Connect with us

በአዲስአበባ ብሔር ተኮር የኮንደሚኒየም እደላ ለምን አስፈለገ?

በአዲስአበባ ብሔር ተኮር የኮንደሚኒየም እደላ ለምን አስፈለገ?
Photo: Facebook

ህግና ስርዓት

በአዲስአበባ ብሔር ተኮር የኮንደሚኒየም እደላ ለምን አስፈለገ?

ዋዜማ ራዲዮ 23 ሺህ የጋራ መኖርያ ቤቶች የልማት ተነሽ ለተባሉ አርሶ አደሮች፣ ልጅና የልጅ ልጆቻቸው በሚስጥር ስለመሰጠቱ ያቀረበውን ዘገባ ሳነብ የተደበላለቀ ስሜት ተሰምቶኛል፡፡ ዘገባው በአጭሩ እንዲህ ይላል፡፡

“በአዲስ አበባ እና ዳርቻዎቿ በልማት ምክንያት ተነስተዋል ለተባሉ አርሶ አደር አባወራዎች : ልጆችና የልጅ ልጆቻቸው በሚስጥር በወጣ እጣ በአዲስ አበባ በተለያዩ ቦታዎች ከተሰሩ የጋራ መኖርያ ቤቶች (ኮንደሚኒየሞች) 23 ሺዎቹ መሰጠታቸውን ዋዜማ ራዲዮ ቤቶቹ ከተሰጣቸው ግለሰቦች አረጋግጣለች። በእጣ የተከፋፈሉት የጋራ መኖርያ ኮንደሚኒየሞች ኮዬ ፈጬ፣ ቱሉዲምቱ እና ካራ ቆሬ የሚገኙ ናቸው።

በዋናነት የተከፋፈሉት የጋራ መኖርያ ቤቶች ያሉት ኮዬ ፈጬ ሲሆን ካራ ቆሬ ከተገነቡት ውስጥ ደግሞ በረከት : ፋኑኤል : ወታደር ሰፈር እና ጀሞ የሚባሉ ሰፈሮች የተሰሩ የጋራ መኖርያ ቤቶች ተከፋፍለዋል።በባለ እድለኞች እየተኖረበት ካለው ከቱሉዲምቱ ሳይት ደግሞ በመጠባበቂያነት የተያዙ ቤቶችም እጣ እንደወጣባቸው ሰምተናል።…”

ይህ ዜና እውነት ነው፡፡ ሳሪስ አካባቢ የሚኖር አንድ ወዳጄ ቤተሰቦቹ ዕድሉን በማግኘታቸው ከአዲስአበባ ተጠርቶ መኖሪያ ቤት ማግኘቱን እንደተአምር ነግሮኛል፡፡ ወዳጄ “ቁልፉን እስክረከብ አላመንኩም ነበር” ሲል ገረሜታውን አክሎ አጫውቶኛል፡፡

አሁን ጥያቄው ባለፉት ዓመታት ከሚኖሩበት ቀዬ የመፈናቀል አደጋ የገጠማቸው ወገኖች ለምን ተካሱ አይደለም፡፡ ገበሬዎቹ ከዚህም በላይ ሊካሱ እንደሚገባ በግሌ አምናለሁ፡፡ ግን ከልማት ጋር ተያይዞ የመፈናቀል አደጋ የገጠማቸው በአዲስአበባ ዙሪያ የሚኖሩ ገበሬዎች ብቻ አይደሉም፡፡

በሌሎች የኦሮሚያ አካባቢዎች፣ በአማራ፣ በጋምቤላ፣ በቤንሻንጉል፣በአፋር፣ በድሬደዋ፣ በሐረሪ…ተመሳሳይ ክስተቶች ባለፉት ዓመታት አጋጥመዋል፡፡ ችግሩን ካሳ በመስጠት መፍታት ይቻላል የሚል ውሳኔና የፖለቲካ ቁርጠኝነት ካለ ትግበራው በሁሉም አካባቢዎች በተመሳሳይ ሁኔታ መፈጸም ነበረበት፡፡ ግን አልሆነም፡፡ ይህ የአሰራር ክፍተት በሌሎች አካባቢዎች ነገና ተነገወዲያ ለሚነሱ ተመሳሳይ የካሳ ጥያቄዎች በምን መልኩ ለማስተናገድ ታስቦ ይሆን የሚል ጥያቄን ያስነሳል፡፡

እርግጥ ነው፤ የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ከአስር በወራት በፊት ለልማት ተነሺ አርሶአደሮች የጋራ መኖርያ ቤት ይሰጥ ብሎ ወስኖ ነበር፡፡ ውሳኔው በልማት የተነሱ ወገኖችን ብቻ የሚመለከት ነበር፡፡ አፈጻጸሙ ግን በልማት ያልተነሱ ወገኖች ጭምር በስጦታ መልክ እንዲንበሸበሹ መደረጉ የካቢኔው ውሳኔ መቀልሱ ብቻም ሳይሆን ምን እየተደረገ ነው የሚል ጥያቄን ያጭራል፡፡

ገዥው ፓርቲ ኦዴፓ/ኢህአዴግ የፌደራል የጠ/ሚኒስትርነቱን ቦታ በመሪነት የያዘ ነው፡፡ የፓርቲው ሊቀመንበር የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው፡፡ ገዥ ፓርቲው በልማት ምክንያት በተመሳሳይ ሁኔታ የተፈናቀሉ በሌሎች ክልሎች የሚገኙ ወገኖች ተመሳሳይ ጥያቄ ቢያቀርቡ በምን አግባብ ሊያስተናግድ እንደሚችል የሚያሳይ ሕግና ሥርዓት ሳይዘረጋ አድሎአዊ አሰራር ለማስፈን መሮጡ ኃላ ላይ የማይወጣው ችግር ውስጥ ሊጥደው እንደሚችል በቅጡ የተረዳ አይመስልም፡፡

ም/ከንቲባ ታከለ ኡማ የኢትዮጵያዊነት፣ የአንድነት ስብከቱን መሬት ላይ ሊያሳይ ካልቻለ ወይንም የሚናገረውና የሚሰራው የሚለያይ ከሆነ የከተማዋ ሕዝብ ወክሎ እንደምን በከንቲባ መቀመጥ ይችላል?

ሌላው ቢቀር በአዲስአበባ የተገነቡት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ከአስር ዓመታት በላይ ከሕዝብ ከነዋሪው በተሰበሰበ ገንዘብ የተሰሩ መሆናቸውን እንደምን ይረሳል? በእነጃዋር መሐመድ አነሳሽነት የተቃውሞ ሰልፍ ምክንያት የወጣላቸውን ዕጣ ከአስር ወራት በላይ መረከብ ያልቻሉ ነዋሪዎች ከዛሬ ነገ መፍትሔ እናገኝ ይሆን በሚል በተስፋ ባሉበት በዚህ ወቅት እንዲህ ዓይነት አድሎአዊ ሥራ ማከናወን የኦሮሞን ሕዝብ እንደምን መጥቀም ሊሆን ይችላል?

እንዲህ በድብቅ በሚሰራ ሸፍጥ የኦሮሞን ሕዝብ ዘላቂ ተጠቃሚ ማድረግስ ይቻላል ወይ? እንዲህ አይነቱ ዓይን ያወጣ የተረኝነት አባዜ የኦሮሞ ሕዝብ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር በሰላምና በፍቅር እንዲኖር ያደርገዋል ወይ የሚለውን በቅጡ መመለስ ይኖርበታል፡፡
የተከበሩ ከንቲባ ታከለ ኡማ ከልብ የከተማዋን ነዋሪ የሚወዱ ከሆነ (በተደጋጋሚ እወዳቹሃለኹ ሲሉ ሰምቻለኹና) ይህ ዓይነቱ አድሎአዊ አሰራር ለምን ሊከናወን እንደቻለ ማብራሪያ እንዲሰጡበት እንደአንድ ዜጋ እጠይቃለኹ፡፡

(ጫሊ በላይነህ)

Continue Reading
Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top