Connect with us

ለሁለት ጌቶች የምንገዛ ኢትዮጵያ …

ለሁለት ጌቶች የምንገዛ ኢትዮጵያ ...
Photo: Facebook

ህግና ስርዓት

ለሁለት ጌቶች የምንገዛ ኢትዮጵያ …

ሳይነግሩን ይፋቀራሉ፤ ሳይነግሩን ይጋጫሉ፡፡ እኛ በጠባቸውም በፍቅራቸውም ሟች ነን፡፡

ሌላው ቢቀር ጠቅላይ ሚኒስትሩን ስለደገፍን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጸጥታ ሃይሎች የምንታሰርባት ሀገር ዜጎች ነን፤
****
ከሰለሞን ሃይሉ

ኢትዮጵያ ዛሬም እንደ ትናንቱ ቡራ ቡሬ ናት፡፡ ዛሬም የሚያስቅ ነገር የሚታይባትና እየሳቅን የምንሞትባት ሀገር መሆኗን ቀጥላለች፡፡ በርካታ በሀሳብ ሀሳብን የሞገቱ ዜጎች ዛሬም እስር ቤት ታጉረው በፍርድ ቤት ቀጠሮ ይጉላላሉ፡፡ ዛሬ ፍትሕ ይስፈን ብሎ አደባባይ መውጣት ያሳስራል፤ በተቃራኒው ሰው መግደል ያስከብራል፡፡ ገዳዮች የሚንቆለጳጰሱባት ሀገር አለችን፤ አደባባይ ወጥቶ ከገዳይ ጋር አንለያይ አንድ እንሁን በሚል የሚማጸን ፓርቲ እየመራን ነው፡፡

ሀሳብ ይዞ ሀሳብን ለምን ያለውን ሰው እስር ቤት የከተትነው ቀን ያኔ ገዳይ ጎዳና ወጥቷል፡፡ ሜንጫ ይዞ አደባባይ የሚሳለቀውን ሰው በክብር እያኖሩ በክብር መኖር የሚገባውን ሰው ካሳደዱት ሀገር አይረጋም፡፡

ጃዋር እኔ በምመራው ንቅናቄ ለስልጣን የበቁት ዶክተር አብይ በእኔ ላይ በመነሳታቸው አዝኛለሁ ብሏል፡፡ ችግሩ እሱን ሲከፋው ሰው ይሞታል፡፡ ችግሩ እሱ ሰጋሁ ሲል የማይቃጠል ንብረት የማይዘጋ መንገድ የማይፈስ ደም የለም፡፡

ይሄንን መቆጣጠር የማይችል መንግስት ቢያንስ ጃዋር እንዳይሰጋ ጃዋር እንዳይፈራ በማድረግ መቶ ሚሊዮን ህዝብ አብሮ እያስፈራራ በመኖር የመኖር መብቱን ሊያከብርለት በተገባ ነበር፡፡ ይህ ካልሆነ ደግሞ ጃዋርን ሲነኩት የሚነካው ፈንጂን ማምከን ያስፈልግ ነበር፡፡ ሁሉን በድብቅና በሴራ ማድረጉ ደግሞ ለማንም አይበጅም፤

እኛ ኢትዮጵያውያን ሁለት ጌቶች አሉን፤ መንግስታችን ሁለት ነው፤ መሪዎቻችንም እንዲሁ ሁለት ናቸው፡፡ መሪ ፓርቲያችንም ሁለት ነው፡፡ ሁለቱም ሊገዙን ይፈልጋሉ፤ ተመካክረው አይገዙንም፡፡ አንዱ በሌላው ሲከፋ ሟች እኛ ነን፡፡ አንዱ ሌላው ላይ ፊቱን ሲያዞር ደማችን ይፈሳል፡፡ አንዱ ከሌላው ሲታረቅ በግድ ጨፍሩ እንባላለን፤ አንዱ ሌላውን የወደደ ቀን አብረን ካላበድን ይዛትብናል፡፡ ሳይነግሩን ይፋቀራሉ፤ ሳይነግሩን ይጋጫሉ፡፡ እኛ በጠባቸውም በፍቅራቸውም ሟች ነን፡፡

ለሁለት መንግስት መገዛት ከባድ ቢሆንም በዓለም ሁለት መሪ ያላቸው ዜጎች ሆነን በድል ተወጥተንዋል፡፡ እኛ የቻልነው ያቃታቸው ገዢዎቻችን ናቸው፡፡ ለሁለት መሪ መገዛታችንን ቦታ አልሰጡትም እንደውም ሽልማታቸው መከራ ሆነ፡፡ እናም ሞት ተሸለምን፤ ሞትን፡፡

የሚያስገርመው በራሱ ቴሌቨዥን መንግስትና መሪዎቹ ላይ ጭምር እየዛተ አመጹን የመራውን ሰው መንግስት አደባባይ ወጥቶ ጥፋተኛውን ጠቁሙኝ ይለናል፡፡ በዚህ ባንስቅ ተሰቃዩ ያለን ነንና አብይ ሌባ ብለው ለወጡ ነውጠኞች አብይ የኛ ብሎ ሰልፍ የወጣ ደጋፊ ወንጀለኛ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትራቸውን ደግፈው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመሩት የጸጥታ መዋቅር ለመታፈስ የበቁት ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ይመስሉኛል፡፡

ዛሬም በአንዳንድ ኦሮሚያ ከተሞች አጥፊዎቹ ሳይሆኑ ተከላካዮቹ እየታፈሱ ነው፡፡ ምክንያቱም ጥቃት ፈጻሚው ጠቋሚ ነውና፤ ጥቃት ፈጻሚው የፖሊስ አጋር ነው፡፡ ቀድሞውንም ጥቃት ስሙ ግጭት ሲባል ፍትሕ ተዛብቷል፡፡ ፍትሕ አሁንም ከመከራው ያወጣል፤ ፍትሕ ፍትሕ ፍትሕ

Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top