Connect with us

የቤተመንግሥቱ መካሪዎች

የቤተመንግሥቱ መካሪዎች
YouTube: Walta TV

ፓለቲካ

የቤተመንግሥቱ መካሪዎች

የቤተመንግሥቱ መካሪዎች | (በኃይሉ ሚዴቅሳ ፍስሃጽዮን)

ከጥቀት ቀናት በፊት የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ሆነው ቤተመንግሥት ውስጥ ካሉት አንዱ የሆኑት ዳኒኤል ክብረት (ዲያቆን) አንድ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡ ይኸውም የውጭዎች ጫናና ተጽእኖ በጠቅላይሚኒስትሩ ላይ አለ ወይ የሚል ነበር፡፡

አማካሪው (በነገራችን ላይ የምን አማካሪ እንደሆኑ ባላይገልጹም ስለ ኢኮኖሚም፣ ስለ ፖለቲካም፣ ስለ ኢሕአዴግም፣ ስለ ሚዲያም እንደ አማካሪ ሲያወሩ ነበር) እንደተለመደው በተረት የተዋዛ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡እንዲህ በማለት ‹‹ወንዝ ሊሻገር ባሕሩ ውስጥ የገባ ሰው፣ውሃ ሳይነካው ይውጣ ማለት አይቻልም›› አሉ፡፡

ይህ አደገኛ ነገር ነው፡፡ እነ አየር መንገድና ቴሌ (የመንግሥት ኮርፖሬሽኖች) እንዲሸጡ እየተደረገ ያለው በፈረንጆቹ ትዕዛዝ እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲነገር ሰንብቶ ነበር፡፡ እኒህ አማካሪ ደግሞ በተረት እንደነገሩን እውነትነት አለው፡፡

ከሳምንታት በፊት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቱ ፕሮፌሰሩ ዓለማየሁ ገዳ ናቸው፡፡ከሁለት ሳምንታት በፊት Ethiopia’s “Homegrown” Reform: If the diagnosis is not right, it may end‐up a Wish List የሚል ጥልቅ ጽሁፍ አስነብበው ነበር፡፡ እርሳቸው አዲሱ የኢኮኖሚ ማሻሻያ አገር በቀል ሳይሆን በአይኤምኤፍና ዓለም ባንክ ትዕዛዝ የተተገበረ መሆኑን IMF Pamphlet series No. 47, 2019ን ‹‹አገር በቀል የተባለውን የጠቅላይሚኒትር ዐቢይን የኢኮኖሚ ማሻሻያ በጥሞና ለመረመረ ሰው አገር በቀል ሳይሆን ዋሽንግተን ሠራሽ እንደሆነ ይረዳል፡፡ ምክንያቱም ቢሮአቸውን ዋሽንግተን ያደረጉት ዓለምባንክና አይኤምኤፍ ታዳጊ አገሮችን ‹‹ገበያችሁን ለኛ ክፈቱ፤ ንብረቶቻችሁንም እኛ እንግዛችሁ›› ከሚለው መመሪያቸው ጋር የተመሳሰለ ስለሆነ ››ይላሉ፡፡

ይህንን ሐሣብ በተለመከተ መስረም 8-2012 በፎረም ኦፍ ፈደሬሽንስ አሰናጂነት በተጠራው ውይይት ላይ የተገኙት አቶ ክቡር ገና ‹‹የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተልዕኮና ውጤታማነት በትርፍ ቢለካ የኢትዮጵያ አየር መንገድና ኢትዮ ቴሌኮም ስኬታማ ናቸው፡፡ የልማት ድርጅቶች ከብሔራዊ ጥቅም እንጂ ከርዕዮተ ዓለም ጋር መያያዝ የለባቸውም፡፡ ይህ የዓለም ባንክን የመሳሰሉ ድርጅቶች የሚያደርጉት ጫና ውጤት ነው ፤ መንግሥት ድርጅቶቹን ወደ ግል ሲያዛውር አብሮ ሉዓላዊነቱንም እንደሚያጣ ማወቅ አለበት›› ብለው በግልጽ ተናግረዋል፡፡ ሲቀጥሉም ‹‹እነ ቻይና የዓለም ባንክና መሰሎቹ የሚያቀርቡትን ውትወታና የርዕዮተ ዓለም ጫና በመቃወም በራሳቸው መንገድ ውጤታማ ሆነዋል፤ የእነዚህን ተቋማት ምክረ ሐሳብ በመቀበል 11‚000 የመንግሥት ድርጅቶችን የሸጡት ሩሲያውያን ግን ከነበሩበት ወርደው ችግር ገጥሟቸዋል፡፡መንግሥት ድርጅቶቹን ለመሸጥ ምን መብት አለው?››በማለት በአጽንኦት ተከራክረዋል፡፡ አቶ ክቡር የቅቡልነት ቀውስ ውስጥ የገባ መንግሥት የአገርን ሀብት የመሸጥ መብት ከየት አገኘ ማለታቸው ይመስላል፡፡

ለዚህ ጉዳይ ማብራሪያ የሰጡትየገንዘብ ሚኒስቴር አማካሪ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) ‹‹ማንም የዓለም ባንክንም ሆነ የዓለም አቀፉን የፋይናንስ ኮርፖሬሽን ባንዲራ አያውለበልብም፡፡ የ‹ፕራግማቲዝም› ጉዳይ ነው›› በማለት ነበር-ሀሳቡን ያጣጣሉት፡፡ከዚህ በላይ ባንዲራ አውለብላቢነት ከየት እንደሚመጣ ግን አላብራሩም፡፡ የዚህ ሁሉ ምንጭ ግን ከአሁኑ መንግሥት አማካሪዎች ማንነት ይመነጫል፡

የፈረንጅ መላዕክተኞች

የአሁኑ መንግሥት አማካሪዎች ረብጣ ዶላር የሚከፈላቸው አይኤምኤፍና ዓለም ባንክ ውስጥ ይሠሩ የነበሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ናቸው፡፡ ይህ ሬትን በማር ለውሶ የማቅረብ ዘዴ አዲሱ የነዚህ ተቋማት መንገድ ነው፡፡በ SAP ዘመን ቀጥታ ፈረንጆቹን ነበር የሚልኩት፡፡ አሁን ደግሞ የአገሩን በሬ በአገሩ ሰርዶ እንዲሉ የአገሬውን ዜጋ ነው የሚልኩት፡፡ በእነዚህ ሰዎች በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ታሪክ ውስጥ ምንም ሚና ያልነበራቸው፣የኢትዮጵያን ገበሬ ነባራዊ ሁኔታ የማያውቁ፣ ለፈረንጅ አለቆቻቸው የሚታዘዙ ናቸው፡፡ለቤተመንግሥቱ ቅርብ ከሆኑት ሰዎች አንዱ የሆኑት ፕሮፌሰር ሕዝቅኤል ገቢሳ ለአንድ ሚዲያ የተናሩት ይህንኑ ነው፡፡‹‹እንደ አማካሪ ጠቅላይሚኒስትሩ ቢሮ የተኮለኮሉት አብዛኞቹ በውጭ አገር የሚከፈሉ ናቸው፡፡በቢልጌትስ ፋውንዴሽን፣ በቶኒ ብሊየር ፋውንዴሽን፣ በዩኔስኮ፣ ያውቃሉ ተብለው የተሰበሰቡ ናቸው፡፡ እነዚህ ግን ከአገሪቱ ሁኔታ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው ናቸው››

እንግዲህ እነዚህ ሰዎች ‹የማንን ባንዲራ እንደሚያውለበልቡ› ግልጽ ነው፡፡ በመጀመሪያው ሥራቸው (በኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ) ላይም አገርን ጥንቅቅ አድርገው ሊሸጡ ጫፍ መድረሳቸውን አረጋግጠናል፡፡ በነገራችን ላይ የፈረንጅ ምንደኛ ሆነው፣ኢትዮጵያ ውስጥ የገቡት ዜጎች በጠቅላይሚኒስትር ጽ/ቤት በኢኮኖሚ አማካሪነትና በፕሬስ ሴክሬታሪያትነት ላይ የተቀጠሩት ብቻ ሳይሆኑ በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድርና በምርጫ ቦርድም ላይ ያሉት ናቸው፡፡ እነዚህን እነ ዩኤንዲፒ የሚከፍሏቸው ናቸው፡፡ ለዚህ ነው እነ ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገዳ (ዶ/ር) አገር በቀልም ያልሆነ፣ በአገር ልጅም ያልተሰራ ሰነድ እንደሆነ የሚገልፁት፡፡

የምዕራቡ ዓለም አስታጥቆ ከላካቸው የኢትዮጵያ መንግሥት የሽያጭና የኢኮኖሚ አማካሪዎች መካከል አሜሪካዊው ኢኮኖሚስት ሪካርዶ ሀውስማን አንዱ ነው፡፡ ይህ ሰው በላቲን አሜሪካ ተመሳሳይ ተልዕኮ ይዞ የተለያዩ አገሮችን አክስሮ የወጣ ብቻ ሳይሆን፣እንደ ቬኒዚዋላ ባሉ አገራት መፈንቅለ መንግሥት ሲያስተባብር የሰነበተ ሰው ነው፡

ሰውዬው በተለይ ደግሞ በኢትዮጵያ ላይ የረባ እውቀት እንደሌለው The Atlas of Economic Complexity የሚለው መጽሐፉ ምስክር ነው፡፡ ከስምንት ዓመታት በፊት በፃፈው በዚህ መጽሐፉ ውስጥ፣ በ2020 የኢትዮጵያ የነፍስ ወከፍ ገቢ ከ453 ዶላር እንደማይበልጥና ዓመታዊ የኢኮኖሚ ዕድገቱም ከ2.5 በመቶ እንደማይበልጥ ነው የተነበየው፡፡ ይሁን እንጂ የዓለም ባንክ ሪፖርት እንደሚያመለክተው የአገሪቱ ሕዝብ የነፍስ ወከፍ ገቢ በ2018 ብቻ 790 ዶላር ደርሷል፤ ዓመታዊ ዕድገቱም ከ10በመቶ በላይ እንደነበረ የአይኤምኤፍ ሰነድ ያሳያል፡፡ የሀውስማን ግምት ግን ነባራዊ ሁኔታን ካለማገናዘብ፣ የኢትዮጵያን ሀብት (መሬትና ሰው) ከግምት ውስጥ ካለማስገባትና የአገሪቱንኢኮኖሚያዊ ክስተቶች ካለማንበብ የሚመነጭ ነው፡፡ይህን ሰው ነው እንግዲህ እነ አሜሪካ የላኩት፡፡ ሀውስማን ያኔ ከተሳሳተ ዛሬ ትክክል ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?

(ይህ ጽሁፍ ከፍትሕ መጽሔት ላይ የተወሰኑ ሐሳቦችንና ገለፃዎችን ተውሷል)

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top