ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከል እየተንቀሳቀሰ ያለው የአዲስ አበባው አስተባባሪ ኮሚቴ የላከው መግለጫ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናት እና ምእመናን ላይ በተለያዩ አካባቢዎች የሚደርሰው ጥቃት እንዲቆም የሚንቀሳቀሰው የአዲስ አበባ አስተባባሪ ኮሚቴ መስከረም 2 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በየጊዜው የሚኖረውን የውይይት ሒደት እና ውጤት፣ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ለማሳወቅ በገባው ቃል መሠረት የመጀመሪያውን መግለጫ መስጠቱም ይታወሳል። ኮሚቴው ካከናወናቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከል፡-
1. ከየክልሉ ርእሳነ መስተዳድሮች ጋር የተደረጉ ውይይቶችን በመከታተል የተገቡ ቃሎች እንዲፈጸሙ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።
❖ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአብያተ ክርስቲያናት የይዞታ ማረጋገጫ ጥያቄዎች ተግባራዊ ምላሽ የመስጠት ሂደቱ በተጠናከረ ሁኔታ ቀጥሏል፡፡
❖ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የተገቡ ቃሎች ትግበራ በተቻለ ፍጥነት እንዲሔድና ተግባራዊ ምላሽ ለመስጠት ከተማ አስተዳደሩና ክልሉ እያደረጓቸው ያሉ ጥረቶች አሁንም በተጠናከረ ሁኔታ ቀጥለዋል፡፡ በዚህ አጋጣሚ የክልሉንና የከተማ መስተዳድሮች ከፍተኛ አመራሮችን በቤተ ክርስቲያናችን ስም ሳናመሰግን አናልፍም። የእነዚህን ያህል ባይሆንም ከኦሮሚያ ክልል በስተቀር በሌሎች ክልሎችም ተስፋ ሰጪ ጅምሮችና እንቅስቃሴዎች አሉ።
❖ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በክልሉ የተፈጠሩና እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ለዘብተኝነት እያሳየ ነው። ኮሚቴው ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በችግሮች ላይ በተወያየበት ወቅት “በክልላችን መዋቅራዊ ጥቃቶች አሉ ብለን ባናምንም በግለሰቦች የሚፈጠሩ ችግሮች ስለሚኖሩ፣ እነዚህን ችግሮች በማጣራት መፍትሔ እንሰጣለን” ብሎ ቃል ቢገባም እስካሁን ምንም ተጨባጭ ውጤት ሊያመጣ እንዳልቻለ ለሕዝበ ክርስቲያኑ በግልጽ ለማሳወቅ እንወዳለን።
2. ከመስቀል በዓል ጋር በተያያዘ የፌደራል ፖሊስ በሰጠው መግለጫ ምክንያት የታሠሩ ኦርቶዶክሳውያን እንዲፈቱ ተደርጓል። ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ጋርም በተደረገው ውይይት በመስቀል በዓል አከባበር ላይ በአንዳንድ የጸጥታ ኃይሎችና ሕገ ወጥ ቡድኖች ምክንያት የተፈጠረውን ችግር ከክልሎች የፖሊስ ኮሚሽነሮች ጋር በመገምገም የመፍትሔ አቅጣጫ ለማስቀመጥና አስፈላጊውን እርምት ለመውሰድ ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
3. በክልሎች ደረጃ የተደረጉ ውይይቶችን አፈጻጸም በቅርበት ለመከታተልና ቀጣይ ችግሮች እንዳይፈጠሩ በቅንጅት ለመሥራት ከመንግሥት እና ከየአህጉረ ስብከቱ የተውጣጡ አካላት ያሉበት የጋራ ኮሚቴ በየዞኖች ተቋቁመው በክልሎቹ በተቋቋሙት የጋራ ኮሚቴዎች አስተባባሪነት፣ በየዞኖቹ በመንግሥት እና በቤተ ክርስቲያን ተወካዮች መካከል ውይይቶች መካሔድ ጀምረዋል።
በአንዳንድ ዞኖች የትግበራ ዕቅድ አውጥተው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ። በዚህ አጋጣሚ ሕዝበ ክርስቲያኑ በየዞኖቹ የተቋቋሙት ኮሚቴዎች ውስጥ በንቃት እንዲሳተፍ፣ መረጃዎችን እንዲሰጥ እና ተገቢውን ድጋፍ በመስጠት ክርስቲያናዊ ግዴታውን እንዲወጣ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
በዚህ አጋጣሚ፡-
• የፌደራል ፖሊስ የመስቀል በዓልን አስመልክቶ በዋዜማው ዕለት የሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫና መግለጫውን ተከትሎ በአረንጓዴ፣ ቢጫ ቀይ ቀለማት የተዋቡ አልባሳትን በለበሱ ምእመናን ላይ ፖሊስ ይፈጽመው የነበረው የማንገላታትና የማመናጨቅ ተግባር አግባብነት የሌለው በመሆኑ ሊታረም ይገባል።
መግለጫው ብዙ ምእመናን ወደ ደመራ በዓሉ እንዳይወጡ፣ የወጡትም በስጋት እንዲያሳልፉ ከማድረጉም በላይ በአንዳንድ አካባቢዎች በዓሉ በሰላም እንዳይከበርና ሁከት እንዲፈጠር ያደረገ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ የፌደራል ፖሊስ ቃል በገባው መሠረት ገምግሞ አስፈላጊውን እርምት እንዲወሰድ እንጠይቃለን።
• የመስቀል በዓል በታላቅ ድምቀት የሚከበር የዐደባባይ አገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ በዓል ሆኖ ሳለ በአንዳንድ አካባቢዎች ሕዝበ ክርስቲያኑን ለግጭት በሚያነሣሣ መልኩ በጸጥታ አካላት አላስፈላጊ እርምጃዎች ሲወሰዱ ተስተውለዋል።
እንዲህ ዐይነት ድርጊቶች ወዳልተፈለገ ግጭት የሚያመሩና በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ፊት የአገር ገጽታን የሚያበላሹ ከመሆናቸውም በላይ የሕዝበ ክርስቲያኑ ትዕግሥትና ማስተዋል ታክሎበት እንጂ የከፉ ችግሮች እንዲፈጠሩ የሚጋብዙ ስለሆኑ በአስቸኳይ እርምት እንዲደረግባቸው እንላለን።
• በኦሮሚያ ክልል በአንዳንድ አከባቢዎች ከመስቀል በዓል አከባባር ጋር በተያያዘ በዝምታ ሊታለፉ የማይችሉ ችግሮች ተፈጥረዋል።
– በደብረ ዘይት ከተማ የመስቀል ደመራ በዓል ላይ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች የለበሳችሁትን ዩኒፎርም አውልቁ መባላቸው፣ በዚሁም ምክንያት የመስቀል ደመራ በዓል ሳይከበር መቅረቱና ደመራው ሌሊት በሕገ ወጥ ቡድኖች መቃጠሉ፣
– በጅማ ከተማ ለመስቀል ደመራ በዓል የወጡ ምእመናን መደብደባቸው፣
– በሻምቡ ከተማ በዓሉ ሲከበርበት ከነበረው መስቀል ዐደባባይ ውጪ ሌላ ቦታ አክብሩ ተብለው መከልከላቸው ቤተ ክርስቲያናችንን በእጅጉ ያሳዘኑ ታሪካዊ ስሕተቶች ናቸው።
በእነዚህ አካባቢዎች ምእመናን በዓሉን በሰላም እንዳያከብሩ ክልከላዎችን ያደረጉ፣ በሕዝበ ክርስቲያኑ ላይ ድብደባ የፈጸሙ እና ምእመናንንና አስተባባሪዎችን በማሰርና በማንገላታት የበዓሉን ድባብ ሰላማዊ እንዳይሆን ያደረጉ የመንግሥት አካላት ሊታረሙና አስፈላጊው እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል።
በተጨማሪም ከግሸን ደብረ ከርቤ ክብረ በዓል የሚመለሱ ምእመናን በየመንገዱ በተደራጁ ወጣቶች እብሪት የተሞላበት የጥቃት ተግባር ተፈጽሞባቸዋል።
የክልሉ መንግሥትም ይህን ነውረኛ ድርጊት በዝምታ በመመልከት መንግሥታዊ ሚናውን ሳይወጣ ቀርቷል፡፡ አሁንም በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች ሃይማኖታዊ ጫናዎች እና ማንገላታቶች ቀጥለዋል። የቤተ ክርስቲያን ይዞታዎችን መውረር፣ መጋፋት እንዲሁም ቤተ ክርስቲያንን እና የኦርቶዶክሳውያን ቤቶችና ሱቆች ማፍረስ ተባብሶ ቀጥሏል። መንግሥት በእነዚህ ሕገ ወጥ ድርጊት ፈጻሚዎች ላይ እርምጃ አለመውሰዱ ጥፋቱን እንዲባበስ አስተዋጽኦ አድርጓል።
የክልሉ መንግሥት ይህን እያደረጉ ባሉ ቡድኖችና የመንግሥት አካላት ላይ አስፈላጊውን አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ፣ እየተፈጠሩ ላሉ ችግሮችም በአፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጥ እንጠይቃለን።
• በአንዳንድ ሚዲያዎችና ግለሰቦች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ እየተሰነዘሩ ያሉ ጸያፍና ከፋፋይ የሐሰት ትርክቶች፣ የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ የማጉደፍና የማጣጣል ድርጊቶች እንዲሁም ቤተ ክርስቲያንን ባልዋለችበት በማዋል የከበረ ስሟን በሐሰት የማጥፋት ዘመቻዎችን እያወገዝን በሕግ ለመጠየቅ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ላይ እንገኛለን፡፡
በቀጣይም መላው ሕዝበ ክርስቲያኑ አንድነቱን የበለጠ እንዲያጠናክር፣ የቤተ ክርስቲያንን መብት በተገቢው ሰላማዊ መንገድ እንዲያስከብር እና በኮሚቴው የሚሰጡትን ቀጣይ አቅጣጫዎች በንቃት እና በትዕግሥት እንዲጠብቅ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ጥቅምት 7 ቀን 2012 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፤
ኢትዮጵያ !