Connect with us

ውስኪ ከሚጠጣው መንገድ የሚዘጋው የደሃ ጉሮሮ ዘግቷል

ውስኪ ከሚጠጣው መንገድ የሚዘጋው የደሃ ጉሮሮ ዘግቷል
Photo: Facebook

ፓለቲካ

ውስኪ ከሚጠጣው መንገድ የሚዘጋው የደሃ ጉሮሮ ዘግቷል

ውስኪው ገንዘባችንን ጨርሶ ንጹህ ውሃ እንዳንጠጣ ቢያደርገንም ወንዝ ሄደን እንዳንቀዳ ግን አታልፉም አላለንም፡፡
****
ከስናፍቅሽ አዲስ

ውስኪ የሚራጭ ሹመኛ ብርቃችን አይደለም፤ ለእኛ ብርቅ ውስኪ መራጨት ነው፡፡ መንገድ ተዘግቶብን መሄድ የለም የሚል ጎረምሳና ፖሊስ ሲቀናጅ ማየት ግን ብርቅ ነው፡፡ ልምዳችንን ብርቅ፣ ብርቃችንን ልምድ ማድረጉ ማደናገር ነው፡፡ ለነገሩ መደናገርም ብርቃችን አይደለም፡፡

ጨዋታው ከጅብ ወደ ውስኪ ተቀይሯል፡፡ የአምናውን እያሙ ዘንድሮ ካምናው አለመሻል ዛሬ የጀመረ ጠባያችን አይደለም፡፡

ኢህአዴግ ደርግን በኮነነባቸው ሐጢአቶች በሙሉ እጁን ነክሮ አይተንዋል፡፡ ዘጠናዎቹ ላይ ግንቦት ሃያን ስናከብር ደርግ ስለአፈነብን የመጻፍ ነጻነት እያወራን ነበር፤ ቀበሌ ስኳር ተሰልፎ መግዛት የጓድ ሊቀመንበርና የሥርዓታቸው ውድቀት ማሳያም ሆኖ ተቀስቅሶበታል፡፡ ይሄ ሁሉ በተሳለቀበት በኢህአዴግ ሲሆን ለማየት ግን ከአሰር ዓመት በላይ አልጠበቅንም፡፡

የለውጥ ሃይሉ መለወጥ ያስፈለገን ቀድሞ ሰብዓዊ መብት የምንጥስ፣ አንዱ ልጅ ሌላው የእንጀራ ልጅ የሆነበት ሀገር ስለፈጠርን፣ ሳናጣራ ስለአሰርን ተብለን ነበር፡፡ ጓዶች በጓዶቻቸው ላይ የቆጠሩት ሀጢአት መልሶ እውን ሲሆን ሁለት አመት እንኳን የእፎይታ ጊዜ አልሰጠንም፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ መጽሐፍ ምረቃት ብሔራዊ ኩነት መሆኑ አግባብ ነው አይደለም የሚለውን ለሌላ ቀን እናሳድረውና ብሔራዊ በዓል ቀን በመሰለው የአንድ ኢትዮጵያዊ መጽሐፍ ምረቃ ላይ ደራሲው ባደረጉት ንግግር ውስኪ ጠጪዎችን ኮንነዋል፡፡ እርግጥ ነው ውስኪ ጠጪ ኢህአዴጎች ንጹህ ውሃ የማይጠጣ ኢትዮጵያዊ እንዳለ ቢያስቡ ጥቅሙ ለእኛው ነው፡፡ በውስኪ ጠጪዎች ከደረሰብን መከራ ይልቅ የመንገድ ዘጊዎቹ ግን ይከፋል፡፡

ውስኪ ጠጪዎቹ የአለመድነውን ባህል አላሳዩንም፡፡ ቀድሞውኑም ሹማምንት ውስኪ ጠጪዎች ናቸው፡፡ ድሮም ደሃና ህዝብ የውስኪ ብር ገባሪ ነው፡፡ ሸጋ መሪን ስናነጻጽር የኖርነው ከውስኪው ተርፎበት ባደረገልን ልማት እንጂ በመናኝነት ሕይወቱ አልነበረም፡፡ ውስኪው የዕለት ሕይወታችንን አላናጋውም፤ ውስኪው ገንዘባችንን ጨርሶ ንጹህ ውሃ እንዳንጠጣ ቢያደርገንም ወንዝ ሄደን እንዳንቀዳ ግን አታልፉም አላለንም፡፡

ከመኮነን የሚኮነን ስራን መራቅ ይጠቅማል፡፡ ዛሬ ማንም ተነስቶ መንገድ በሚዘጋበት ሀገር ይበልጥ የህዝቡን የዕለት ኑሮ የትኛው መቼና እንዴት እያቃወሰ እንዳለ አጢኖ ሰላማዊ ሀገር ቢፈጠር ለሁላችንም ይበጅ ነበር፡፡ ውስኪ ጠጪዎቹ ቢያንስ ከሚጠጡበት ወንበር ሳይነሱ ከዳር ዳር ሀገር ሰላም እንድትሆን ቀጭን ትዕዛዝ አስተላላፊዎች እንደነበሩም መርሳት የለብንም፡፡

ዛሬ መሬቱም ሰማዩም የባለጊዜዎች ሆኗል፡፡ መንገድ ፖሊስና ጎበዝ ተባብረው የሚዘጉበት፣ ወጥቶ መግባት በባለግዜዎች መልካም ፍቃድ የተመሰረተበት እየመሰለ ነው፡፡ እንጥፍጣፊ ተስፋ ለመጫር የሆነውን እየመሰለ ነው ከማለት የሚበልጥ ትህትና የለም፤ እናም ጠቅላያችን ከውስኪ ጠጪው መንገድ ዘጊው ለጎዳው ደሃ ህዝብ ከአምናው የከፋ ቀን እንዳይመጣበት ደጋግመው ያጢኑና የሚበጀውን ያድርጉ

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top