መንግሥት ጀዋር መሐመድን በዝምታ ሊያልፈው አይችልም፤ በጭራሽ! | (ጫሊ በላይነህ)
ጀዋር መሐመድ “ጥበቃዎቼ ሊነሱ ነው…ተከብቤአለሁ” በሚል አከታትሎ በማህበራዊ ድረገጾች የለጠፋቸው ቅስቀሳዎች ተከትሎ ደጋፊዎቹ በቁጣ ወደጎዳና ወጥተው በሁለት ቀናት ቆይታ ብቻ መንግሥት ባመነው ለ 86 ሰዎችን ሞት መንስኤ ሆነዋል፡፡ ሥርዓት አልበኞቹ በሠላም የሚኖሩ ዜጎችን (የኦሮሞ ልጆችን ሳይቀር) በጠራራ ጸሐይ ከቤታቸው እየተጎተቱ በአስነዋሪና በአሰቃቂ ሁኔታ ጨፍጭፈዋል፡፡
እነሆ ከጥቅምት 12 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ሲቆጠር ዛሬ ጭፍጨፋው 16 ኛ ቀኑን ቢይዝም ዋና አቀናባሪዎቹ በሕግ የመጠየቃቸው ነገር በዝምታ ተዳፍኖ ቀናትን መቁጠር ይዟል፡፡ ሌላው ቀርቶ ለዚህ ጥቃት እስካሁን በይፋ ይቅርታ እንኳን የጠየቀ አካል አለመኖሩ እንደእግር እሳት ያንገበግባል፡፡ የፖለቲካ ሰዎቻችን የጭፍጨፋ ስምሪት ሰጪዎችን በሕግ በመጠየቅና ባለመጠየቅ ንትርክ ጉዳይ እያጠፉ ያሉት ጊዜ፣ በየእለቱ የሚደመጠው የመሀላ ብዛት ያሰለቻል፤ ያማል፡፡
ከምንም በላይ በድርጊቱ የሚጠረጠረው ጀዋር መሐመድ አሁንም አንገቱን ቀና አድርጎ ምንም እንዳልተፈጠረ ኑሮውን ቀጥሏል፡፡ የተለያዩ መንግሥታዊ አካላት፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ የፖለቲካ አመራሮች ከምንም በላይ ሕዝቡ፤ ጨፍጫፊዎች ለሕግ እንዲቀርቡ በተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርበዋል፤ እያቀረቡም ይገኛሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ተመጣጣኝ እርምጃ እንደሚወሰድ ከተናገሩ በኋላ የኦሮሚያ ፣ የድሬደዋ፣ የሐረሪ ክልሎች ተጠርጣሪዎችን መያዝ መጀመራቸውን እያወሩ ይገኛሉ፡፡ ሕዝቡ ግን ለምን ተላላኪዎቹ ብቻ? ዋንኛ የጥቃት ጠንሳሾች ለምን አይጠየቁም እያለ መወትወቱን አላቆመም፡፡ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ያስኬዳል ባሉት መንገዶች ሁሉ አጥፊዎች በሕግ እንዲቀጡ በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው፡፡
ይብላኝለት ለመንግሥት እንጂ ሕዝቡ እነጀዋርን በሚገባ መቅጣቱን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ለዚህም አባባል ከሰዓታት በፊት ጀዋር በፌስቡክ ገጹ አንድ ካርቱን ስዕል ለጥፎ የተሰጠውን አስተያየት ማየት ይበቃል፡፡ ሕዝቡ በሚገባው ቋንቋ እኩይ ሥራውን ነግሮታል፡፡ በዓለም ላይ እንዲህ በሕዝብ ከመተፋት የበለጠ ከባድ ቅጣት ስለመኖሩ በግሌ አላውቅም፡፡
በሕግ አረዳድ፤ የወንጀል ሕግ ዓላማው አጥፊን መቅጣት ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም ማስተማር እና ማስጠንቀቅም ነው፡፡ ማህበረሰቡ ያጠፋ ሲቀጣ፣ በሕግ ሲጠየቅ ሲያይ ይጠነቀቃል፣ ሌሎችንም ያስጠነቅቃል፡፡ በዚህ ምክንያት ሥርዓት አልበኝነት እንዳይስፋፋ፣ ሕግ እንዲከበር፣ ሠላምና መረጋጋት በሀገር እንዲጸና ይረዳል፡፡ አሁን መንግሥት እነጀዋርን በሕግ ለመጠየቅ በማንገራገሩ ያጣው ተአማኒነቱን ብቻ አይደለም፡፡ ተመሳሳይ ጥፋት ቢፈጸም በሕግ ለመጠየቅ የነበረውን አቅምም አብሮ አጥቷል፡፡ በተግባር ማን ከእነማን ጋር እንደተሰለፈ ለሕዝብ ማሳየት ችሏል፡፡ ይህ ደግሞ በቀጣይ ሥርዓት አልበኝነት እንዲስፋፋ ምቹ ጫካ መፍጠሩ አይቀርም፡፡
ከምንም በላይ መዘንጋት የሌለበት ደግሞ ዛሬ በፖለቲካ ጥቅም የሕግ የበላይነትን የደፈጠጠው አመራር ነገ በሕግ መጠየቁ የማይቀር የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡ እናም ከፍተኛ አመራሩ ሕግና ሥርዓትን የሚያስከብረው ለማንም ብሎ ሳይሆን ለራሱም ብሎ መሆኑን በቅጡ ቢረዳ ይበጀዋል፡፡ አበቃሁ፡፡ (ጫሊ በላይነህ)