ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ ከተሞችና አካባቢዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች ለተጎዱ ምእመናን፣ የኹለት ሚሊዮን ብር ጊዜያዊ ርዳታ እንዲደረግ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የወሰነ ሲኾን፣ የተመደቡ ብፁዓን አባቶች የማጽናናት ተልእኮዋቸውን ጀምረዋል፡፡
ከጥቅምት 12 እስከ 15 ቀን 2012 ዓ.ም፥ በምሥራቅ ሐረርጌ ጎሮ ጉቱ ወረዳ፣ በምዕራብ አርሲ-ዶዶላ እና ኮፈሌ፣ በባሌ ሮቤ እና ድሬዳዋ፣ የብሔርና የሃይማኖት አክራሪዎች ካደረሷቸው አሠቃቂ ግድያዎች ባሻገር፣ የምእመናንን መኖርያ ቤቶች፣ ልዩ ልዩ ንብረቶችና የንግድ ተቋሞች፣ ሙሉ በሙሉ በመዝረፍና በማቃጠል የተነጣጠረ ጥቃት ፈጽመዋል፡፡ በዚህም፣ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ምእመናን ከቀዬአቸው ተፈናቅለው፣ በአብያተ ክርስቲያንና በሌሎች ጊዜአዊ መጠለያዎች ለመቆየት ተገደዋል፡፡
በዶዶላ ምዕራፈ ቅዱሳን አቡነ ገብረ ክርስቶስ እና ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን፣ ከ4ሺሕ400 በላይ የኾኑ ምዕመናን ከቤተ ሰቦቻቸው ጋራ ተጠልለው ይገኛሉ፤ የወረዳው ቤተ ክህነት ጽ/ቤት፣ መኖርያ ቤቶቻቸው፣ ልዩ ልዩ ንብረቶቻቸው፣ የንግድ ተቋሞቻቸውና ድርጅቶቻቸው በአክራሪዎቹ የተዘረፉባቸውንና በቃጠሎ የወደሙባቸውን ከ133 ያላነሱ ምእመናን ዝርዝር በሪፖርት አስታውቋል፡፡
በምሥራቅ ሐረርጌ ጎሮ ጉቱ ወረዳ መንዲሳ ቀበሌ ጋንጌሶ፣ ዴራ እና ቡራክሳ ጎጦች እንዲሁም በካራሚሌ እና ባሮዳ፣ ከ149 በላይ አባወራዎች ንብረት ሙሉ በሙሉ ተዘርፏል፤ መኖርያ ቤቶቻቸው ተቃጥሎ ለእንግልትና መፈናቀል ተዳርገዋል፡፡ በድሬዳዋ የተፈናቀሉ ምእመናን በቤተ ክርስቲያንና በትምህርት ቤት ተጠልለው እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡
ከጠቅላይ ጽ/ቤቱ አንድ ሚሊዮን ብር፣ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አንድ ሚሊዮን ብር ወጪ ኾኖ የኹለት ሚሊዮን ብር አስቸኳይ ርዳታ እንዲደረግላቸው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ባለፈው ሳምንት ወስኗል፤ በዘላቂነትም ተጎጂዎችን ለማቋቋም የሚያስችል የተጠና ድጋፍ፣ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ በሚያቋቁመው ኮሚቴ በኩል እንዲከናወን መመሪያ ሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል፣ በምልአተ ጉባኤው የተመደቡ ሦስት ብፁዓን አባቶች፣ ትላንት እሑድ ጥቅምት 23 ቀን፣ በዶዶላ ምዕራፈ ቅዱሳን አቡነ ገብረ ክርስቶስ እና ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን በመገኘት የማጽናናት ተልእኮውን ጀምሯል፡፡
በምዕራብ አርሲ-ሻሸመኔ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኄኖክ የተመራው ልኡኩ፣ የባሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ እና የሶማሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ የሚገኙበት ሲኾን፣ የልዩ ልዩ መምሪያ ሓላፊዎችንና የሀገረ ስብከቱን ሓላፊዎች ያካተተ ነው፡፡ በዶዶላ ቆይታው፣ ምእመናኑን በማጽናናት የምግብ እና የቁሳቁስ ልገሳ አድርጓል፡፡
በቀጣይም ይኸው የቅዱስ ሲኖዶስ ልኡክ፣ በባሌ ሮቤ እና ሌሎች ጉዳት ወደደረሰባቸው አካባቢዎች ተዘዋውሮ የማጽናናት እንዲሁም አስፈላጊውን ርዳታ የመስጠት ተግባራትን ያከናውናል ተብሎ ይጠበቃል።
በተያያዘ ዜና፣ በሚያዝያ ወር 2007 ዓ.ም. በአይ ኤስ ዓለም አቀፍ የሽብር ቡድን፣ በሜዲትራንያን የባሕር ዳርቻና የሊቢያ በረሓ፣ በሰይፍ ተቀልተውና በጥይት ተደብድበው ሰማዕትነትን የተቀበሉ 28 ኢትዮጵያውያን ሰማዕታትን ዐፅም ወደ ሀገር ለማምጣት ጥረቱ እንደቀጠለ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ላይ ተገልጿል፡፡
“ስለ ሰማዕታተ ሊቢያ ዐፅም ጉዳይ” በሚል በተያዘው አጀንዳ ላይ እንደተገለጸው፣ የሰማዕታቱ ዐፅም በጅምላ የተቀበረበት ቦታ ተለይቶ መታወቁን፣ ወደ ሀገር ቤት በሚመጣበት ኹኔታ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋራ ንግግር እየተደረገ እንደኾነ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡ “መሥመር ይዟል፤ እንዴትና መቼ ይምጣ የሚለውን እየመከርንበት ነው፤” ብለዋል አንድ የምልአተ ጉባኤው አባል፡፡
ሃይማኖታችንን አንክድም ብለው ስለ ሃይማኖታቸው የተገደሉት 28ቱ ወጣቶች፣ የሃይማኖት መስተጋድላን በመኾናቸው የሰማዕትነት ክብር እንደሚገባቸው ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ሚያዝያ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. ባደረገው የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ መወሰኑ ይታወሳል፡፡(ምንጭ፡-ሐራ ተዋህዶ)