የታከለ ኡማ መንግሥት በምስጢር ያደላቸው ቤቶች
(በኃይሉ ሚዴቅሳ ፍስሃጽዮን)
ከንቲባው ተሾሙ፣ተሻሩ የሚለው ዜና አብቅቶ ደግሞ አሁን በምሥጢር ቤት አደሉ የሚል ዜና ሰምተናል፡፡ ዋዜማ ሬዲዮ በተደጋጋሚ ሲዘግብ የነበረው ነገር አሁን ግልጽ ሆኗል፡፡ ከሳምንታት በፊት በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ከኦሮሚያ ለሚመጡ ብቻ ሰዎች ‹‹በልማት ምክንያት ተፈናቅለዋል›› ለተባሉ ሰዎች 23 ሺህ ቤት ቤት ለማከፋፈል ዕቅድ ተይዞ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ወሬው አስቀድሞ በመገናኛብዙሃን እጅ በመግባቱ፣ ሳይፈፀም ቀረ፡፡ አሁን ደግሞ በምስጢር ቤቱን ማከፋፈላቸውን ሰማን፡፡
አጃኢበኛ አገር ነች መቼም!
ቀድሞ ነገር ቤቱን ከሌላቸው ላይ ቆጥበው ያሰሩት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ናቸው፡፡ ይህንን ቤት ከአዲስ አበባ ነዋሪ ላይ ቀምቶ ለመስጠት ያስቻላቸው ሕጋዊ ምክንያት ምን እንደሆነ አይታወቅም፡፡ በልማት ምክንያት የተፈናቀሉ ከሆኑም ያፈናቀላቸው ራሱ መንግሥት እንጂ የአዲስ አበባ ነዋሪ አይደለም፡፡ ሥለዚህ ኃላፊነት መውሰድ ያለበትና ወጪውን ሸፍኖ ቤት ማሠራት ያለበት መንግሥት እንጂ የአዲስ አበባ ድሃ አይደለም፡፡
ሲቀጥል ይህንን ሥራ በምስጢር ማከፋፈልስ ምን አመጣው የአዲስ አበባ ሕዝብ ‹‹በዙሪያህ ያሉት ሰዎች በልማት ምክንያት ተፈናቅለዋልና ቤት እንስጣቸው›› ተብሎ ምክር ቢጠየቅ እምቢ ይላል እንዴ መንግሥት ከመቼውም በላይ የአዲስ አበባንና የኦሮሚያ ልዩ ዞን ነዋሪዎችን በጥርጣሬ እንዲተያዩ እያደረገ ነው፡፡ ተባብረውና ተዛዝነው መኖር የቻሉበትን ታሪክ እያጠፋ ነው፡፡ይህ የኮንዶሚኒየም ምስጢራዊ እደላ አደገኛና ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጠራጥር፣ መንግሥትንም የበለጠ የማይታመን የሚያደርገው ነው፡፡
በኢትዮጵያ ሕገመንግሥት አንቀጽ 12 መሠረት የመንግሥት የትኛውም ሥራ ግልጽ መሆን አለበት፡፡ይሁን እንጂ አሁን በድብብቆሽ ቤት ማደል ከተጀመረ ነገ ከዚህም የከፋ ነገር ሊደርስ ይችላል፡፡
ዋዜማ ሬዲዮ ከታማኝ ምንጮቹ ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የኮዬ ፈጬንና ሌሎች ሳይቶች ኮንዶሚኒየሞችን መንግሥት ሰጥቷል፡፡ ‹‹የቤቱ ክፍፍል ላይ አሁንም ከፍተኛ ችግሮች መከሰታቸውን ዋዜማ ራዲዮ ከታማኝ ምንጮቿ መረዳት ችላለች››የሚለው ዋዜማ ሬዲዮ፣ ‹‹በመጀመርያ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ለልማት ተነሽ አርሶ አደሮች በምትኩ የጋራ መኖርያ ቤት ይሰጥ ብሎ ባለፈው አመት ሲወስን ኮንደሚኒየም የሚሰጠው ለልማት ተነሽ አባወራ ብቻ እንዲሆን ነበር የደመደመው።
አሁን ግን ከካቢኔ ውሳኔው ውጭ ከልማት ተነሽ አርሶ አደሮች በተጨማሪ የትኛውም ያህል ቁጥር ያላቸው ልጆች ቢኖራቸው የጋራ መኖርያ ቤት ለልጆቻቸውም ተሰጥቷል ሲያልፍም ለልጅ ልጆቻቸውም እንዲሰጥ ተደርጓል። በምን መነሻ ካቢኔው መጀመርያ የወሰነው ውሳኔ እንደተቀለበሰ ግን አልታወቀም››