Connect with us

የኢህአዴግ ውህደት እንድምታዎች

የኢህአዴግ ውህደት እንድምታዎች
Photo: Facebook

ፓለቲካ

የኢህአዴግ ውህደት እንድምታዎች

የኢህአዴግ ውህደት እንድምታዎች፤
(ያሬድ ኃይለማርያም እንደጻፈው)
+++++

ይህ አገሪቱን ዛሬ ላለችበት ክፉ ሁኔታ የዳረገ ድርጅት እራሱን አድሶ እና ከከፋፋይነት ሚናው ወጥቶ ኢትዮጵያን አንድ የማረግ ኃላፊነት ለመሸከም ወደሚያስችለው ውህድ ፓርቲነት መምጣቱ ብዙ እንድምታዎች ሊኖሩት ይችላሉ። ከብዙ በጥቂቱ፤

አዎንታዊ

+ ህውሃት አገሪቱን በክልል ከፋፍሎ ሲሻው አጣምሮ ሊገዛ፤ ሳይፈልግ ሲቀር ደግሞ ሊያፈርሳት በሚያመቸው መንገድ ያዋቀራትን ኢትዮጵያን ለመታደግ ለሚታገሉ ኃይሎች ትልቅ አቅም ይፈጥራል፤

+ ቋንቋን መሰረት አድርገው የተካለሉት ክልሎች እያደር አገር ወደመሆን የጀመሩትን የቁልቁለት ጉዞ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ለማክሸፍ ይቻላል፤ በከፊል ያልኩት የዛሬዋ ኢትዮጵያ በሙሉ ቅርጿ ትቀጥላለች ወይ የሚለውን መቶ በመቶ እርግጠኛ ሆኖ መናገር ስለማይቻል ነው፤

+ ዶ/ር አብይ ከታሰሩበት የፓርቲ ወጥመድ በተወሰነ ደረጃ ነጻ የመሆን እድል ይፈጥርላቸዋል። አብይ በዛሬው አቋሙ የኦዴፓ እስረኛ መሆኑን አፍ ሞልቶ መናገር ይቻላል። እርምጃውም ሆነ ንግግሩ ኦዴፓ በፈቀደለት ልክ መሆኑን በሰሞኑ ክስተቶች በደንብ አሳይቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ የመቀጠል እድሉም በኦዴፓ እጅ ነው ያለው። ስለዚህ ይህ ውህድ ፓርቲ አብይን ከእስር ነጻ ያወጣዋል የሚል ግምት አለኝ።

+ የአብይ ከኦዴፓ እስር ነጻ መውጣት ደግሞ በሙሉ አቅሙ በአገሪቱ ውስጥ ሕግ እና ሥርዓትን ለማስከበር አቅም ይፈጥርለታል።

+ አብይ ሕግ ማስከበር ከጀመረ ኢትዮጵያ እንደ ጃዋር ያሉ ጽንፈኛ ፖለቲከኞች የሚፈነጩባት እና ከሕግ በላይ ሆነው ያሻቸውን የሚያደርጉባት አገር መሆኗ ያበቃ ይሆናል።

+ ውህዱ እውን ሲሆን ከአራቱ ድርጅቶች ውጭ የነበሩ አጋር ድርጅቶች እና ሌሎች ኃይሎችም በአብይ ዙሪያ በመሰባሰብ አቅም ስለሚፈጥሩለት በራሱ ድርጅት በኦዴፓ ውስጥ የሚገዳደሩትን አክራሪ ኃይሎች አሸንፎ መውጣት ይችላል፤

+ ህውሃት ውህዱን ስካልተቀላቀለች ድረስ በህውሃት እና በፌደራል መንግስቱ መካከል ያለው ግንኙነት ግልጽ መልክ ይይዛል። ሕውሃት የገዢ ፓርቲ አካል ሳትሆን ተቃዋሚ ሆና ትቀጥላለች። ይህ አይነቱ አሰላለፍ ከምርጫው በፊት የአገሪቱን በተለይም ትግራይን የማስተዳደሩ ጉዳይ ላይ ሌላ ውዥንበር ቢፈጥርም ለመፍትሔ ግን በር ሊከፍት ይችላል።

+ አዲሱ ውህድ ፓርቲ በአንዳንድ ክልሎች ድጋፍ ቢያጣ እንኳ በምርጫው ስልጣን እንዳያጣ እንደ ኢዜማ ካሉ ህብረ ብሄራዊ ድርጅቶች ጋር እስከ መዋሃድ ሊሄድ ይችላል።

+ አዲሱ ውህድ እና ኢዜማ ግንባር ፈጥረው ከተዋሃዱ በብሄር ተደራጅተው ከሕውሃት ጎን የሚቆሙትን ኃይሎች ለመገዳደር አቅም ይፈጥርላቸዋል።

+ ሌሎችም አዎንታዊ ገጽታዎችን መዘርዘር ይቻላል፤

አሉታዊ

+ ኢህአዴግ ወደ ውህድ መሄዱ እራሳቸውን ከክልልነት ወደ እራስ ገዝ መንግስትነት ለማሸጋገር ቀን ለሚቆጥሩ የክልል እና አክራሪ የብሔር ድርጅቶች እራስ ምታት ስለሚሆን ግጭቶች የመበራከት እድላቸው ሰፊ ሊሆን ይችላል፤

+ እህን ተከትሎ የሚቀሰቀሱት ግጭቶች ደግሞ ከፊታችን የሚመጣውን ምርጫ በታሰበለት ጊዜ እንዳይካሄድ ምክንያት ይሆናል፤

+ ምርጫው በጊዜው ሊካሔድ የማይችልበት ሁኔታ ከተፈጠረም ይህንንም እንደ እድል አሰፍስፈው የሚጠብቁ ኃይሎች ሕጋዊ መሰረት በሌለው አስተዳደር አንተዳደርም የሚል ሌላ ቅራኔ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ፤

+ የምርጫው መራዘም በአገሪቱ ውስጥ አለመረጋጋት እንዲሰፍን ከማድረጉም ባሻገር የፖለቲካ ምክዳሩንም ሊያጠበው ይችላል።

+ ህውሃትን ጨምሮ ውህደቱን ከወዲሁ እየተቃወሙ ያሉ ኃይሎች በተጠናከረ መልኩ ተቀናጅተው የሚፈጥሩት እንቅፋት የኢትዮጵያን አንድነት አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል።

ግራም ነፈሰ ቀኝ የኢህአዴግ ውህድ መሆን እና ብሔር ተኮር የሆነውን አደረጃጀት ወደ ህብረብሔራዊነት እንዲያድግ ማድረግ ብዙ መንገጫገጮችን ቢፈጥርም ኢትዮጵያን ለመታደግ የተሻለ አማራጭ መንገድ ነው ብዮ አምናለሁ። የኢህአዴግን ውህድ መሆንም ሆነ የኢዜማ ዜጋ ተኮር ፖለቲካ ማራመድ ያስደነበራቸው አክራሪ ብሔረተኞች አህዳዊ ሥርዓትን መጣብህ እያሉ ሕዝቡን ለማደናበር የጀመሩት እዮዮ ቀጣዩ የአገሪቱን ፖለቲካ እጅግ ውጥረት የተሞላው እና መናቆሮችም የሚታዩበት እንደሚያደርገው ከወዲሁ መገመት ይቻላል።

የብሔር ፌደራሊዝም ነጋዲዎች አገሪቱን የግጭት ቀጠና እንዳያደርጓት እና ሕዝቡንም ወደ እርስ በርስ ግጭት እንዳይመሩት ከወዲሁ በቂ እና ሰፊ ዝግጅት ማድረግ የግድ ይላል።

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top