ጎበናን እወደዋለሁ፡፡ ራስ ጎበና ባይኖር ትልቅ ሀገር አትኖረኝም ነበር፡፡
****
(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ዛሬ ራስ ጎበናን አስታውሷቸዋል፡፡ በዐፄ ምኒልክ ዘመን ታላቋን ኢትዮጵያን ዳግም ለመፍጠር በተደረገ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ትልቁን ሚና የተጫወቱት ራስ ትልቅ ሀገር እንድትኖረኝ ምክንያት ናቸው ይለናል በተከታዩ ጽሑፉ፡፡)
ሄኖክ ስዩም በድሬቲዮብ
አሜሪካዊ ቢሆኑ ኖሮ ዛሬ ልጆች ከወላጆቻቸው ቀጥሎ ስማቸውንም ክብራቸውንም የሚያጠኗቸው የዓለም ሰው ይኾኑ ነበር፡፡ ግን አልታደሉም፡፡ የታደለች ሀገር ያልታደሉ ጀግና ኾኑ፡፡ ኢትዮጵያ እንጂ ጀግኖቿ አልታደሉም፡፡ ናፖሊዎንን ሳስብ ያን መሳይ የሀገሬ ጀግና ጎበና ዳጬ ኾኖ ልቤ ላይ ይኖራል፡፡
ታዋጊ ነው፡፡ ሱሪን ታጥቋታል፡፡ ዛሬ ስሙን ማንም አቅልሎ ሲጠራው ስሰማ እገረማለሁ፡፡ ትናንት በስሙ ተራሮች የሚሸሹለት የሚመስል አስፈሪ ወንድ ነበር፡፡ መጣ ከሚለው ቃል ቀጥሎ ድል አደረገ መገለጫው ነው፡፡ ከራስ ጎበና ጋር ደፍረው ውጊያን የተጋፈጡት ጥቂት ናቸው፡፡ ዕጣ ፈንታቸው ግን መሸነፍ ነበር፡፡ ታሪክ ይሄንን ለዘለዓለም አተመው፡፡
የተወለዱት ሸዋ ነው፡፡ የተመኙት አንዲት ታላቅ ሀገር ለመፍጠር; ልመለስ የሌለበት ጉዞ መጓዝ፡፡ ብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል ዐፄ ምኒልክ በንጉሠ ነገሥቱ በዐፄ ዩሐንስ ውስጥ ነበሩና ነጻ ለመውጣት ሀሳባቸው ጎበናን የመሰለ በማግኘታቸው መደሰታቸውን ጽፈዋል፡፡
ዓይኖቻቸው ሥልጣንና ወንበርን የሚመኙ አልነበሩም፡፡ ያ ሁሉ መስዋዕትነት ለሥልጣን ሳይሆን ትልቅ ሀገር ለመፍጠር ነው፡፡ ዓይኑን ልየው ያሉት ዝናውን የሰሙት ዐፄ ዩሐንስ አራተኛ ፊት እንኳን ለመቅረብ ምክንያት የለኝም ያለ ጀግና ነበር፡፡ ሀገሩን ለሚወድ ለነፍሱ ይቀርባልና እንደ አባት አንተ እንለዋለን፡፡ እሱ ታላቋን ኢትዮጵያ ለመሥራት ታላቅ ጀብዱ የፈጸመ ራስ ጎበና ዳጬ ነው፡፡
ከፋሌ እስከ ሱዳን ወሰን የኢትዮጵያን ድንበር ያቀና ነው፡፡ ትልቅ ሀገር አለን የምንለው ትልቅ ሰዎች ስለፈጠሯት ነው፡፡ ከፈጠሯት ተጣልተን በተፈጠረች ሀገር የምንጣላ ትንንሾች ስንሆን የግዙፍ ጀግኖቻችን ታሪክ ደጅ እንዳለ ጠበል ልጥ መንከሪያ ሆነ፡፡
ራስ ጎበናን የሸዋ መሳፍንት የሸዋ መኩሪያ ይሏቸዋል፡፡ እኔ ግን እላለሁ፤ ኢትዮጵያስ በማን ኮርታ ነው? ራስ ጎበናን የገጠመው ከባድ ጦርነት የኢማም ሀሰን አንጃሞ ነው፡፡ ራስ ጎበና አባ ጥጉ የኢትዮጵያዊነት ጥግ ነበር፡፡ ጠንካራ አፍሪቃዊት ሀገር የሰራ መሀንዲስ፤
ራስ ጎበና ሲሞት ለሀዘኑ የሚሆን ግጥም ጠፋ፡፡ እንዲህ ተብሎ ተለቀሰ፤
“ጎበና አባ ጥጉ ሞተ ወይ የምር
ወሬውም አያምር”
===
ታሪክ
ራስ ጎበና ዳጬ በአፄ ምኒሊክ ዘመነ መንግስት ከነበሩ ታላላቅ ሹማምንትና የጦር አበጋዞች አንዱ ነበሩ። ለዘመናዊቷ እና አንድነቷ የተጠበቀ ኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት ምስረታ መሃንዲሶች መካከል ግንባር ቀደሙ የጦር አዛዥ ናቸው።
ራስ ጎበና ለአፄ ምኒልክ አብሮ አደግ ወዳጃቸው የነበሩ ከመጀመሪያዎቹ የራስነት ማዕረግ ከተሰጣቸው አንዱ ጀግና ናቸው። ራስ ጎበና የቱለማ መሪ የዳጬ ልጅ እናታቸው ጎራዲት ይባላሉ የፈረሳቸው ስምም አባ ጥጉ የትዉልድ ሀገራቸው አብቹ ነዉ።
በለጋነት እድሜሀቸው እድል አጋጥሞሀቸው ወደ ምኒሊክ ቤተመንግስት በመግባታቸው የቤተመንግስቱን ህግ ፣ አስተዳደርና አጠቃላይ ስነስርሀት እየተማሩ ደረጃ በደረጃ በፍጥነት ማደግ ጀመሩ።
ራስ ጎበና በአፄ ምኒሊክ ዘመን ገናና ስም ከነበራቸው መኳንንት አንዱ በመሆን ኢትዮጵያ በንጉሰ ነገስቱ ጥላ ስር በአንድነት እንድትተዳር እና የድንበር ወሰኖቿም የጥንቱን መልክ እንድትይዝ፣ አንዲት ጠንካራ ኢትዮጵያ እንድትኖር ጠንከረው ከሰሩ የጦር አበጋዞች አንዱ ናቸው።
አፄ ምኒሊክ ራስ ጎበና ያበረከቱትን አስተዋፅኦ ከግምት ውስጥ በመክተት የሸዋ ጠቅላይ አዛዥ አድርገው ሾመዋቸዋል፣ በዘውድ በአላቸውም ወቅት የራስ ወርቅ ለራስ ጎበና ሽልማት ሰጥተዋቸዋል። ራስ ጎበና ከሰሯቸው ትልልቅ ስራዎች አንዱ ወሊሶን ሌቃ ነቀምቴ እና ሰዮ ወለጋ የተባሉትን የኢትዮጵያ አውራጃዎች በሰላም በፀጥታ እና በስርዐት እንዲኖሩ አርገው ማስተዳደራቸው ነው።
ልዑል ራስ መኮንን ወደ ቤኒሻንጉል ዘምተው ግብር አልገብርም ካሉት ሼህ ሆጀሌ ጋር ጦርነት ባደረጉ ጊዜ አብረዋቸው ከዘመቱት የጦር አበጋዞች አንዱ ናቸው። በ1880 አም በአሶሳ በኩል ድንበር ጥሶ የገባ የውጭ የሱዳን መሀዲስቶችን ሀይል በመጣ ጊዜም ዘምተው ተዋግተው ድል በማድረግ መሀዲስቶችን ጠራርገው አባረዋል።
ራስ ጎበና ከአፄ ምኒሊክ ጋር የቀረበ ጓደኝነት እንደነበራቸው ታሪክ ይነግረናል። የአፄ ምኒሊክ ልጅ …. ዘውዲቱ ምኒሊክ እና የአፄ ዮሀንስ ልጅ ራስ አርአያስላሴ ዮሀንስ በተጋቡ ጊዜ ራስ ጎበና በወቅቱ ለአፄ ምኒሊክ ያላቸውን አክብሮት ለማሳየት ትልቅ የነበረውን ሽልማት 1300 ፈረሶችን ለሙሽሮቹ ሸልመዋል።
ራስ ጎበና በሰኔ ወር 1881 ዓ.ም ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል። የቀብር ስነስርዐታቸውም በደብረሊባኖስ ተፈፅሟል።