Connect with us

በሰሞኑ ሁከት ከ70 እስከ 80 የሚደርሱ ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል

"አጥፊዎች በሕግ ሊጠየቁ ይገባል" የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን
Photo: Facebook

ህግና ስርዓት

በሰሞኑ ሁከት ከ70 እስከ 80 የሚደርሱ ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል

በተከሰተው ሁከት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ የተሳተፉ አካላት በሕግ ሊጠየቁ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አሳሳበ።

ኮሚሽኑ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጠው መግለጫ በኢትዮጵያ የተጀመረው የለውጥ እና ተሃድሶ እርምጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ተጨባጭ ውጤቶች እንዳስገኘው ሁሉ ውስብስብ ተግዳሮቶችም እየገጠሙት ይገኛል ብሏል።

በተለይም ከጥቅምት 12 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በተቀሰቀሰው ሁከት የተሞላ ነውጥ የበርካታ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን እና የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት መድረሱን ጠቅሶ፥ የህግ በላይነትን በእጅጉ የተፈታተነ እና መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶችን ከፍተኛ አደጋ እና ስጋት ላይ የጣለ ክስተት መሆኑን ገልጿል።

በዚህ ሁከት ምክንያት እስከ አሁን ባለው መረጃ ከ70 – 80 የሚደርሱ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን እና ከዚህ ውስጥ 10 ያህሉ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በተፈጠረ ግጭት በጥይት ተመተው መሞታቸውን ጠቁሟል።

ከዚህ ባለፈ ግን አብዛኛዎቹ ሰዎች በሁከቱ በተሳተፉ ሰዎች እጅግ አሰቃቂ በሆነ መንገድ በግፍ እና ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በዱላ፣ በድንጋይ እና በስለት ተደብድበው እንዲሁም በእሳት ተቃጥለው ተገድለዋልም ነው ያለው።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ የአካል እና የሥነ ልቦና ጉዳት እንደደረሰባቸው አስታውሶ፥ በሚሊየኖች የሚገመት የግለሰቦች፣ የሕዝብና የሃገር ንብረት ወድሟልም ነው ያለው በመግለጫው።

እንዲሁም የሃይማኖት ተቋማት ሆን ተብሎ በተፈጸመ ጥቃት ለጉዳት መዳረጋቸውን በማንሳትም፥ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ቅሬታ ወይም ጥያቄ በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ ሊቀርብ የሚችልበት ምቹ ሁኔታ መኖሩን አውስቷል።

ድርጊቱ እና ያስከተለው ጉዳት የሕግ የበላይነትን፣ የሃገር ሰላም እና ሥርዓትን በአደባባይ በመገዳደር እና በመጣስ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ቀውስ ማስከተሉን የጠቀሰው ኮሚሽኑ፥ በየደረጃው በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ በጥፋቱ ተሣታፊ የሆኑ አካላት በሕግ ሊጠየቁ እንደሚገባም አሳስቧል።

የድርጊቱ ተሳታፊዎች በደረሰው ጥፋት ማዘን፣ መፀፀት እና ለሕግ የበላይነት መከበር የመተባበር ኃላፊነት እና ግዴታ እንዳለባቸውም አንስቷል።

መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥና አጥፊዎችን በሕግ ፊት ለማቅረብ እንደሚሠራ መግለጹ ተገቢ መሆኑን በመጥቀስም፥ ይህ የመንግስት ኃላፊነት እና ተግባር በሕጋዊ ሥርዓት ሊተገበር ይገባልም ብሏል።

ህብረተሰቡም ለሚደረገው የወንጀል ምርመራ ሥራ በመተባበር ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን እና ሰብዓዊ መብቶች ሁሉ እንዲከበሩ የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዝም ጠይቋል።

(ምንጭ:- ፋና)

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top