Connect with us

የጥላቻ ንግግር ህጉና ህገ-መንግስቱ!

የጥላቻ ንግግር ህጉና ህገ-መንግስቱ!
Photo: Facebook

ህግና ስርዓት

የጥላቻ ንግግር ህጉና ህገ-መንግስቱ!

የጥላቻ ንግግር ህጉና ህገ-መንግስቱ! | (በአፊላስ አእላፍ)

ለጥቅል ግንዛቤ ይረዳን ዘንድ፤ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል በወጣውና በቅርቡ በሚንስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በተላከው ረቂቅ አዋጅ ክፍል አንድ ላይ፡-

<< “የጥላቻ ንግግር” ማለት የሌላን ግለሰብን፤ የተወሰነ ቡድንን ወይም ማህበረሰብን ብሄርን፤ ሀይማኖትን፤ ቀለምን፤ ጾታን፤ አካል ጉዳተኝነትን፤ ዜግነትን፤ ስደተኝነትን፤ ቋንቋን፤ ዉጪያዊ ገጽታን፤ መሰረት በማድረግ ፣ሆነ ብሎ እኩይ አድርጎ የሚስል፤ የሚያንኳስስ፤ የሚያስፈራራ፤ መድልዎ እንዲፈጸም፤ ወይም ጥቃት እንዲፈጸም የሚያነሳሳ ንግግር ነው።›› የሚል የትርጉም ብይን ይሰጣል፡፡

እንዲሁም በረቂቅ አዋጁ ‹‹ “ሃስተኛ መረጃ” ማለት የፍሬ ነገር ወይም አንኳር ይዘቱ ውሸት የሆነና ሁከት ወይም ግጭት የማስነሳት፣ ወይም ጥቃት እንዲደርስ የማድረግ እድሉ ግልጽ በሆነ መልኩ ከፍ ያለ ንግግር ነው።›› የሚል ፍቺ ይሰጠዋል፡፡

የረቂቅ አዋጁን አላማዎች በተመለከተም ፤
ሰዎች ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብታቸውን ተግባራዊ ሲያደርጉ ሰብዓዊ ክብርን፣ የሌሎችን ደህነነትና ሰላም አደጋ ላይ ከሚጥል ንግግር እንዲቆጠቡ ለማስቻል፤ በማህበረሰቡ ውስጥ እኩልነት እንዲሰፍን፣ መከባበር እንዲኖርና መግባባትና ዲሞክራሲያዊ ስርዐት እንዲጎለብት ለማድረግና ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት አደጋ የሆኑ የጥላቻ አመለካከትና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን መስፋፋትን እና ተያያዥ ወንጀሎችን መከላከል እና መቀነስ እንደሆነም ተብራርቷል።

እንግዲህ የጥላቻ ንግግር ተግባራት በምን ይገለጻሉ? የሚል መጠይቅ ከተነሳም ረቂቅ አዋጁ ‹‹ ሆነ ብሎ የሌላን ግለሰብን፤ የተወሰነ ቡድንን ወይም ማህበረሰብን ብሄርን፤ ሀይማኖትን፤ ቀለምን፤ ጾታን፤ አካል ጉዳተኝነትን፤ ዜግነትን፤ ስደተኝነትን፤ ቋንቋን፤ ዉጪያዊ ገጽታን፤ መሰረት በማድረግ ፣ እኩይ አድርጎ የሚስል፤ የሚያንኳስስ፤ የሚያስፈራራ፤ መድልዎ እንዲፈጸም፤ ወይም ጥቃት እንዲፈጸም የሚያነሳሳ ጥላቻ አዘል መልእክቶችን መናገር፤ ፅሁፍ መፃፍ፤ የኪነጥበብ እና እደ-ጥበብ ውጤት መስራት፤ የድምጽ ቅጂ ወይም ቪድዮ ማተም፤ ማሳተም ወይም ማሰራጨት፤ መልእክቶችን ብሮድካስት ማድረግ ወይም በማህበራዊ ሚዲያ ማሰራጨት፤ ወይም በሌሎች ማናቸዉም መገናኛ መንገዶች ለህዝብ መልእክቱ እንዲደርስ ማድረግ ክልክል “መሆናቸውን በአጽንኦት ይደነግጋል፡፡

የሃሰት መረጃንም በተመለከተ ‹‹ የፍሬ ነገር ወይም አንኳር ይዘቱ ውሸት መሆኑን እያወቀ ወይም ማወቅ ሲገባው፣ ሁከት ወይም ግጭት የማስነሳት፣ ወይም ጥቃት እንዲደርስ የማድረግ እድሉ ግልጽ በሆነ መልኩ ከፍ ያለ መረጃን ሆነ ብሎ በማንኛውም መንገድ ማሰራጨትና ለህዝብ እንዲደርስ ማድረግ የተከለከለ ነው። ›› ይላል፡፡

ረቂቅ አዋጁ አንድ ንግግር እንደ ጥላቻ ንግግር ተወስዶ በወንጀል የማያስጠይቅበትን ልዩ ሁኔታም ሲያብራራ፡- ድርጊቱ ለትምህርታዊ ወይም ሳይንሳዊ ምርምር የተደረገ እንደሆነ፤ የሚዛናዊ እና ትክክለኛ ዘገባ፤ በዲሞክራሲያዊ ስርዐት ውስጥ ተቀባይነት ያለው ትችትና የፖለቲካ ንግግር፤ የማስታወቂያ ወይም ማስጠንቀቂያ አካል እንደሆነ፤ በቅን ልቦና የሚደረጉ ሃይማኖታዊ አስተምሮት ወይም አተረጓጎም ከሆነ፤ ንግግሩ የጥሬ ሃቅ ዘገባ ወይም ዜና ከመሆን ይልቅ ወደ ፖለቲካ አስተያየትና ትችትነት ያጋደለ ከሆነ፣ ንግግሩ ቀልድ፣ ስላቅ ወይም ልብወለድ መሆኑ ግልጽ ከሆነ፣ንግግሩን ያደረገው ሰው የመረጃውን እውነተኛነት ለማረጋገጥ በሱ ሁኔታ ካለ ሰው የሚጠበቀውን ምክንያታዊ ጥረት ያደረገ እንደሆነ እንደ ጥላቻ ንግግርና ሃሰተኛ መረጃ ተወስዶ በወንጀል እንደማያስጠይቀው በግልጽ ያብራራል።

እንዲሁም በረቂቅ አዋጁ ማንኛውም ግለሰብ፤ የሚዲያ ተቋማትና አገልግሎት ሰጪዎች በአዋጁ የተከለከሉ ተግባራትን የፈጸሙ እንደሆነ፤ በህግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ አስምሮበታል፡፡

እንግዲህ የኛን የጥላቻ ንግግርና ሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የወጣውን ረቂቅ አዋጅ በግርድፉ ካየን ዘንዳ እስቲ ደግሞ አቶ ውብሸት ሙላት ‹‹ መጥላት ላለብን የጥላቻ ንግግር የተጨማሪ ሕግ አስፈላጊነት›› በሚለው መጣጥፋቸው በወፍ በረር የሌሎች ሀገራትን ህግጋትና አካሄድ ያስቃኙናል፡፡

‹‹ስለጥላቻ ንግግር የአሜሪካ መንገድ፡-

አሜሪካ ትልቅ ቦታ የምትሰጠው እሴት ቢኖር ነፃነት ነው፡፡
ነፃ ንግግር ደግሞ አንድም የሰው ልጅ ህልውና አካል ሲሆን፣ በሌላ መልኩ ደግሞ ነፃነትና ዴሞክራሲ፤ ያለ ነፃ ንግግር ምንጊዜም ጎደሎ እንደሆኑ ነው፡፡

በመሆኑም የአሜሪካ መርህ ነፃነትን ራሱን የሚያጠፋ እስካልሆነ ድረስ፤ ንግግር ላይ ገደብ አይኖርም፡፡
በተለይም ደግሞ የንግግሩ ይዘት፤ ጥላቻን ያዘለ ነው በሚል ሰበብ ብቻ ክልከላ የለም፡፡
ገደብ የሚደረገው፤ ንግግሩ የሚደረገበትን ዐውድ በማየት ይሆናል፡፡

የተደረገው ንግግር የኃይል ድርጊት ላይ የተመሠረተ ሕገወጥ ድርጊት ለማስነሳት ቅርብ ከሆነ፤ ሊገደብ ይችላል ፡፡
ካልሆነ ንግግርን መልሶ በንግግር በመጋፈጥ እንጂ፤ በመገደብና በማፈን ዴሞክራሲ አይሰፍንም የሚል ነው የአሜሪካ አካሄድ፡፡

የብዙኃኑ መንገድ፡-

በርካታ አገሮች ከአሜሪካ የተለየ መንገድ ነው የሚከተሉት፡፡ አገሮች ለተለያየ እሴት ቅድሚያ ይሰጣሉ፡፡
የእሴቶቻቸው መነሻ ደግሞ የራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ ነው፡፡

ለአንዳንዶች እኩልት፤ ለሌሎች ሰብዓዊ ክብር ወይንም ተከባብሮና ተፈቃቅዶ መኖር አሊያም የእነዚህ ቅይጥ ሊሆን ይችላል፡፡
እኩልነትን የሚያስቀድሙት፤ አንድን ግለሰብ ከሌላ ጋር ለሚኖረው ግንኙነት ትኩረት ይሰጣሉ፡፡

ስለግለሰቡ ነጠላ ሕይወት ወይንም ምርጫ ሳይሆን ከሌሎች ጋር የሚኖረው መስተጋብር ነው ዋና ማጠንጠኛቸው፡፡
ሰብዓዊ ክብርን የሚመርጡ ደግሞ፤ ማንም ሰው የሌላውን ስም ሳያጎድፍ፣ ሳያንኳስስ፣ ሳያጣጥል፣ ወዘተ. እንዲኖርና መከባበር እንዲሰፍን ይመርጣሉ፡፡

በቡድኖች መካከል ተከባብሮና ተፈቃቅዶ መኖርን የሚመርጡም አሉ፡፡
ስለሆነም ሰብዓዊ ክብርን የሚነካ፣ ተቻችሎና ተፈቃቅዶ የሚኖርን ማኅበረሰብ እንዳይኖር እንከን የሚሆን፣ በማኅበረሰብ መከካል ያለው የባህል ሥሪት አንዱ ከአንዱ የሚበልጥ እንደሆነ የሚሰብክ ንግግር እንዲኖር አይፈቀድም ወይንም አይበረታታም፡፡
የኢትዮጵያንም ሕገ መንግሥት ስናጤነው፤ ትልቁ እሴቱ የግለሰቦች ነፃነት ላይ የተመረኮዘ ሳይሆን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እኩልነት፤ ተከባብሮና ተፈቃቅዶ መኖርን የመረጠ ስለሆነ፤ ነፃ ንግግር ወይንም ሐሳብን በነፃነት መግለጽና ለእነዚህ እሴቶች ተገዥ መሆን ግድ ነው፡፡

ኢትዮጵያም በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች መ/ቤት ታጸድቀዋለች ተብሎ የሚጠበቀው ሕግም የሚጸድቅ ከሆነ ከወዲሁ ትርፍና ኪሳራዎቹን ለመለየት በሁለት ጎራ የሚነሱት መከራከሪያዎችን በጥቂቱ እናንሳ፡፡
ንግግር፣ የጥላቻም ቢሆን ወንጀል መሆን የለበትም ባዮች፡-

የመጀመሪያው መከራከሪያቸው ንግግርን ወንጀል በማድረግ ከሚገኘው ጥቅም ይልቅ፣ ጥላቻ ባለው ንግግር የሚፈጠረውን ጉዳት መታገስ የሚያስገኘው ይበልጣል የሚል ነው፡፡

ንግግርን ማፈን በርካታ መብቶችን እንዲጣበቡ ያደርጋል፣ በርም ይከፍታል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ማንኛውም መጥፎ ሐሳብ የሚጠፋውና ማምከኛ ሊሆን የሚችል ተቃራኒ ሐሳብ በማቅረብ እንጂ፤ ንግግሩን በመከልከል አይደለም፤ መንግሥትም የምንናገረውን ነገር ይዘቱን ሊመርጥልን አይገባም፤ ግለሰቦችም ክፉን ከበጎ ለይቶ የማወቅ አቅምም ችሎታም ስላላቸው፤ ይኼንኑ ነፃነታቸውን ማክበር ተገቢ ነው፡፡

ሕግም ቢሆን ክፉ የማሰብንና የመናገርን ባሕርይን ሊቀይር አይችልም፤ ስለሆነም ወንጀል ማድረጉ ፋይዳ ቢስ ነው ይላሉ፡፡
የጥላቻ ንግግር ይከልከል የሚሉት መከራከሪያዎች፡-

ጥላቻን ያዘለ ንግግር በብዙ ምክንያት ጠቃሚ አይደለም፣ አስጸያፊ ነው ይላሉ፡፡
ለዚህ ከሚያቀርቡት ምክንያቶች ውስጥ የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡

የንግግሩ ሰለባ የሚሆኑትን የአንድ ቡድን አባላት እንደ ጠላት እንዲቆጠሩ ያደርጋል፤ ለብዙ ነገሮች ተጠርጣሪዎች እንዲሆኑ ያመቻቻል፡፡ ሌላው መከራከሪያ ደግሞ ሌሎች የማኅበረሰብ አባላት በእኩልነት አይታዩም፡፡
ለምሳሌ እንደ ተገንጣይ የሚሳሉ ከሆነ የመገንጠል ፍላጎት ከሌላቸው ጋር እኩል ተደርገው አይታዩም፡፡
ከዚህ ሌላ ደግሞ፣ በማኅበራዊ አቋማቸው ዝቅ ተደርገው እንዲታዩ ያደርጋል፡፡

ከሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር የተረጋጋና ቅንነት የተሞላበት ግንኙነት እንዳይኖር እንቅፋት ይፈጥራል፡፡
በግለሰቦችና በቡድኖች መካከልም ጥርጣሬና ውጥረት እንዲሰፍን ያደርጋል፡፡

አንዱ የሃይማኖት ተከታይ ወይንም የብሔር አባላት የበለጠ ለአገር አሳቢ፤ ሌላውን ጠላት አድርጎ የመሳል አዝማሚያን ይፈጥራል፡፡
ችሎታቸውንና አቅማቸውን በተገቢው ሁኔታ እንዳይጠቀሙ ያደርጋል፤ የተወሰኑ ሰዎችን ባሕርይ ለጠቅላላው የማሳደግ አዝማሚያን ስለሚያበረታታ፤ የቡድኑን አባላት በሙሉ ተጠቂና ሰለባ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡
በመሆኑም ጥላቻ አዘል ንግግር መከልከል አለበት ይላሉ፡፡››

መልካም ወደ ማጠቃለያው ስንመጣ የንግግር ነፃነትን አስመልክቶ ህገ-መንግስታችን ገደብ ሰጥቶታል ወይ የሚል መጠይቅ መንሳቱ ተገቢ ይሆናል፡፡

በሕገ መንግሥታችን አንቀጽ 29(6) ላይ በማያሻማና በግልጽ ቋንቋ እንደተገለጸው፤ ሐሳብን በፕሬስና በማናቸውም መገናኛ ብዙኃን ማንኛውም ሰው ሲገልጽ፤ የሐሳቡ ይዘት ምንም ይሁን ምን፣ ሐሳቡ በመገለጹ የሚያስከትለው ውጤት ምንም ይሁን ምን፣ መከልከል አይቻልም፡፡

በመሆኑም ይዘቱን መሠረት በማድረግ ሐሳብን የመግለጽ ክልከላ አይኖርም ማለት ነው፡፡
ሌላው ደግሞ አንድ ጽሑፍ ታትሞ በመውጣቱ፤ የመንግሥትን ተአማኒነት ያሳጣል በማለት መከልከል አይቻልም፡፡
ጠንከር ስናደርገው ደግሞ፤ አንድ ጽሑፍ መውጣቱ፤ አንድን ብሔር ከሌላው ጋር ሊያጋጭ ይችላል በሚል ምክንያት ክልከላ አይኖርም፡፡ የሚከለክል ሕግም ማውጣትም አይቻልም፡፡

ይህ ደግሞ የሚያስከትለውን ውጤት በማሰብ ብቻ መገደብ አይቻልም ማለት ነው፡፡
በሕግ የሚገደብባቸው ምክንያቶች ‘የወጣቶችን ደኅንነት የሚያናጉ፣ የግለሰብን መብት የሚጥሱና ሰብዓዊ ክብርን የሚነኩ፤ የአደባባይ መግለጫዎችን ማድረግ፣ የጦርነት ቅስቀሳ ማድረግ’ ብቻ ናቸው፡፡

ከእነዚህ ከአራቱ ውጪ፤ በሌሎች ምክንያት ፈጽሞ የሐሳብን ነፃነትን፤ በማናቸውም የፕሬስ ውጤቶችም ይሁን በኤሌክትሮኒክስ መንገድ እንዳይገለጹ መከልከል ወይንም ወንጀል ማድረግ ፈጽሞ ሕገ -መንግሥቱን መጣስ ነው፡፡
ከላይ የተገለጹትን ግቦች ለማሳካት ሲባል ብቻ ነው የንግግር ነፃነትን መገደብ የሚቻለው፡፡
ባጭሩ የጥላቻ ያዘሉ ንግግሮችን ለመገደብ መነሻዎቹ እነዚህ ብቻ መሆን አለባቸው፡፡

ባጠቃላይ በዚህ ጽሁፍ ለማሳየት የተሞከረው በቅርቡ ይጸድቃል ተብሎ የሚጠበቀው ‹‹የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን መከላከል›› ረቂቅ አዋጅ ከሌሎች ሀገራት ተመክሮና ከህገ-መንግስታችን አንጻር ያለውን አዎንታዊና አሉታዊ መስተጋብር ለማሳየት ነውና አንባቢው የራሱን ሃሳብና አተያይ ያክልበት ዘንድ በመሻት ነው፡፡

Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top