Connect with us

የም ቦር ተራራ ወጥቶ መድኃኒት ሲለቅም አብሬ ነበርሁ

የም ቦር ተራራ ወጥቶ መድኃኒት ሲለቅም አብሬ ነበርሁ

ባህልና ታሪክ

የም ቦር ተራራ ወጥቶ መድኃኒት ሲለቅም አብሬ ነበርሁ

የም ቦር ተራራ ወጥቶ መድኃኒት ሲለቅም አብሬ ነበርሁ፤
ከስራስሩ አንዱ ምናል ሀገሬን ቢፈውሳት፤

(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም የም ልዩ ወረዳ በየዓመቱ ጥቅምት 17 ቀን የሚከናወነውን የመድኃኒት ለቀማ ሥነ-ሥርዓት ታድሟል፡፡ ምናለ ሀገሬን ከስራ ስሩ አንዱ በፈወሳት ሲል ውሎውን እንዲህ ይዘግብልናል፡፡) | ከሄኖክ ስዩም በድሬቲዩብ

የሞች ማልደው ተነስተዋል፡፡ ከየአቅጣጫው ወደ ቦር ተራራ እየመጡ ነው፡፡ ቦር የጉም ጋቢ ለብሶ ቁልቁል ተመለከተኝ፡፡ ሽቅብ አየሁት፡፡ ማደበሪያ ያነገቱ ሰዎች ወደ ተራራው አናት እየወጡ ነበር፡፡ ዛሬ ጥቅምት 17 ቀን፤
ቦር የእጽዋት አምባ ነው፡፡ ቦር የፈውስ ማማ ነው፡፡ ቦር የተፈጥሮ ፋርማሲ ነው፡፡ የሞች ይሄንን ያውቃሉ፤ ጠብቀውታል፡፡ እሱም ከበሽታ ጠብቋቸዋል፡፡ ከቀደሙት የወረሱት በተፈጥሮ የመፈወስ ጥበብ ሀገራዊ እሴት ነው፡፡ ትልቅ እውቀት ነው፡፡ እኔ እዚህ ነኝ፤ ይሄንን እያየሁ፡፡

በየም ባህል ጥቅምት 17 ቀን ጠዋት ሰው ሁሉ ወደ ቦር አናት ይወጣል፡፡ አሁን እንደማየው አንካሴ ይዞ ምድር ይምሳል፡፡ ሁሉም እጽ መድኃኒት ነው፡፡ እዚህም እዚያም ከየዓይነቱ ይቀጥፋሉ፡፡ ቦር አረንጓዴ ነው፡፡ ቀለሙ ይማርካል፡፡ ደግሞ ደርሶ ጉም ይወድቅበታል፡፡ በጉም የተዋጡ ሰዎች ከአበባውም ከቅጠሉም እየቀጠፉ ወደ አነገቡት ማዳበሪያ ይከታሉ፡፡

የአመት የመድኃኒት አስቤዛ ዛሬ ነው የሚሰበሰበው፤ የም በእጽዋት ጥበብ አስቀድሞ በሽታን ይከላከላል፡፡ ቀጥሎ ህመምን ያስወግዳል፡፡ ፈውስን ከምድር ገጸ በረከት የሚያገኝ ጥበበኛ ህዝብ ነው፡፡ ቦር ላይ እያየሁ ያለሁት ይሄንን ነው፡፡

ይጠፋ ይሆን ብዬ ስሰጋ ተስፋ የማደርግበት ሌላ ክስተት አየሁ፤ ህጻናት ልጆች ወጣቶች ተራራው ገደል ላይ ተንጠልጥለው መድሃኒት ይለቅማሉ፤ አዲሱ ትውልድ በአባቶቹ መንገድ እየሄደ ነው፡፡

ከዚህ እጽ አንዱ ምናለ ሀገሬን በፈወሳት ስል ተመኘሁ፡፡ አሁን አንዱን ነገራችንን ነጥሎ ማከም ሞኝነት ነው፡፡ ሁለመናችን ታሟል፡፡ የየም እውቀት ከእጽዋት የውስጥም የውጪም ደዌን ይፈውሳል፡፡ እዚህ እጽዋት መካከል አለመደማመጥን የሚያሽር እጽ ይኖር ይሆን?

ፈዘዝኩ፤ አሰብኩ፤ ትካዜ ሩቅ ወሰደኝ፡፡ የራሳችንን ነገር ሁሉ ጥለናል፡፡ የጣሉትን ሁሉ አንስተናል፡፡ ስልጣኔያችን ባህር ማዶውን እንዲመስል ደከምን፤ ክኒን ያጋበስነውን ያክል እንደ ምዕራባውያኑ መደማመጥን ኮርጀን ቢሆን የት በደረስን፤
ይሄ ትልቅ እውቀት ነው፡፡ ሀገረሰባዊ ጥበብ ነው፡፡ ከአባቶች የወረደ ነው፡፡ ለልጆች ተስፋ ሆኗል፡፡ የሞች እንዲህ ባለው ጥበብ እስከ ቀጣዩ ጥቅምት 16 ቀን የሚያቆዩትን የአመት እጽዋት ከፈውስ ተራራቸው ላይ ሲለቅሙ በሀገሬ ጉዳይ በተሰበረ ልብ ሆኜ አብሬ አለሁ፡፡ አንድም እንዲህ ካለው የአባቶቻችን ጥበብ ሀገር የሚፈውስ ሌላ እውቀት ይታደገናል ብዬ አንድም በራሳችን በተተኪዎቹ አፍሬ የም ተራራ ጫፍ ቆሜያለሁ፡፡ የየም አባቶች በርቱልኝ፤

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top