የፋሲል ግንቧ የፍቅር አዳራሽ- የጻድቁ ዩሐንስ መታሰቢያ፤
እንኳን ለሰው ለእንስሳ የተረፈው ደጉ ንጉሥ፤
****
(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ከጎንደር ነገሥታት አንዱ የኾነውን ጻድቁ ዩሐንስ ለዛሬ እንዘክረው ሲል አጭር ታሪኩን ሊነግረን ነው፡፡ ጻድቁ ዩሐንስ የንግሥና በዓለ ሲመቱ በወርሃ ጥቅምት ሲሆን በጎንደር ገናና ከነበሩ ንጉሦች አንዱ ነው ይለናል ተከታዩ ጽሑፍ፡፡)
ሄኖክ ስዩም በድሬቲዮብ
ጻድቁ ዩሐንስ ንጉሥም ጻዲቅም ነው፡፡ በጎንደር ከነገሡ ነገሥታት አንዱ ብቻ ሳይኾን በመልካም ተግባሩ የሚታወቅም ነው፡፡ የንግሥና ስሙ አእላፍ ሰገድ ነው፡፡ የነገሠው ደግሞ የዛሬ 352 ዓመት ጥቅምት 11 ቀን ነበር፡፡ አመቱ 1660 ዓ.ም. ነው፡፡
በዩሐንስ ስም ከነገሡት ነገሥታት ቀዳሚው ስለኾነ ዩሐንስ አንደኛ ይሉታል፡፡ አስቀድሞ ለንግስና ያስመረጠው ደግነቱና ለደሃ አዛዥነቱ ነው፡፡ ደግ መሆንና ለደሃ ማዘንን በመንፈሳዊ እውቀት ለረዥም ዓመታት በተከታተለው ትምህርት ተምሯል፡፡
ጎንደርን የሚጎበኝ ጎብኚ በዐፄ ፋሲል ቅጥር በጎንደር አብያተ መንግስታት ግብረ ሕንፃ ውስጥ የፍቅር አዳራሽ የምትባል ደስ የምታሰኝ ኪነ ህንፃ ይመለከታል፡፡ ያቺ ሕንፃ የጻዲቁ ዩሐንስ ቅርስና ውርስ ናት፡፡ በነገሠ በመጀመሪያው አመት የሰራት የአንድ ዘመን መገለጫችን፤
ጻዲቁ ዩሐንስ ንጉሥ ብቻ ሳይሆኑ መናኝም ናቸው፡፡ ለጥበብ እድ ክብር ነበራቸው፡፡ ጎንደር አዲስ ዓለም መስጂድን የጎበኘ እንግዳ መስጂዱ ደጃፍ ላይ በጻዲቁ ዩሐንስ ዘመን ተመሰረተ የሚል ጽሑፍ ያነባል፡፡ አገውና ጻዲቁ ዩሐንስም ብዙ ታሪክ አላቸው፡፡
ታሪካዊው የጠዳ እግዚሐር አብ ቤተ ክርስቲያንን የሰሩት እኒሁ ንጉሥ ነበሩ፡፡ አንተም አንቱም የምንላቸው የእኛ ንጉሥ፤
በአባ እንጦንስ ስምም ቤተ ክርስቲያን ተክለዋል፡፡ ጻዲቅ ማክበር ብቻ ሳይኾን በጻዲቅ ተግባር ስማቸው የሚነሳ ንጉሥ ናቸው፡፡ የተጠበሰ ዓሳ ዘሎ ባህር እስኪገባ የተሰወረን የሚናገሩ ይላቸዋል ታሪካቸው፡፡
የቤተ መንግሥቱን ደውል የደውለው ጨው ሲጭን የተገጠበ አህያ አስቀድሞ የተበደለ የሚደውለውን ደውል ደውሎ ባሰማው ድምጽ አህያ ነው ብለው ከናቁት አገልጋዪች ይልቅ ንጉሡ ተረዱትና ህግ አወጡ፤ ያም የተገጠበ አህያ እንዳይጫን የሚል ነበር፡፡ ዛሬ ሆነን ስናስበው ከሦስት መቶ ዓመት በፊት ለእንስሳ መብት ጭምር የሚቆረቆረው የቤተ መንግስት መንፈሳችን የት ገባ? ያስብለናል፤
የመደባይዋን ባላባት ልጅ ነው ያገቡት፤ እቴጌ ሰብለወንጌል ትባላለች፡፡ ከዚህች እቴጌ ዮስጦስን እያሱን እሌኒን አቤቶሁን ቴዎፍሎስንና አቤቶ ቆላዣን ወልደዋል፡፡ ስልጣንን የቆዩባት በቅድስና ቢሆንም ከአስራ አምስት አመት በላይ ሊሹት ግን አልቻሉም፡፡ በነገሡ በአስራ አምስተኛው አመታቸው ልጃቸውን ኢያሱን አነገሡ፡፡ ኢያሱ አድያም ሰገድ፤
ጻድቁ ዩሐንስ ሐምሌ 15 ቀን 1674 ዓ.ም. ይህቺን ዓለም ተሰናበቱ፤ መቀበሪያቸው ያሰሩት ጠዳ እግዜአብሔር አብ ሆነ፡፡