23 ሺህ የጋራ መኖርያ ቤቶች የልማት ተነሽ ለተባሉ አርሶ አደሮች : ልጅና የልጅ ልጆቻቸው በሚስጥር ተሰጡ
በአዲስ አበባ እና ዳርቻዎቿ በልማት ምክንያት ተነስተዋል ለተባሉ አርሶ አደር አባወራዎች : ልጆችና የልጅ ልጆቻቸው በሚስጥር በወጣ እጣ በአዲስ አበባ በተለያዩ ቦታዎች ከተሰሩ የጋራ መኖርያ ቤቶች (ኮንደሚኒየሞች) 23 ሺዎቹ መሰጠታቸውን ዋዜማ ራዲዮ ቤቶቹ ከተሰጣቸው ግለሰቦች አረጋግጣለች። በእጣ የተከፋፈሉት የጋራ መኖርያ ኮንደሚኒየሞች ኮዬ ፈጬ : ቱሉዲምቱ እና ካራ ቆሬ የሚገኙ ናቸው።
በዋናነት የተከፋፈሉት የጋራ መኖርያ ቤቶች ያሉት ኮዬ ፈጬ ሲሆን ካራ ቆሬ ከተገነቡት ውስጥ ደግሞ በረከት : ፋኑኤል : ወታደር ሰፈር እና ጀሞ የሚባሉ ሰፈሮች የተሰሩ የጋራ መኖርያ ቤቶች ተከፋፍለዋል።በባለ እድለኞች እየተኖረበት ካለው ከቱሉዲምቱ ሳይት ደግሞ በመጠባበቂያነት የተያዙ ቤቶችም እጣ እንደወጣባቸው ሰምተናል።
የእጣ ማውጣት ስነ ስርአቱ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚካሄድ ቀጠሮ ተይዞ የነበረ ቢሆንም ባልታወቀ ምክንያት የሚሊኒየም አዳራሹ ስነ ስርአት ተሰርዞ አሁን ላይ እጣ የማውጣት ስነ ስርአቱ በሚስጥር መከናወኑን ተገንዝበናል።ከሰሞኑም ቤቱ በእጣ የተሰጣቸው ግለሰቦች በየሳይቱ እየሄዱ የደረሳቸውን ብሎኮች እያዩ እንደሆነም ማረጋገጥ ችለናል።ባለ እጣዎቹም ባለ ስንት መኝታ ቤት? የት ሳይት? ቤት እንደደረቸሳውም አውቀዋል።
የልማት ተነሽ ለተባሉት ለአባወራዎች ባለሶስት መኝታ ቤት የደረሳቸው ሲሆን ለልጅና ልጅ ልጆቻቸው ደግሞ እንደ እድላቸው ባለ ሁለትና ባለ አንድ ደርሷቸዋል።
የጋራ መኖርያ ቤት ለተሰጣቸው አርሶ አደር : ልጅና የልጅ ልጆቻቸው የተሰጣቸውን ቤት ለመኖርያ ዝግጁ አድርገው እንዲያጠናቅቁ ለማድረግም ሁለት ቢሊየን ብር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መድቧል። በዚህ ገንዘብ ራሱ ከተማ አስተዳደሩ ሰራተኛ ቀጥሮ ቤቱን ያስጨርስ ወይስ ለቤቱ እድለኞች ገንዘቡ ተተምኖ እንዲሰጣቸው ይታሰብ አይታሰብ ግን ማወቅ አልቻልንም።
ሆኖም የቤቱ ክፍፍል ላይ አሁንም ከፍተኛ ችግሮች መከሰታቸውን ዋዜማ ራዲዮ ከታማኝ ምንጮቿ መረዳት ችላለች።
በመጀመርያ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ለልማት ተነሽ አርሶ አደሮች በምትኩ የጋራ መኖርያ ቤት ይሰጥ ብሎ ባለፈው አመት ሲወስን ኮንደሚኒየም የሚሰጠው ለልማት ተነሽ አባወራ ብቻ እንዲሆን ነበር የደመደመው።
አሁን ግን ከካቢኔ ውሳኔው ውጭ ከልማት ተነሽ አርሶ አደሮች በተጨማሪ የትኛውም ያህል ቁጥር ያላቸው ልጆች ቢኖራቸው የጋራ መኖርያ ቤት ለልጆቻቸውም ተሰጥቷል ሲያልፍም ለልጅ ልጆቻቸውም እንዲሰጥ ተደርጓል። በምን መነሻ ካቢኔው መጀመርያ የወሰነው ውሳኔ እንደተቀለበሰ ግን አልታወቀም።
በሌላ በኩል በካሳ መልክ የጋራ መኖርያ ቤት ለማግኘት የልማት ተነሽ የተባሉ አርሶ አደሮች የእርሻ ቦታቸው ላይ ይሰሩ በነበረበት ወቅት ግብር የከፈሉበት ደረሰኝ : ያለፉትን ጊዜያት የተደረጉ ምርጫዎችን በዚያው ቦታ ለመምረጣቸው ማረጋገጫ መረጃዎች ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል። እንዲሁም በነበሩበት አካባቢ ያሉ ኮሚቴዎች እንዲመሰክሩላቸውም ይጠበቃል። ሆኖም ከነዚህ መመዘኛዎች ውጭ በርካታ ሰዎች የጋራ መኖርያ ቤት ማግኘት ችለዋል። ከአዲስ አበባ ውጭ ይኖሩ የነበሩና አርሶአደርም የአርሶ አደር ልጅ ያልነበሩ ሰዎችም የጋራ መኖርያ ቤት ተሰጥቷቸዋል።
በካራ ቆሬ አካባቢ ብቻ ሰላሳ የጋራ መኖርያ ቤቶች ያለ አግባብ ተሰጥተዋል።በኮዬ ፈጬ ሳይት ከተሰሩ ቤቶች መካከልም ባለፈው አመት የካቲት ወር ላይ ለቆጣቢ እድለኞች በእጣ ወጥተው የነበሩ ቤቶችም አሁን ራሳቸው ቤቶቹ ተደርበው የልማት ተነሽ ለተባሉ አርሶ አደሮችና ልጆቻቸው በእጣ ደርሷቸዋል። በአስገራሚ ሁኔታም በአካል ሀገር ውስጥ የሌሉም ሰዎች እንዲሁ የጋራ መኖርያ ቤቶቹ ደርሷቸዋል።
ኮዬ ፈጩ ያሉት የጋራ መኖርያ ቤቶች እጣ ከወጣባቸው በሁዋላ የኦሮሞ መብት ተከራካሪ ነን የሚሉ ግለሰቦች ባስነሱት አመጽ የኦሮሚያና የአዲስ አበባ ወሰን አከላለል ጥናት እስኪጠናቀቅ እንዳይተላለፍ መታገዱ ይታወሳል። ከ1997 አ.ም ጀምሮ ቤቶቹን የቆጠቡ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ቤቶቹን ለማግኘት እየተጠባበቁ ነበር።
ከሁለት ቀናት በፊት የኣአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አዳዲስ ሀያ ሺህ የጋራ የመኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት መዘጋጀቱን ምክትል ከንቲና ታከለ ዑማ ይፋ አድርገዋል። [ዋዜማ ራዲዮ]