጠር መንግስት ኃላፊነቱን እንዳልተወጣ ማሳያ ነው። ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የፌዴራል ሀብቶች ናቸው። ቆመጥ ካላየ አደብ አልገዛም የሚል ተማሪንም ቢሆን እንደ አጋእዚ ያለ ወታደር አዘጋጅቶ ቀጥቅጦ እንዳይገድል ቀጥቅጦ ማስተማር ነው።

አሁን ባለው ሁኔታ ትውልዱ አርጩሜ ይፈልጋል። ወላጁ ሳይቀጣው ዩኒቨርሲቲ የደረሰ ተማሪ መንግስት ሲመክረው ሊሰማ አይችልም። እናም ቅጣት ይፈልጋል። ጣቱን ሲቀስር የሌላን ዓይን ሳይዘነቁል ጣቱን ቆርጦ የሚጥል ውሳኔ ካልተተገበረ የደሃ ልጅ ሞት የደሃ እናት እንባ ማቆሚያ የለውም።

ህዝብ ደጋግሞ ፍትህ ይከበር ይላል። ትዕግስቴ አልቋል የሚለው መንግስትም ሰው ሲያልቅ እንጂ ትዕግስቱ ሲያልቅ ማሳየት አልቻለም። አንዱ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ከተሰዳደበ ሌላው ጋር ድብድብ ሌላው ጋ ግድያ ይቀጥላል። ስጋትና የፀጥታ ቅድመ ትንበያን ተከትሎ ቀድሞ ማክሸፍ አይታይም። መጨረሻችንን ለማየት ከመጣደፍ የየራሳችን ልጆች ላይ መንግስት ሆነን አደብ እናስገዛ። ስርዓት ከቤት ይጀምር ትውልዱ ከቤት ነውና የወጣው

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top