ከመከራ በፊት እንመካከር!
(በአፍላስ አእላፍ)
ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን ‹‹እናት አለም ጠኑ›› በተሰኘው ተውኔቱ የመጨረሻ ክፍል ላይ እንዲህ የሚል መነባንብ እናገኛለን፡-
‹‹ዘላለም የቂም በቀል ቅርስ፣ ለነግ ትውልድ የቂም ድግስ፣ ከዘር ዘር ስናግበሰብስ፣ ሀገር እንደ ኮረዳ አካል ያለ ፍቅር ላትጠና፣ ምድራችንን ፍቅር ነስተን፣ በስሜት እጦቷ መክና፣ አዎ ይብላኝልኝ ለዘመናዊ ወላጆች፡፡ እንደ እባብ ልጅ የርግማን ዘር፣ በልባችን ተጥመልምለን፣ ልጆቻችንን ነድፈን፣ ትቢያ ልሰን መርዝ ተፍተን፣ ነጻነት ሳይሆን ባርነት እንካችሁ ውርስ ነው ብለን፤ ፍቅር የሞተበት ጎጆ የሞቀ ትዳር ነው ብለን በልጆቻችን ፈረድንባቸው፡፡ የህይወት ጣዕሙን ሳይሆን ወጉን፤ የፍቅር ወዙን ሳይሆን ስሙን፤ የነጻነት ግብሩን ሳይሆን ተረቱን እንዳወረስናቸው ልጆቻችን ባዩብን በነቁብን ፈረድንባቸው፡፡ መንፈሳቸውን አኮላሸናቸው!…››
በርግጥም ባለቅኔው‹‹ ህያዊ ሳንሆን አፋዊ፤ ቃለ-ህይወት ሳንሆን ብኩን ቃል አፍ ብቻ!›› መሆናችንን በዘመን ተሸጋሪ ስራው በቅጡ ገልጾናል!
አለአንዳች ቅጥፈት እያንዳንዳችን፣ በድምር ሁላችን የዘረኛነት ልክፍት ተጠናውቶናል። ከሊቅ እስከ ደቂቅ ሁሉም ወደ ዘሩ ዘሟል። እያደር የተጋጋለው ዘረኝነት ሊያስከትል የሚችለው ሀገራዊ ክስረት አልታይ ብሎናል። ሁላችንም ከሰብዓዊነት፣ ከሚዛናዊነትና የወልን ጥቅም ከማስከበር ምህዋር አፈንግጠን በዘር ኮርቻ ላይ ተፈናጠን ሽምጥ ስንጋልብ፤ የዚህች ሀገር መጨረሻ ምን ይሆን? ብለን ለአፍታ ቅጽበት ማሰብ ተስኖናል።…እናም ወዴት እያቀናን ነው? የሚል ጥያቄ ማንሳቱ ግድ ነው።
እውነት ለመናገር ምንም ነገር ብትናገር፣ አንዳች ነገር ብትጽፍ ሃሳብህ በዘረኝነት መስፈርት ይቃኛል። ሀገርን አዳኝ የሆኑ ሸጋ ሐሳቦች ቢኖሩህ ‹‹ከየትኛው ዘር መነጩ›› የሚል ፍተሻ ይከናወንባቸዋል። ሰው ክፉኛተጠራጣሪ ሆኗል። ያንንም ይህንንም ዘረኛ ነው ብሎ ይፈርጃል።
አዎን ዛሬ ዛሬ በየመንደሩና በየስርጣ ስርጡ በዘር የተደራጀው የጦር አበጋዝ ተበራክቷል። ተሰሚነትን ለማግኘት «ዘሬን ዘሬን» ማለት የሚያስወድስ ተግባር ሆኗል። ሁሉም «ዘሬን ዘሬን» እያለ ይጮኻል። ዘረኝነት እንደ ገደል ማሚቱ ያስተጋባል።
እኔም አንተም በማህበራዊ የመገናኛ መድረኮች ላይ ፊጥ ብለን ሰርክ እንደ ጠዋት ጸሎት የዘረኝነትን ዝማሬ ስናሰማ እንውላለን። በፌስ ቡክ ግድግዳችን ላይ ምሁር እንደሆን እየገለጽን ፣ዘረኝነትን መሰረት አድርገን ያለአንዳች እፍረትና ማመንታት የጥላቻ ስብከት እንሰብካለን። በግልጽ በአደባባይ ጸያፍ ዘረኝነትን ስናቀነቅን ሐፍረት እንኳ አይሰማንም።
በርግጠኝነት ብዙዎች በዘረኝነት አብሾ ሰክረዋል። ስትደግፋቸውም ስትቃወማቸውም በዘረኝነት ከረጢት ውስጥ ይከቱሃል። በዚህች ሀገር በአራቱም መአዘን ውስጥ የጎጠኝነት ክፉ ደዌ እንደወረርሽ ተሰራጭቷል። በቃ ሁሉም ነገር በዘር አጉሊ መነጽር የሚታይ ሆኗል። የዘረኝነት አብሾ መጨረሻው ጦርነት፣ መገዳደል፣ መፈናቀል፣ መሰደድና አገርን ማፈራርስ መሆኑ ተረስቷል። ኧረ ጎበዝ ምን ይሻለናል? ማንስ ነው ካሸለብንበት የሚያነቃን?
ቆይ በየጊዜው በግጭት ሳቢያ ህዝብ ሲጨራረስ፤ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ነው አደብ የሚያስገዛን? የከፋ እልቂት ከተፈጠረ በኁላ፤ በሚቆፈሩት መቃብሮች ነው የምንሰክነው?
ዛሬ የኔ ብለን «አካኪ ዘራፍ» የምንልባቸው ክልሎችና ዞኖች፤ በጎሳ ግጭት ምክንያት ድራሻቸው ጠፍቶ፤ በሚከሰተው ምስቅልቅሎሽ ነው የምንገራው?
እሺ ማን ይንገረን?! ነጋሪ ያጣን ተናጋሪ ብቻ ሆነናል እኮ! ኤዲያ ግራ የገባ ነገር፤ ግራ የገባት ሀገር።
ይሄው ዘረኝነቱ አልበቃ ብሎን፤ የማንነት ጥያቄውም መጦዙን ቀጥሏል። በትልቁ ክልል ውስጥሌላ ዘርን መሰረት ያደረገ‹‹ ክልል ይቋቋምልን!›› ጩኸት እዚህም እዚያም ከፍ ብሎ ይሰማል። ይባስ ብሎ በዚያው ክልል ውስጥ ‹‹የልዩ ዞን›› ጥያቄ ይነሳል። አዎን ተበድያለሁና ‹‹ዞን ይሰጠኝ!›› የሚል ጠዝጣዥ ጥያቄ፤ ለዚህች ሀገር የአጥንት እከክ ሆኗል።
ልብ ላለው፣ነገር አለማችን ሁሉ ‹ከድጡ ወደ ማጡ› እየሆነ ነው። በእርግጠኝነት ከመቼውም ጊዜ በላይ ጥሞና ያሻናል!። እስከ አፍንጫችን ድረስ የታጠቅነው የዘረኝነት ትእቢት ተንፍሶ በእርጋታ ልንመካከር ይገባል! ሰብሰብ ብለን የተሻለች፣ ለሁላችን የምትበጅና ለቀጣዩም ትውልድ የምናስረክባት ሀገር ትኖረን ዘንድ መወያየት፣ መነጋገር አለብን። አዎን ከዘራችን በፊት፤ ለሰላምና መረጋጋት ቅድሚያ እንስጥ!!
ኢትዮጵያን «የኔ» በምንለው መልኩ ብቻ ልንቀርጻት ከተነሳን ፤ ከከሳሪዎች ጎራ እንሰለፋለን። በመደማመጥ ሀገር ለማዳን እንነሳ። አንዱ አንዱን ጥሎ ለማሽነፍ የሚያደርገው ጥረት፤ ሁላችንንም ተሸናፊ ያደርገናል። ጊዜው የመፈራረጃና እኔ የተሻልኩ ነኝ የምንልበት ሳይሆን የመጣውን አደጋ በጠረጴዛ ዙሪያ ተወያይትን የምንመክትበት ነው።
ጊዜው ሳይረፍድ፤ ዘርፈ-ብዙ ሃሳቦችን አንሸራሽረን፤ አሸናፊ የሆነ የወል ሀሳብን ጨምቀን ማውጣት ግድ ይለናል። ‹‹እኔ እበልጥ፤ እኔ እበልጥ!›› ብለን ከተናከስን፤ ምድሪቱ የሁላችንም መቀበሪያ ትሆናለችና ልብ እንግዛ።
ልብ ካለን ልብ እንበል!ከመከራ በፊት ፈጥነን እንመካከር!