Connect with us

የአምስት ሺህ ተማሪ የአምስት ሺህ ቤተሰብ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መላ

የአምስት ሺህ ተማሪ የአምስት ሺህ ቤተሰብ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መላ፤
Photo: የጎንደር ዩኒቨርሲቲ

ነፃ ሃሳብ

የአምስት ሺህ ተማሪ የአምስት ሺህ ቤተሰብ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መላ

አንድ ተማሪ የጎንደር ቆይታውን ሲያጠናቅቅ ከዲግሪው ጋር “እታታይ” የሚላት ስፍስፍ የአደራ እናት አግኝቶ ይመለሳል፡፡

የአምስት ሺህ ተማሪ የአምስት ሺህ ቤተሰብ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መላ፤
ልጆቹን ጎንደር የላከ ቤተሰብ ዲግሪም ዝምድናም ያተርፋል፤
(ሄኖክ ስዩም በድሬቲዮብ)

ጎንደር በአበው ዳና ሄዳለች፡፡ ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ አበ ልጅ፣ የዐይን አባት እያልን እንደምንቆጥረው የዩኒቨርሲቲ ወላጅ የሚለውን ፍልስፍና እውን ያደረገ ዩኒቨርሲቲ ኾኗል፡፡
.
ዘንድሮ ወደ ጎንደር ልጁን የላከ ወላጅ ለልጁ ተጨማሪ ጎንደሬ እናት አባት እንዳገኘ ይወቅ፤ አምስት ሺህ ወላጆች ለዚህ የቤተሰብ ዝምድና ፕሮጀክት ፍቃደኛ ሆነዋል፡፡ አምስት ሺ አዲስ ገቢ ተማሪዎች በታሪካዊቷ የኢትዮጵያ የቀድሞ መናገሻ አንድ ቤተሰብ ይኖራቸዋል፡፡ በተማሪውና በጎንደር ቤተሰቡ መካከል ጠንካራ ዝምድና ይፈጠራል፡፡

ይህ ሪፖርትና እቅድ ብቻ አይደለም፡፡ ጎንደር እጇን ዘርግታለች፡፡ እያንዳንዱ ተማሪ እያንዳንዱ ቤተሰብ እቅፍ ይገባል፡፡ በዓል በዚሁ ቤተሰብ ዘንድ ያከብራል፤ ይህ ቤተሰብ የተማሪውን ደህንነት ይከታተላል፡፡ ወላጃዊ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ አይዞህ ይላል፡፡

የእረፍት ቀንና የበዓል ቀናትን በዚህ ቤተሰብ ዘንድ ያሳልፋል፡፡ አንድ አራት አመታት በጎንደር ቆይታ የሚኖረው ተማሪ ሲጨርስ ከተማዋን እንዲሁ ጥሎ አይወጣም፤ ፍቅር በልቡ ይዞ እንዲሄድ የሚያስችል ፕሮጀክት ነው፡፡

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሰላሙ ዩኒቨርሲቲ የሚል መለያ አለው፡፡ የሚለይበትን ለመሆን ከታች እስከ ላይ አመራሩ ብዙ ደክሟል፡፡ ከፕሮፌሰር መንገሻ እስከ ዶክተር ደሳለኝ፤ ዛሬ ደግሞ ዶክተር አስራትና አመራሮቹ አዲስ ባህልን ለኢትዮጵያ እንካችሁ ብለዋል፡፡

የተማሪ ቤተሰብ ትስስር፤ ተማሪው ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ብቻ ተመርቆ አይወጣም፤ ወዲህ ጎንደሬም ይሆናል፡፡ የአዲስ አለምን የዓሊሞች በረከት ይዞ ይመለሳል፡፡ የአርባ አራቱን ቡራኬ ይቀበላል፡፡ ራሱን ጎንደሬ ብሎ የሚጠራበት የባህል አንባሳደርነት መንፈስን ይወርሳል፡፡ እሱ ከታላቁ ከዐፄ ፋሲል መዲና ቤተሰብ ያለው የሁለት ወላጅ ልጅ ነውና፤ የተማሪ ቤተሰብ ትስስሩ ቀላል አይደለም፡፡

አንድ ተማሪ የጎንደር ቆይታውን ሲያጠናቅቅ ከዲግሪው ጋር “እታታይ” የሚላት ስፍስፍ የአደራ እናት አግኝቶ ይመለሳል፡፡ ይሄ የትም ቢሆን ደስ የሚለኝ ለሀገሬ የሚያስፈልግ አዲስ የደከመ የአብሮነት መንፈሳችን ማበርቻ ዘዴ ነው፡፡

ከሞያሌም ይምጣ ከሚዛን አማን፣ ከጋምቤላም ይሁን ከአሶሳ ከዛላአምበሳም ይሁን ከቡሬ ጎንደር የደረሰው ተማሪ ቤተሰቤ ሩቅ ነው አይልም፤፤ ይልቁንስ ሩቅም ቅርብም ቤተሰብ አለው፡፡ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ እውን ያደረገው ይህ ፕሮጀክት የጠብ፣ የቁርሾና የክፉ መዓት መሸሸጊያ ለሆኑት የሀገራችን ዩኒቨርሲቲዎች ጥሩ ልምድ ይመስለኛል፡፡

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top