Connect with us

“ሥርዓት አልበኞች ለፍርድ ይቀርባሉ!!!” – የግሎባል አልያንስ መግለጫ

"ሥርዓት አልበኞች ለፍርድ ይቀርባሉ!!!" - የግሎባል አልያንስ መግለጫ
Photo: Facebook

ህግና ስርዓት

“ሥርዓት አልበኞች ለፍርድ ይቀርባሉ!!!” – የግሎባል አልያንስ መግለጫ

በአርቲስት ታማኝ በየነ የሚመራው ግሎባል አልያንስ (ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት) ባወጣው መግለጫ የጠ/ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ አስተዳደር እየተከተለው ነው ያለውን ዘውጋዊና ፓለቲካዊ አድልዎ በአስቸካይ እንዲቆምና የሁሉም ዜጎች መብት በእኩልነት እንዲጠበቅ ጠየቀ፡፡(የመግለጫው ሙሉ ቃል እነሆ)
………
ሥርዓት አልበኞች ለፍርድ ይቀርባሉ!!!
የግሎባል አልያንስ መግለጫ

በቅድሚያ ስሞኑን በኢትዮጵያ ውስጥ በኦሮሚያ ክልል ሃላፊነት በጎደለውና “እኛ የቄሮን ጉልበትና አቅም አሳይተናል ” እያለ የሚፈክረው አክትቪስት ነኝ ባዩ ባስተላለፈው ጥሪ ተነሳስተው አብዛኛውንና ስላማዊውን የኦሮሞ ወጣት የማይወክሉ ሥርአት አልበኞች በስላማዊ ዜጎች ላይ ባደረሱት ብሄርና ሃይማኖት ተኮር ጭፍጨፋ በአስቃቂ ሁኔታ ህይወታቸውን ላጡ ፣ ለቆስሉና ቤት ንብረታቸው ለወደመባቸው ከቄያቸው ለተፈናቀሉ፣ወገኖቻችን በሙሉ ለደረስባቸው ጥቃት ዘግናኚና ኢስብአዊ ጥቃት የተስማንን ልባዊና ከፍተኛ ሃዘን እየገለጽን ይህንን ከስበዓዊነትና ከኢትዮጵያዊነት ተፃራሪ የሆነ ግፍና አስቃቂ ድርጊት አጥብቀን እናወግዛለን።

ላለፍት 28 አመታት አፋኝና አምባገነናዊ በሆኑ የአገዛዝ ስርዓቶች ውስጥ የቆየችው አገራችን የዛሬ ሁለት አመት በህዝብ፤ በተለይ በወጣት ልጆቿ ከፍተኛ መስዋእትነት ወደ ሌላ ምእራፍ ተሽጋግራለች። ይህ የሺዎች ህይወት የተገበረበት፣ በአስር ሺዎች የሚቆጥሩ ለእስር እና ለከፍተኛ እንግልት የተዳረጉበት ለውጥ በአገዛዝ ቁንጮ የነበረውን የህወሃት ቡድን ከፖለቲካና ከኢኮኖሚ የበላይነቱ ገሽሽ አድርጎ፤ አገሪቱን ከደም መፋስስ እድኖ ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ጎዳና ይመሩናል በሚል እምነትና ተስፋ፤ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከገዢው ፓርቲ ከኢህአዴግ አብራክ ለወጡት የለውጥ ሃይሎች ድጋፍ በመስጠት መልካም ውጤቶችን ሲጠባበቅ ቆይታል ። ለውጡን የሚመሩት ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ የዚህ ተስፋ ተምሳሌት ሆነው የተገኙበት ዋናው ምክንያት ኢትዮጵያዊነትንና ኢትዮጵያን ስላስቀደሙ ነበር። በመጀመርያው ቀን የፓርላማ ንግግራቸውና ከዚያም በኋላ ከኢትዮጵያዊያን ጋር ባደረጓቸው ውይይቶች ሁሉ ባለፋት የጭካኔ፤ የጭቆናና የምዝበራ አመታት ለተፈጸሙት የስብአዊ መብት ጥስቶች ሁሉ መንግስት እና ድርጅታቸው ተጠያቂ መሆናቸውን፤ ከዚህም አልፈው “እኛም ሽብርተኞች ነበርን፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅርታ ያድርግልን” በማለት ስሜቱ ተጎድቶ ለነበረው ህዝብ ትልቅ መጽናኛ ሆነዋል።

ሕዝቡም የፓለቲካ እስረኞቹ መፈታት፣ የፍትህ ተቋማትን ጨምሮ የሌሎች መንግስታዊ ተቋማት ለማጠናከር የተጀመረውን እንቅስቃሴ ከግምት በማስገባት በለውጡ ላይ እና ለውጡን በሚመሩ ስዎችም ላይ ትልቅ ተስፋ ስንቆ ነበር። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ በቡራዩ ከተማ የተፈጸመው በማንነት ላይ ያነጣጠረ የጅምላ ጭፍጨፋ ለብዙ ዜጎች በአስቃቂ ሁኔታ ሕይወት መጥፋት ምክንያት ሆናል። ብዙዎቹም የአካልና የስነልቡናዊ ቀውስና ጉዳት ደርሶባቸዋል። ከቤትና ከንብረታቸው የተፈናቀሉትም ቁጥራቸው ቀላል አልነበረም። ይህ ግፍና ጭካኔ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ነገር ግን ጥቃቱን ያቀነባበሩትና የመሩት የፓለቲካ መሪዎችና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ለፍርድ ይቀርባሉ ተብሎ ቢነገርም ወንጀላቸው እስካሁን ድረስ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ አልተደረገም። ባለሥልጣናትም ሆኑ ጨፍጫፊዎቹ ሊማሩበት አልቻሉም። ወንጀልና ጭካኔ እንደ ልምድና እንደ ተራ ነገር ታለፈ። አሁንም እተደገመ።

እንደውም ይባስ ብለው ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውን የአዲስ አበባን ወጣቶች በግፍ በማስር ከአንድ ወር እንግልትና ስቃይ በሃላ “ሁለተኛ አይለመደንም ብለው” ከእስር እንዲለቀቁ ተደርገዋል። በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ በቡራዩ ብሄር ተኮር ጥቃት ያደረጉት ወንጀለኞች በህግ ባለመጠየቃቸው ባለፋት ሁለት አመታት በርካታ ተመሳሳይ ጥቃቶች ተከስተዋል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ሲንገላቱ የከረሙበት አሳዛኝ ሁኔታ ተፈጥራል። በአገሪታ ውስጥ የታየው ስርአተ አልበኝነት እና የህግ የበላይነት መፋለስ እያደር አድማሱን አስፍቶ እና በተደራጁ አክራሪዎችና ጽንፈኞች እየተገፋ ዛሬ አገሪቱ የተጋረጠባትን ቀውስ ፈጥራል። በስሞኑም ያየነው መንግስት ቀለብ ከሚስፍርላቸውና ጥበቃ ከሚደረግላቸው መካከል አንዱ አክቲቪስት ተብየው ያስራጨውን ጥሪ ተከትሎ በደብረዘይት፣ በአዳማ፣ በአርሲ፣ በባሌ ሮቢና በዶዶላ፣ በሃረር፣ በድሬደዋ፣ እና በአዲስ አበባ ዙሪያ ሥርአተ አልበኛ ቡድኖች ባደረሱት ጥቃት ወገኖቻችን በአስቃቂ ሁኔታ የተገደሉና በመቶዎች የሚቆጠሩ ከባድና ቀላል የመቁስል አደጋ የደረስባቸው መሆኑን ቤት ንብረታቸው የተቃጠለባቸው እና በአሁኑ ስአት መውደቂያ የሌላቸው ወገኖቻችን እጅግ በርካታ መሆናቸውን በመገንዘብ አለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት (ግሎባል አልያንስ) እንደተለመደው ዲያስፓራውን አስተባብሮ የወገን አለኝታነታቸውን በተግባር እንዲያሳዩ የሚከተሉት እርምጃዎችን ለመውስድ በቁርጠኝነት መወስኑን ለመላው የኢትዮጵያና ለአለም ህዝብ ይገልጻል ።

1- የጠ/ሚንስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ መንግስት ዋንኛው ተቀዳሚ ተግባሩ የህግ የበላይነት ማረጋገጥ የዜጎችን ህልውና በስላም የመኖር ዋስትና ማረጋገጥ ሊሆን ይገባል፡፡ ሆኖም እስካሁን በተከታታይ እየታየ ያለው ሁኔታ የተለየ ገጽ ያሳያል። ለምሳሌ ወንጀለኞች፣ ነፍስ ገዳዮች፣ ደብዳቢዎች፣ ብሄርና ሃይማኖት እየለዩ ግጭት የሚፈጥሩ ጠብ አጫሪዎችና ሚዲያ እየተጠቀሙ ግጭቶች እንዲከስቱ፣ ባንኮች እንዲዘረፋ የሚቀስቅሱ ግለስቦችና ቡድኖች ተጠያቂ አልሆኑም። በተገላቢጦሽ አንዳንድ የፌዴራልና የክልል ባለስልጣናት “እንክብካቤም” ሲያደርጉም ይስተዋላል የተጎዱት ወገኖች አድላዊ በሆነ ደረጃ ግፍና በደል ሲደርስባቸው ይታያሉ ። ይህ ዘውጋዊና ፓለቲካዊ አድልዎ በአስቸካይ እንዲቆምና የሁሉም ዜጎች መብት በእኩልነት እንዲጠበቅ እንጠይቃለን ። ጠ/ሚንስትሩ መንግስትና የሚመሩት ገዢ ፓርቲ ማንኛውንም የመንግስት ባለስልጣን በአደባባይ ቦታዎች ሃላፊነት የጎደላቸውን ንግግሮችን ዛቻዎች ከማድረግና ያልተናበቡ መግለጫዎችን በመስጠት የህዝቡ ስጋትና ጥርጣሬ እንዲጨምር ከማድረግ እንዲቆጠቡና የተጣለባቸውን ሃላፊነት በብቃት ባለመወጣታቸው ተጠያቂ እንዲሆኑ አበክረን እናሳስባለን።

2- በመንግስት የሚወስደው እርምጃ እንደተጠበቀ ሆኖ በኛ በኩል ማንኛውም ግለሰብ፣ ምሁር፣ ቡድን፣ ወጣቶች፣ በግል ሆነ በጋራ በብሄራቸው ተደራጅተው የሌሎች ብሄር ተወላጆች በሚኖሩበት አካባቢ በመሄድ ብሄርና ሃይማኖት ተኮር ግጭት በማስነሳት ዜጎች ሃብትና ንብረት አፍርተው ከሚኖሩበት ቦታ በመሳሪያ፣ በዱላ፣ በገጀራ፣ እና በድንጋይ የዜጎችን ህይወት ያጠፋትን፣ ያቆስሉትን፣ ያፈናቀሉትን፣ ቤት ንብረታቸውን ያቃጠሉትን ግለሰቦች በደረስን መረጃ መስረት በማድረግ አለም አቀፍ ጠበቆችን በማስባስብ ለአገር ውስጥና ለዓለም አቀፍ ፍርድ ለማቅረብ መወስናችንና በዝግጅት ላይ መሆናችንን ማሳወቅ እንወዳለን።

3- ማንኛውም ግለሰብ የፈለገውን እምነት የመከተል መብቱ በአለም አቀፍ ህግ የተጠበቀ ቢሆንም ከ50 ሚሊዮን በላይ ተከታዮች ያሉት የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አገልጋዮች ያረዱትንና አብያተክርስቲያናትን ያቃጠሉትን፣ ምእመናን አስገድደው የደፈሩትን እና በአንዳንድ መስጊዶችም ላይ ጉዳት ያደረሱትን ወንጀለኞች ለፍርድ እንዲቀርቡ ጥረት እናደርጋለን።

4- ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እንደተጠበቀ ሆኖ ሃላፊነት በማይስማቸውና ሚዛናዊነት የጎደለው የሃስት ወሬ በሚያስራጩ ሚዲያዎች በተለይም ብሄር ከብሄር፣ ሃይማኖት ከሃይማኖት እንዲጋጩ ቅስቀሳ በሚያደርጉ የሚዲያ ተቃማት ሃላፊዎችና ባለሙያዎች አስራራቸውን እንዲመረምሩና እንዲያስተካክሉ እያስገንዘብን በፌስቡክ፣ በቲውተር፣ በዩቲዩብና በመሳስሉት ሚዲያዎች ተጠቅመው ህዝብን የሚያውክ ስራ የሚስሩትን በመከታተልና በማጋለጥ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ጋር በመተባበር ተገቢ እርምጃ እንዲወስድባቸው ተግተን እንስራለን።

5- በቅርቡ በተቀስቀሱ ብሄር ተኮር ጥቃቶች ለሞቱት ቤተስቦች፣ ለቆስሉትና ለተፈናቀሉት ወገኖቻችን እርዳታ የሚውል የጎ ፈንድ ሚ (gofundme) አካውንት ስለከፈትን ከዚህ በፊት በቡራዩና በጌዲኦ የተባበራችሁን ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በአፋጣኝ ወገኖቻችሁን ለመርዳት እንድትረባረቡ በእግዚአብሔር ስም ጥሪያችንን እናቀርባለን። ለወገን ደራሽ ወገን ነውና ለጥሪው አፋጣኝ ምላሽ እንደምትስጡን እንተማመናለን።

በመጨረሻም ለምንወዳችሁ እና ለምናከብራችሁ አዋቂና ታጋሽ ለሆናችሁ ኢትዮጵያውያን በሙሉ “ሊነጋ ሲል ይጨልማል” እንደሚባለው እስካሁን ድረስ ያንን አስከፊ ግፍና መከራ በልበ ስፊነት፣ በተስፋና፣ በእምነት እንዲሁም በጽናት ታግስህ እንዳሳለፍከው ሁሉ ዛሬም መከራው ቢበዛም፣ ችግሩ የከፋም ቢሆንም የኢትዮጵያ አምላክ አይተዋትምና አይዛችሁ፣ በርቱ እኛ በውጪ ብንኖርም በመንፈስ ሁል ጊዜም ከናንተው ጋር ነን።

ከታገስነው ሁሉም ስለሚያልፍ ግሎባል አልያንስ ባለው አቅም ሁሉ ለወገኖቻችን ተስፋ ለመሆን የሚቻለውን ሁሉ ለማድረግ ያላስለስ ጥረት እንደሚያደርግ ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን የዜጎች ሕልውና እንዲረጋገጥና የሁሉም መብት እንዲከበር በመተባበርና በአንድነትና በቆራጥነት ዘብ መቆም የሁላችንም ግዴታና ሃላፊነት ነው።
ኢትዮጵያ በዜጎቻ ተከብራና በአንድነት ፅንታ ለዘላለም ትኑር!!!
ለበለጠ መረጃ

አለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት (ግሎባል አልያንስ) ድህረ ገፅን ይከታተሉ RescueEthiopians

ከታላቅ አክብሮት ጋር
ታማኝ በየነ ሊቀመንበር

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top